>

የሱሌይማን ደደፎ ደብዳቤ! (ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ)

የሱሌይማን ደደፎ ደብዳቤ!
ኤርሚያስ ለገሰ ዋቅጅራ
* ጅቡቲ ይህን ህገወጥ አሰራር ለአለም አቀፍ የመርከበኞች ማህበር ሪፖርት ካደረገች ኢትዮጵያ በጥቁር መዝገብ ሰፍራ መርከቦቹ በደረሱበት እንዲያዙ ይደረጋል።
 
*  አንድ ኢትዮጲያዊ መርከበኛ በስራ ላይ እያለ አደጋ ደርሶበት እንዳይታከም በመከልከሉ ከብዙ ስቃይ በኃላ ወደ ሆስፒታል ሲሄድ ጉዳቱ ወደ ጋንግሪን በመቀየሩ እግሩ እንዲቆረጥ ታዟል። 
በሕውሓቱ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ስለሚመራው የመከላከያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፕሬሽን ( ሜቴክ) ሌብነት እና ዝርፊያ ብዙ ተብሏል። እድሜ ይስጠን እንጂ ለወደፊቱም እጅግ በጣም ብዙ ይባላል። በትክክልም ይህ በእውቀት አልቦነት እና ማን አለብኝነት የሚንቀሳቀስ ኮርፖሬሽን በአንድ በኩል የአገሪቱ መፃኢ እድል እያጨለመ፣ በሌላ በኩል የሕውኃት የግል ንብረት የሆነውን ኤፈርት የፋይናንስ አቅም እያደለበ እንዲሄድ በማድረጉ ምክንያት ጊዜ አጥፍቶ መነጋገሩ ቢያንስ ከህሊና ተጠያቂነት የሚያድን ይሆናል። ዘለግ ባለ ሁኔታ መነጋገሩ ፍሬ ካፈራ ደግሞ የህውሓቶችን የዘረኝነት አምድ ለማፈራረስ ፣ የአገር መግደያ ሃይላቸውን ለመደምሰስ እና የአፓርታይድ መሰል ፓሊሲና አካሄዳቸውን ለመግታት የሚረዳ ይሆናል።
 እርግጥ ለሁላችንም የማይካድ አንድ ሐቅ አለ። ሲጋራን በቄንጥ ከማጨስ ውጭ ሌላ ዘመናዊ እውቀት የሌላቸው የሜቴክ ጄኔራሎች ገደብ የለሽ በሆነው ዝርፊያቸው ታውቀዋል። በተለይ ዋና ዴሬክተር የሆነው ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የመቶ ፐርሰንት የሕውኃት/ ኢህአዴግ ፓርላማ ላይ ቀርቦ ያቀረበው ማስፈራሪያ የአመቱ አስገራሚ ንግግር ተደርጐ የተወሰደ ነው። በግሌ የጄኔራሉን መረን የለቀቀ ድንፍታ የሰማሁ እለት የተሰማኝን ሐዘን የምገልፅበት ቃላት ማግኘት ባለመቻሌ አልታደልኩም። እንደ እውነቱ ከሆነ ጥልቅ ሀዘኔን መጠን የለሽ ያደረገው የተወዳጁ ፓርላማ መዘለፍ ብቻ ሳይሆን ሸንጐው የምን አይነት ሰዎች ስብስብ እንደሆነ ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ በመሆኑ ነው። ተደጋግሞ የተገለጠ ቢሆንም ፓርላማው የፈሪዎች፣ የአድርባዬችና የደንቆሮዎች ስብስብ መሆኑ በአደባባይ የተጋለጠበት ሆኗል።
  አሁን አሁን ሜቴክን የተመለከቱ የግላጭም ሆነ በሚስጥር ሾልከው የሚወጡ ደብዳቤዎች ኮርፖሬሽኑ የደረሰበትን አደገኛ ሁኔታ የሚያመላክቱ ሆነዋል። አምና በተመሳሳይ ወቅት ላይ ከመንገዶች ባለሥልጣን መስሪያቤት ለኢሳት የደረሰውና ለህዝብ ይፋ የሆነው መረጃ መነጋገሪያነቱ አሁንም አላባራም። በወቅቱ ይፋ እንደተደረገው ሜቴክ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተረከበውን ግምታቸው ከ65 ሚሊዬን በላይ የሆኑ ከ88 በላይ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጠግኖ ማስረከብ ሲጠበቅበት በሕውኃት ትእዛዝ ለትግራይ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ያስተላልፋል ።
