>
5:13 pm - Wednesday April 18, 7601

ቀጣዩን ምርጫ ተወዳዳሪ ባልሆንም የዳር ተመልካች አልሆንም!!! (ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ)

 

ቀጣዩን ምርጫ ተወዳዳሪ ባልሆንም የዳር ተመልካች አልሆንም!!!

 

ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ

 

ቢሲሲ

 

ከሰሞኑ ከ7 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት የቀድሞዋ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አመራርና የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ መስራችና መሪ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ያለፈውን የፖለቲካ ትግላቸውንና የወደፊት ውጥናቸውን በተመለከተ ከቢሲሲ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

ጥያቄ- አሁን ጊዜው ወደሀገር ቤት የምመለስበት ነው ብለው የወሰኑበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

ወ/ት ብርቱካን-የወሰንኩበት ቀንና ሁኔታ እንደዚህ ነው ብዬ መናገር ባልችልም በሀገራችን ያለው የለውጥ ሂደት ከመነሻው ጀምሮ በዚህ የለውጥ ሂደት ሕይወቱን ሰጥቶ እንደነበረ ሰው በደስታም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በመስጋትም የምከታተለው ነገር ነበር። በጣም ጥሩ የሚባሉ ነገሮች ተከናውነዋል፤ አንደኛ ለውጡ ከውስጡ ጭቆናን ሲፈጥር በነበረው አገዛዝ አካል መሪነት የሚከናወን መሆኑ ሀገራችን ልትገባበት ከነበረው ቀውስ ያዳናት ይመስለኛል። ያው የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ ፣ለሚዲያ የተሻለ ነገር ሲፈጠር ጎን ለጎን ደግሞ የሚያሳስቡኝ ነገሮች ይታዩኝ ነበር ፤ የህግ የበላይነትን ማስጠበቅ እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥ በኩል የታዩ ችግሮችን እንደ ሀገር ካላስወገድንና የዲሞክራሲ ለውጡን ወደ ተሻለ ሂደት ካልለወጥነው፤ በፊት ከነበርንበትም ወደበለጠ ችግር ውስጥ ልንገባ እንደምንችል ተመልክቻለሁ ። እናም ሁላችንም የምንችለውን ነገር አድርገን የዴሞክራሲ ለውጡ ሊመለስ ወደማይችልበት ሁኔታ ካላሳደግነው ችግር ውስጥ እንደምንወድቅ በምረዳበት ጊዜ የራሴን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብኝ ብዬ ወስኜ ነው እንግዲህ የመጣሁት።

ጥያቄ- ምን ዓይነት አስተዋጽኦ?

ወ/ት ብርቱካን-እስካሁን ያደረግኩት የትግል ሂደት የዴሞክራሲ ስርዓት ከማምጣት ጋር፣ ነጻና ገለልተኛ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማትን ከመገንባት ጋር የተያያዘ ነው ። በፖለቲካ ትግል የተሳተፍኩትም እነዚህ ተቋማት፣ ለምሳሌ እኔ ራሴ ስሰራበት የነበረው ፍርድ ቤት፣ የዜጎችን መብት ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ያለበት ነገር ግን በአብዛኛው አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያደርግ የነበረው የፖሊስ ኃይል፣ የአቃቤ ህግ መስሪያ ቤት፣ የምርጫ አካላትና የመሳሰሉትን ተቋማት በገለልተኝነትና በጠንካራ ሁኔታ ተቋቁመው እንዲታዩ ስለምፈልግ ነው፤ አሁን ይህን እውን ለማድረግ የተሻለ ሁኔታ ነው ያለው። የግድ በፖለቲካ በመቀናቀን መሆን የለበትም የሚል አረዳድ አለኝ፤ ምክንያቱም ሥልጣኑን ይዘው እየመሩ ያሉ ወገኖች ያንን ለማድረግ ፈቃደኝነት ስላሳዩ ማለት ነው። የኔም አሰተዋጽኦ በዚሁ ላይ የሚያተኩር ይሆናል፤ በየትኛው ተቋም ላይ እሳተፋለሁ የሚለውን ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሳውቅ እነግራችኋለሁ።

ጥያቄ-መቼም ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ ነገር እየተባለ እንደሆነ እርሶም ሳይሰሙ አይቀሩም፤ ሰዎች ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው ወይስ በእርግጥም የተሰማ ነገር አለ?

ወ/ት ብርቱካን-ወሬው ከየት እንደመጣ ይሄ ነው ማለት አልችልም፤ በብዙ ሰዎች እንደሚነሳ አውቃለሁ። ከመንግሥትም ጋር በምነጋገርበት ጊዜ ከሙያዬና ከልምዴ አንጻር የተለያዩ የዴሞክራሲ ተቋማትን አይተን ልታግዢ ትችያለሽ? የሚል ጥያቄ ቀርቦልኛል፤ እኔም አስቤያለሁ፤ ግን ጨርሰን ይህን አደርጋለሁ የሚለው ላይ ገና ስላልደረስኩኝ ምንም ማለት አልችልም። ሰዎች ምኞታቸውንም ሊሆን ይችላል የገለጹት፤ በበጎ መልኩ ነው የማየው።

ጥያቄ- ጠቅላይ ሚኒስትር ቢይ አሜሪካ እያሉ ‘በኢትዮጵያ የሴቶች ትግል ውስጥ ደማቅ ቀለም የጻፈች ጀግና ሴትን እንዳመሰግን ፍቀዱልኝ” ሲሉ ምን ተሰማዎት?

