>
5:13 pm - Sunday April 18, 2151

ጦር አውርድ እያላችሁ ነጋሪት የምትጎስሙ ወደ ልብ ናችሁ ተመለሱ!!! (ክብረአብ ማናዬ)

ጦር አውርድ እያላችሁ ነጋሪት የምትጎስሙ ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ!!!
ክብረአብ ማናዬ
በቅርብ ጊዜ ወደ ሶሻል ሚዲያው ጎራ ባልኩ ቁጥር  በሀገሬ በተለይም በሰሜን ኢትዮጲያ በአማራና በትግራይ አክቲቪስቶች መሀል እየተጎሰመ ያለው የጦርነት አዋጅ የሚጠራ ነጋሪት ድምፁ ያስፈራል ፡፡ ሁለቱም ጦርነት በጣም ፈልገዋል፡፡ ከጦርነቱ በሗላ ያለውን ነገር ማንም የሚያስበው የለም፡፡ እኔን ግን በእጅጉ አሳሰበኝ፡፡ ባለፈው አስር አመት በአለማችን የተደረጉ ጦርነቶች በቀላሉ የሚቆሙ አልሆኑም፡፡ ቢሊዮን ዶላር የፈሰሰባቸው ፣ የሚሊተሪ ሳይንስን ልቀት ያየንባቸው የሀያላኑ ሀገራት ጦርነቶች ኢራቃውያንን፣ አፍጋናውያንን፣ ሶሪያውያንን እና ብዙ ህዝቦችን ስደተኛና ሀገር አልባ ከማድረግ የዘለለ ጥቅም አልነበራቸውም፡፡
ምዕራባውያኑንም በስደተኛ ከማጥለቅለቅ የተረፈ ነገር ያልነበረቸው አሸናፊው የማይታወቅባቸውን ጦርነቶች ስናይ ከረምን፡፡ በዚህ መሀል ብዙ ሽህ ሀዝቦች አለቁ፣ ሚሊዮኖች ስደተኛ ሆኑ፣ ቢሊዮን ዶላሮች ከሰሩ፣ ብዙ ሀብቶች ወደሙ፣ የጨቅላ ህጻናት የትምህርትና የጨዋታ ወርቃማ ጊዜ እንደዋዛ ባከነ፡፡ አሸናፊ ግን አልነበረም፡፡ ጦርነት በዚህ ዘመን  የሀያላኑንን ኢኮኖሚ የሚፈትን ክፉ ነገር ሆኗል፡፡  ለምንም አይመከርም፡፡ ይህ ነገር ብድር ባደቀቃት፣ ሙስናና የፖለቲካ ቀውስ ባሰቃያት፣ ችግርና ረሀብ በፈተናት፣ ስደት አቅም ያላቸውን ልጆቿን በነጠቃት በሀገሬ እንዲሆን ቀንና ሌሊት እየሰበኩ ያሉ ሰዎችን በየቅፅበቱ ስመለከት የምር አሳሰበኝ፡፡ ትርፍ በሌለው ጦርነት የሚፈናቀሉ፣ የሚሞቱ፣ የሚራቡ ፣የሚሰደዱ ወገኖቼን አስቤ የምርም አሳሰበኝ፡፡ አስቡት እኔ ከአማራ ቤተሰቦች ተወለድኩ ፣ በእናታቸው አማራ በአባታቸው ትግሬ የሆኑ የምወዳቸው የአክስቴ ልጆች አሉ፣ በእናታቸው አማራ በአባታቸው ኦሮሞ የሆኑ የምወዳቸው የሌላ አክስቴ ልጆች አሉ፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ጋር ተለያይተን እንደ ኤርትራውያን ከአመታት በሗል እግዜር ካለ ልንገናኝ ነው? ወገኖቼ ሆይ የምትጠሩት ጦርነት ሀገር ያፈርሳለል፣ ቤተሰብም ይበትናል፣ የደቀቀ ኢኮኖሚን የበለጠ ያደቃል፡፡ የድንበር ጉዳዮችን በብዙ ድርድር፣ በብዙ ውይይት፣ በብዙ ንግግር ፍቱ ሀገር ግን አታፍርሱ፡፡ ሁላችንም የተለያየ ማንነት ያለን ኢትዮጲያውያን ነን፡፡ ተዋልደናል ስንል ለይምሰል አይደለም፡፡ ዘንድሮ ጦርነት  አያልቅም ልብ ግዙ አደብ ግዙ፡፡
እኔ በኢትዮጲያና በኢትዮጲያዊነት አምናለሁ የሚያድነን እሱ ነው….
Filed in: Amharic