   ሁኔታው ግራ ያጋባው የመንገዶች ባለስልጣን ዋና ዴሬክተር ዛይድ ወልደገብርኤል ተደጋጋሚ ደብዳቤዎችን ለሜቴክ እና ለገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ይጽፋል ። ለደብዳቤው ምላሽ የሚሰጥ ይታጣል ። ከዚህ በተጨማሪም በአለም ባንክ ኤዲተሮች የስንግ  የተያዘው የኢትየጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ተቀዳሚ ዋና ዴሬክተር የሆነው አቶ ሲሳይ በቀለ አንድ ጊዜ በትሕትና ሌላ ጊዜ በልመና ሜቴክ የወሰደውን ንብረት እንዲመልስ ይጠይቃል። አሁንም ምላሽ የሚሰጥ ይጠፋል። የኮንስትራክሽን ማሽኖችን ከንብረት መዛግብት የመሰረዝ ስልጣን ያለው የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በደብዳቤ ቢጠየቅም መጽሐፉም ዝም ቄሱም ዝም ይሆናል።
  ሁኔታዎች እየከፋ ሲሄዱ በኢትየጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የሚሰሩ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ህዝብ እየተፈፀመ ያለውን ዝርፊያ እንዲያውቅ በማሰብ በጥብቅ ሚስጥር ለኢትዮጵያ ሳተላይት ሬዲዬ እና ቴሌቪዥን (ኢሳት) እንዲደርስ ያደርጋሉ። ይህ ከ16 ገፆች በላይ የያዘ ዝርዝር መረጃ በሚዲያው ይፋ ከሆነ በኋላ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆነ።  ከወንጀለኝነቱ ባሻገር ሜቴክ ለምን ለኦሮሚያ፣ ለምን ለአማራ፣ ለምን ለቤኔሻንጉል፣ ለምን ለሱማሌ ወይም አፋር አላስተላለፈም የሚል ሰፊ ጥያቄ ተነሳ።ለኢፍትሐዊነት እና ዝርፊያ ከዚህ በላይ ምን ማሳያ ሊመጣ ይችላል የሚለው አነጋጋሪ ሆነ።
  እነሆ! አመቱን ጠብቆ ሌላ አስደንጋጭ ደብዳቤ ለኢሳት ደረሰ። የደብዳቤው ባለቤት የጅቡቲ አምባሣደር የነበረው ሱሌማን ደደፎ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለነበረው ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተፃፈ ነበር። በአቶ በረከት እጅግ የሚጠላውና በህውሃቶች ዘንድ በኦነግነት የሚጠረጠው ሱሌይማን በአስደንጋጩ ደብዳቤው በኢትየጵያ ንግድ መርከቦች ላይ የተጋረጠውን አደጋ ግልጥልጥ አድርጐ አመላክቷል ። የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ንብረት የነበሩት ” አብዬት” እና ” አባይ” የተባሉት ሁለት መርከቦች በሕውኃት መራሹ መንግሥት ውሳኔ ለሜቴክ የተሸጡ ቢሆንም በጅቡቲ ወደብ ላይ መልህቃቸውን ጥለው በመቆማቸው በመቶ ሚሊዬን ብሮች በአገዛዙ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አሳውቋል።
 እየደረሰ ያለውን ጉዳት እንደሚከተለው ገልጿል ፣
        ” መርከቦቹ በሽያጭ ወደ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከተዘዋወሩ ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ በጅቡቲ ወደብ ላይ መልህቅ ጥለው በመቆም ላይ ይገኛሉ። ለዚህም ባህር ላይ የቆሙበትን ሂሳብ በየቀኑ ከሁለት ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ እየተከፈለ እስካሁን ድረስ ምንም ገቢ ሳያገኙ 391 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተከፍሎባቸዋል። መርከቦቹ ባህር ላይ መልህቅ ጥለው በሚቆሙበት ወቅት ሞተሮቹም ሆነ የኃይል ማመንጫ ጄኔሬተሮች እየሰሩ ስለሚቆይ የነዳጅ ወጭና የምድብተኞች መኖሪያ ከአንድ ሚሊዬን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል” በማለት ይገልፃል።