ወ/ት ብርቱካን-እኔ ራሴን የተለየ አድናቆት እንደሚቸረው፣ ወይም የተለየ ጥንካሬ እንዳሳየ ሰው አልቆጥርም፤ ሀገሬ ላይ የተሻለ ነገር ማየትን እፈልጋለሁ፤ ሕይወቴን የህዝብ ተጠያቂነት ያለበት ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለማምጣት፣ ለዜጎችም የተሻለ ሕይወትን ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ማሳለፍ እፈልጋለሁ። ግን ሀገራችን የነበረችበት ሁኔታ መጥፎ ሆኖ ያ ጥረቴ በአብዛኛው በውጣ ውረድ ፣ ስቃይን በሚያመጡ እስራትና መንገላታት የታጀበ ነው፤ ውጭ በነበርኩበትም ጊዜ በብዙ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ ስቃይ ሲፈጸም ሁልጊዜ የሚሰማኝ ህመም ነበር፤ እና በእርሳቸው ደረጃ የኔን አስተዋጾ በዚያ መልኩ ሲያቀርቡት ደስ ብሎኛል። ለሀገራችን በአጠቃላይ የሚሰጠው ተስፋ ደግሞ ይበልጥ አስደስቶኛል፤ ብቻ የተደበላለቀ ስሜት ነው፤ ግን የዚያ የስቃይና የእንግልት ዘመን ምዕራፍ መዝጊያ መሆኑን እንዲሰማኝ አድርገዋል።

ጥያቄ-ይህንን ጥያቄ የጠየቅኩበት ምክንያት ያው ያኔም ስለ ጨቋኝነቱ የሚናገሩለትና ወህኒ ያወረዶት የኢሕአዴግ መንግሥት ነበር፤ አሁንም የተመለሱበትን ሀገር የሚመራው ኢሕአዴግ ነው። በሁለቱ መካከል መሰረታዊ የሆነ ለውጥ አለ ብለው ያምናሉ?

ወ/ት ብርቱካን-በውስጥ ያሉ ለውጦች ወደ አደባባይ እየወጡ የሚታይ እውነት ነው? ወይስ ከውጭ የሚደረግ የመቀባባት ሂደት ነው? ለሚለውን ጥያቄያችን በሂደት መልስ እያገኘንለት መጥተናል። ማንም ሊክዳቸው የማይችላቸው ተጨባጭ እርምጃዎች ተወስደዋል፤ የፖለቲካ እስረኞች ተፈተዋል፣ በሚዲያ ላይ የነበረው ተጽዕኖ ተነስቷል፤ ንግግሮችም ቢሆኑ በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም፤ ምክንያቱም ንግግርና ያንን ለማሳካት የሚታየው ቁርጠኝነት ነው ወደተግባር የሚወስዱት፤ ግን ያ ተግባር አሁን የበላይነቱን በተቆጣጠረውና ለውጡን በሚደግፉ በተወሰኑ ቡድኖች ወይም ሰዎች ላይ ብቻ የሚመረኮዝ ከሆነ አሁንም በስጋት ነው የምንኖረው፤ ለዚያ ነው ተቋማዊ መሰረት በጣም አስፈላጊ ነው የምለው።

ጥያቄ- በቀጣዩ ዓመት ጠቅላላ ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፤ ኢትዮጵያውያን በዚህ ምርጫ ከእርስዎ ምን ይጠብቁ?

ወ/ት ብርቱካን-አንድ ነገር በእርግጠኝነት መጠበቅ ይችላሉ ፤ በምርጫው አልወዳደርም። እውነት ለመናገር የፖለቲካ ፉክክርን በጣም ከሚመኙት ሰዎች መካከል አይደለሁም፤ ከፉክክር በላይ መተጋገዝን፣ መተሳሰብን፣ የቡድን ሥራን ነው ግብ ማድረግ የምፈልገው ። መጀመሪያውኑም የገባሁበት መንግሥት ጨቋኝ ስለነበረ፣ የምፈልጋቸውን የህግ የበላይነት፣ የሰብዓዊ መብት መከበርና የዴሞክራሲ አስተዳደር የምንላቸውን ነገሮች ለማምጣት የግድ የፖለቲካ ትግል አስፈላጊ ስለነበረ ነው፤ አሁን ግን የፖለቲካ ውድድር ውስጥ ለመግባት ምንም ፍላጎት የለኝም፤ ህዝቡን ለማገልገል እድል አለ ብዬ አምናለሁኝ፤ ምርጫውን ከዳር ሆኜ ባልታዘብም ተወዳዳሪ ግን አልሆንም።

ጥያቄ- በእስካሁኑ የፖለቲካ ተሳትፎዎ ይህን ባለደርግኩኝ ብለው የሚጸጸቱበት ነገር አለ?

ወ/ት ብርቱካን-በፍጹም የለም ካልኩኝ ሰው አይደለሁኝም ማለት ነው፤ ወደ ኋላ ስትመለከቺው ልታሻሽይው የምትችይው ፣የተሻለ ምርጫ ልትወስጂበት የምትችይው ነገር ሁልጊዜም ይኖራል፤ ግን ባለኝ መረዳት የሞራል መርሆዎቼን ጠብቄ ባለሁበት ጊዜ ትክክለኛ ነው የምለውን ውሳኔ ወስኛለሁ። በዚህ ደግሞ ሁልጊዜም ትልቅ የህሊና ነጻነት ይሰማኛል፤ በሄድኩበትና በመረጥኩት መንገድ አንድም ቀን ጸጸት ተሰምቶኝ አያውቅም ፤ድጋሚም ህይወቴን ብኖረው በዛው መንገድ እኖረዋለሁ።

Filed in: Amharic