>

ሰላሳ የሆነው በምክንያት ነው" (ቴዲ አፍሮ)

”ሰላሳ የሆነው በምክንያት ነው”
~ቴዲ አፍሮ
ሚልንየም አዳራሽ በታሪኩ እንዲህ የሙዚቃ ድግስ ሰምሮለት አያውቅም። የባንዱ ውህደትና ፍቅር የተሞላበት ጉልበት፤ ከቴዲ የማይነጥፍ ብቃት ጋር ተደምሮ ልዩ ምሽት ነበር።
ወትሮ የሙዚቃ ድግስ ላይ ሲታደሙ እምብዛም ታይተው የማይታወቁ ብዙ ሰዎችን አስተውያለሁ።
በእድሜ የገፉ አዛውንቶች፤ አባትና ልጅ፤ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለት የባህል ልብስ የዘነጡ ጎልማሳ እንስቶች፤ ከነጠባቂዎቹ ከማረሚያ ቤት የመጣ ታራሚ፤ የኢትዮጵያ ቡና እና የቅ/ ጉዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች በአንድ ላይ እጅግ ትኩረት የሚስቡ ታዳሚዎች ነበሩ።
ከድምፃዊያን መሐል ተወዳጁ የሂፕሆፕ አቀንቃኝ ልጅ ሚካኤልን አገኘሁት። “ይህንን የመሰለ ልዩ ኮንሰር በአካል ተገኝቼ ዊትነስ በማድረጌ በጣም እድለኛ ነኝ። እኔ ኢንስፓየርድ መሆን እና መማር የምፈልገው ከዚህ ግዙፍ የመድረክ ስራ ነው። በአንድ ምሽት ሁሉም ነገር ስኬታማ ሆኖ ማየት በጣም ያስደስታል። መብራቱ፣ ድምፁ፣ የባንዱ ኤነርጂ፣ የቴዲ ፐርፎርማንስ፣ በእውነት እኔ እንደዚህ የተሳካ ዝግጅት አይቼ አላውቅም።” አለኝ ልጅ ሚካኤል።
ጓደኛዬ ደቻሳ አንጌቻ ሳልሰማ ተዘለልኳትን በሳቅና በጭብጨባ የታጀበውን የቴዲ የመድረክ ላይ አጭር ንግግር  ነገረኝ። ታዳሚው በጋራ “ጃ ያስተሰርያል!” እያለ ቴዲ እንዲዘፍን ይጠይቃል። ጃ ያስተሰርያልን ቀድሞም ለመዝፈን ያቀደ በመሆኑ እና በሙዚቃዎቹ ቅደም ተከተል አደራደር መሰረት የሚያቀርብበት ግዜ ገና ባለመድረሱ በጨዋ እና በቀልድ አዋዝቶ አንድ ቃል ጣል አደረገ “30 የሆነው በምክንያት ነው – ተረጋጉ” ይህ አባባሉ ብዙውን ሰው ማሳቁን እና ማስጨብጨቡን ምስክር ነኝ።
በሚልንየም አዳራሽ ዙሪያ የነበረው የፀጥታ ጥበቃ በእጅጉ የሚያስደስት ነበር። ምንም እንኳን መግቢያ በር አካባቢ ፖሊሶች ሰዉን እስከ መደብደብ የደረሰ ያልተገባ ተግባር የፈፀሙ ቢሆንም አብዛኛው የጥበቃ ቅድመ ዝግጅት የሰመረ ነው ማለት ይቻላል። በርካታ ታዳሚ በህገወጥ ሻጮች ተጭበርብሮ ፎርጂድ ትኬት ይዞ መንገላታቱንም እማኝ ነኝ።
ሚልንየም አዳራሽ የሙቀት ማስተካከያ መሳሪያ አብዝቶ ካልገጠመ ይህን የመሰለ ልዩ ኮንሰርት በተዘጋጀ ቁጥር ከፍተኛ እክል መግጠሙ አይቀርምና ይታሰብበት።
እጅግ ጨዋ ታዳሚ፤ ሰላማዊ ምሽት፤ የፍቅር ጣራ፤ ድንቅ ሙዚቃ የተዋሀዱበት ኮንሰርት ጥቅምት 24 ቀን 2011ዓ.ም ተካሔደ ብለን ለታሪክ መዝግበናል።
እንኳን ደስ አለህ ወንድም ቴዲ አፍሮ
* ጃ ያስተሰርያል
* ኢትዮጵያ
* ጥቁር ሰው
* ሰንበሬ
* አናኛቱ
* ቴዎድሮስ
* ማር እስከ ጧፍ
* ሼመንደፈር
* ግርማዊነትዎ
* ኦላን ይዞ
* ፍዮሪና
* ሔዋን እንደዋዛ
* አቦጊዳ
* ማዘንድ ይደር
* ማራኪዬ
* ይሰስታል አይኔ
* አፍሪካዬ
* ቀላል ይሆናል …
Filed in: Amharic