    አቶ ሱሌይማን በደብዳቤው ላይ በስድስት ወራት ብቻ ከአንድ ሚሊዬን 400ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላር ወጪ መደረጉን ይናገራል። ከአንድ ደሃ አገር ሀብት ላይ ይህን ያህል ብክነት መድረሱን በቁጭት ይገልፃል። ከፍተኛ ደሞዝ የሚከፈላቸው የውጭ ሀገር ዜጐችም ያሉበት 36 መርከበኞች ያለስራ ደሞዝ ለሚወስዱት ተጠያቂ ማነው በማለት ጥያቄ ያነሳል።
  የቀድሞ አዲሳአባ ምክርቤት ወዳጄ በዚህ ደብዳቤው ለኢትዮጵያ ህዝብ አስደንጋጭ መርዶ ይናገራል። መርከቦቹ ነዳጅ በመጨረሳቸው ሞተሩና ጄኔሬተራቸው ጠፍተዋል። የመርከቡ ዋና ኢንጂነር ጋናዊው ሳሙኤል አማኮ ጨምሮ ሌሎች መርከበኞች የአገዛዙ አካሄድ በአለምአቀፍ ህግ የማይገዛ መሆኑን ለባህሩ ባለቤት ለሆነችው ጅቡቲ አቤቱታ አቅርበዋል። ጅቡቲ ለአለም አቀፍ የመርከበኞች ማህበር ሪፓርት ካደረገች ኢትዮጵያ በጥቁር መዝገብ ሰፍራ መርከቦቹ በደረሱበት እንዲያዙ ይደረጋል። አንድ ኢትዬጲያዊ መርከበኛ በስራ ላይ እያለ አደጋ ደርሶበት እንዳይታከም በመከልከሉ ከብዙ ስቃይ በኃላ ወደ ሆስፒታል ሲሄድ ጉዳቱ ወደ ጋንግሪን በመቀየሩ እግሩ እንዲቆረጥ ታዟል።
   ሱሌይማን በዚህ ደብዳቤው የሕውሐት አገዛዝ በአለም አቀፍ ሕግ ወንጀል እየፈፀመ እንደሆነ ሳያቅማማ አጋልጧል። ምን አልባት ይሄ ደብዳቤ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአለም የጤና ድርጅት ሲወዳደሩ ተጋልጦ ቢሆን ኖሮ ውጤቱን ይገለብጠው ነበር። አሁንም ቢሆን ሀሞተ ኮስታራ ኢትዬጲያዊ ሰው ካለ አለም አቀፍ አደባባይ ለማቅረብ የዘገየ አይደለም።
ለማንኛውም አለም አቀፍ ወንጀል እንደሆነ በሱሊማን ደደፎ የተገለፀው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፣
      ” ከተገዙት መርከቦች መካከል አንዱ በአሁኑ ሰአት ካፒቴን የሌለው በመሆኑ መርከብን ያለአዛዥ ውሃ ላይ ማቆም በአለምአቀፍ ህግ ወንጀል በመሆኑ ጉዳዩ በሌሎች ሳይታወቅ/ ሳይጋለጥ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። መርከቦቹን  ያለምድብተኞች ውሃ ላይ መተው በአለምአቀፍ ህግ ተከለከለ ነው” በማለት ይገልፃል።
 ሱሌይማን ለዚህ ሁሉ ወንጀል ተጠያቂው ማን እንደሆነ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ በግልፅ አመላክቷል።
   እንዲህ በማለት፣
   ” ስለዚህ ሁኔታው አሁን አገራዊ ጉዳይ በመሆኑ ከቁጥጥር ውጭ በመውጣቱ እና የንግድ መርከብ ድርጅታችንን መልካም ስምና የአገር ገፅታ ከማበላሸቱ በፊት የብረታ ብረት ኮርፕሬሽን ከያዘው ህገ ወጥ አድራጐት እንዲቆጠብ መመሪያ እንዲሰጥበት” በማለት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለነበረው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ያሳውቃል ።
 አሁን ጥያቄው ዶክተር ቴድሮስ የተባለውን አደረገ ወይ ይሆናል?… አሁን ጥያቄው በአገዛዙ ወንጀል እግሩ በጋንግሪን የተቆረጠው ሰው ምን ፍትህ አገኘ ይሆናል?…  አሁን ጥያቄው በአለማቀፍ ህግ ወንጀል የፈፀመ ሰው የአለም ጤና ድርጅት የበላይ ሐላፊ ሆኖ መቀጠል ይችላል ወይ? የሚለው ይሆናል።
Filed in: Amharic