>
5:14 pm - Monday April 20, 4426

በብድር መያዣ ስም አገር መሸጥ ማለት ይህ አይደል?!? (ስዩም ተሾመ)

በብድር መያዣ ስም አገር መሸጥ ማለት ይህ አይደል?!?
ስዩም ተሾመ
የኤርትራ፣ #አሰብ፣ #መተማና #ባድመ መሬትና ወደብ ተላልፈው የተሸጡትና የተሰጡት ከ20 አመት በፊት ነው። ከሁለት አስርት አመታት በፊት የሆነን ነገር ወደኋላ ተመልሶ ማሰብና አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ማቅረብ አዳጋች ነው። ሆኖም ግን ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የፈፀሙትን ተግባር ግን መዋሸት ሆነ መደበቅ አይችሉም። ምክንያቱም ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም (እ.አ.አ ከ2013 – 2018) ባሉት አመስት አመታት ሀገሪቱን ለመሸጥ የፈፀሟቸው ተግባራት በግልፅ የሚታዩና በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፉ ናቸው።
ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት 90% የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚካሄደው በአሰብ ወደብ፣ 5% በምፅዋ ወደብ እና የተቀረው 5% በጅቡቲ ወደብ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ 95% የገቢና ወጪ ንግድ በጅቡቲ ወደብ በኩል ሆነ። በዚህ ምክንያት ለጅቡቲ መንግስት የመጠጥ ውሃ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ ጀምሮ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መዘርጋት የሀገሪቱን የገቢና ውጪ ንግድ ለማቀላጠፍ መልካም ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ብድር ስምምነት ማድረግ ተገቢ ነው።
በቻይና አምባሳደር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን እና ብርሃነ ገብረክርስቶስ አማካኝነት በተሰራ “የዲፕሎማሲ” ስራ ከፍተኛ የገንዘብ ብድር ማግኘት ተቻለ። በዓለም ላይ ካሉት ግዙፍ የንግድ ባንኮች ከሚያስከፍሉት ጋር ተቀራራቢ በሆነ የወለድ መጠን በአስር አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ 13.5 ቢሊዮን ዶላር ከቻይና ተበደረች። ከዚህ ውስጥ ወደ 6.5 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው በ2006 ዓ.ም (እ.አ.አ. በ2013) የተገኘ ብድር ነው። ከዚህ ውስጥ 3 ቢሊዮን ዶላሩ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ለመዘርጋት የዋለ ነው። በተመሳሳይ ጅቡቲ ትልቅ ወደብ ለመገንባት ከቻይና የ1 ቢሊዮን ዶላር ብድር ስምምነት ከቻይና ጋር ተፈራረመች።
በኢትዮጵያምሆነ በጅቡቲ ከቻይና በተገኘው ብድር የሚሰሩት የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር እና የጅቡቲ ወደብ የግንባታ ስራው ለቻይና ተቋራጭ ድርጅት ተሰጠ። ይህ የግንባታ ድርጅት እ.አ.አ. በ2016 ዓ.ም የባቡር መስመሩን ዘርግቶ ለማስረከብ ውል ገባ። ይሁን እንጂ የባቡር መስመሩ ተጠናቅቆ በተግባር ሥራ የጀመረው ከሁለት አመት መዘግየት በኋላ በ2018 መጀመሪያ ላይ ነው። የቻይና ተቋራጭ ድርጅት በውሉ መሰረት ግንባታውን ባለማጠናቀቁ ምክንያት የባቡር መስመሩ በታቀደለት ግዜ አልጀመረም።
ይሁን እንጂ ከ2016-2018 ባሉት ሁለት አመታት ውስጥ የባቡር መስመሩ ተገንብቶ ሥራ ሳይጀምር ብድሩን ለቻይና ሲከፈል ቆይቷል። በዚህ መሰረት የቻይና ተቋራጭ ድርጅት በውሉ መሰረት ሥራውን ሰርቶ ባለማጠናቀቁ፣ በዚህም ከቻይና የተወሰደው ብድር በኢኮኖሚው ውስጥ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምር ኢትዮጵያ ዕዳ ስትከፍል ቆይታለች። በብድር የተገኘው ገንዘብ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምር ዕዳ መክፈል ያልሰሩበትን ገንዘብ ከደሃ ሀገር ላይ እንደ መቀማት ነው።
ባለፈው አመት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ከተፈጠረባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያ ያለ አግባብ ለቻይና የምትከፍለው የብድር ዕዳ ነው። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የብድር መጠን ከጠቅላላ የሀገሪቱ የምርት መጠን 59% ላይ ደርሶ ነበር። በዚህ መሰረት የዕዳ መጠኑ በሀገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ አደጋ ለመጋረጥ የቀረው 1% ብቻ ነው። የብድር መጠኑ 60% እና ከዚያ በላይ ከሆነ ማንኛውም የፋይናንስ ተቋም ለኢትዮጵያ ብድር አይሰጥም። ምክንያቱም ሀገሪቱ የወሰደችውን ብድር የመክፈል አቅም የላትም። በመሆኑም ለሀገሪቱ ከፍተኛ ብድር የሰጡ ሀገራት ያበደሩት ገንዘብ እስኪመለስ በሚል የኢትዮጵያን ሃብትና ንብረት የመውረስ መብት አላቸው።
ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንፃር ሲታይ የጅቡቲ ኢኮኖሚ በጣም ትንሽ ነው። በመሆኑም ሀገሪቱ ከቻይና የወሰደችው ብድር መጠን ከሀገሪቱ ጠቅላላ የምርት መጠን ውስጥ 88% ሆኗል። ስለዚህ ጅቡቲ ከየትኛውም ሀገርና የፋይናንስ ተቋም ብድር መጠየቅና ማግኘት አትችልም። በዚህ መሰረት ጅቡቲ ወደቧን ሲያስተዳድር ከነበረው የዱባይ ኩባንያ ጋር የነበራትን ውል በመሰረዝ ለቻይና ኩባንያ ሰጠች። ከዚህ በተጨማሪ የቻይና መንግስት በጅቡቲ የራሱን የጦር ሰፈር በመገንባት 2500 ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ አፍንጫ ስር አምጥቶ አሰፈረ።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በውጪ ምንዛሬ እጥረት ለመውደቅ የቀረው 1% ነው። ስለዚህ እየተንገዳገደ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሲወድቅ ቻይና የሰጠችውን ብድር ለማስመለስ በሚል ልክ እንደ ጅቡቲ የኢትዮጵያን መሬትና ሃብት የመውረስ መብት አላት። በዚህ መሰረት ቻይና የኢትዮ-ጅቡቲን የባቡር መስመር ለመውረስ ቅድመ-ዝግጅቷን አጠናቅቃለች። ለዚህ ደግሞ ቻይና 95% የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚተላለፍበትን የጅቡቲ ወደብ ተቆጣጥራለች። ከዚህ በተጨማሪ የራሷን የጦር ሰፍር በመገንባት 2500 የሚሆኑ ወታደሮቿን አስፍራለች። ከጥቂት ወራት በኋላ ኢትዮጵያ ከቻይና የወሰደችውን ብድር መክፈል ያቅታታል። ቻይና ብድሯ እስኪመለስ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር እንዲሰጣት ትጠይቃለች። “እምቢ” ካለች ደግሞ 95% የገቢና ወጪ ንግድ የሚተላለፍበትን ወደብ “ሲጥ” በማድረግ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬትና ሃብቷን እንድትሰጣት ታደርጋለች። ታዲያ ሀገር መሸጥ ማለት ይሄ አይደለም?
Filed in: Amharic