>

አንድ አፍታ  ከብርቱካን ሚደቅሳ እናት ጋር (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

አንድ – አፍታ

ከብርቱካን ሚደቅሳ እናት ጋር
ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን
እነሆ በብርቱ መገፋት ውስጥ ሆና ታላቅነቷን የሰበከችላት፣ ፅኑ ተስፋዋን የጣለችባት ኢትዮጵያ ወደ ምድሯ ጠራቻች!!!
 
 እንደ መግቢያ
ዛሬ ዕለተ ሰንበት ጠዋት ወደ ወደ 5 ሰዓት ተኩል ገደማ ወደቤታቸው አመራሁ፡፡ እህቷ ን ኢየሩስ በረንዳ ላይ አገኘኋት፡፡
“ማዘር አሉ?”
“አለች”
ገባሁ፡፡ ሳሎን ውስጥ አንደኛው ሶፋ ላይ ቁጭ ብለው ከሰል ምድጃ ላይ የተጣደውን ድስት ያማስላሉ፡፡
“ማዘር”
“ውይ፤ ከየት ተገኘህ ወሰኑ”
ወሰኑ የሚሉኝ ሁለት ሰዎች ናቸው፤ የአውራምባ ጋዜጣ የስራ ባልደረባዬ ግዛው ለገሰ እና የብርቱካን እናት፡፡
“ልጃችን ልትመጣ ነው ሲባል ካለሁበት ብቅ አልኩ”
“ መቼም ይኼ ነገራችሁ (ፌስቡክ ማለታቸው ነው) የማያወራው የለም” አሉኝ እየሳሙኝ፡፡
“ጤንነትዎ እንዴት ነው?”
“አዬ ጤንነት፤ ይኼ እግሬ ተይዞልህ …. ከቤት አልወጣም እኮ” አሉኝ  እንድቀመጥ እየጋበዙኝ፡፡ ተቀመጥኩ፡፡  እናም የባጥ የቆጡን ማውጋት ጀመርን፡፡ ወጋችን እንዴት እንዴት ሆኖ የኋሊት እንደሸመጠጠ አላውቅም  መኖሪያ ቤት የሰሩበትን ሁኔታ ተረኩልኝ፡-
—- ➊ —
“…. ይኸውልህ እዚህ ማዞሪያ (12 ቁጥር አውቶብስ) አሁን ባንክ ቤት የተሰራበት ቦታ አቶ አበበ የሚባሉ ሰው ነበሩ፡፡ መሬት ታልሰጡኝ  ብዬ አስቸገርኳቸው፡፡ ያኔ እህ ሰው አልነበረበትም ስጧት አሉ፡፡ 120 ብር ከፍዬ መሬቱን ገዛሁና …. የ20 ብር እንጨት፣ ለአናጢ 15 ብር፣ 12 ሁለት ቁጥር 30 ቆርቆሮ በ103 ብር ገዛሁና ….”
“በ3 ብር ከሆነማ 30 ቆርቆሮ 90 ብር ነው የሚሆነው” አለች ከፊት ለፊታችን ተቀምጣ ቡና የምትቆላው ኢየሩስ፡፡
“ … የለም” አሉ ወ/ሮ አልማዝ “ሳንቲም አለው፤ ብቻ በ30 ቆርቆሮ ቤት ሰራሁ”
“12 ቁጥር ሚስማር ማለትዎ ነው?”
“ ቆርቆሮ ነበር 12 የሚባል፡፡ በርሜል በለው ውፍረቱ፡፡  ብርቱካን ይኼን ቤት በአዲስ መልክ ስታሰራው ለአጥርነት አገልግሎ ነበር፡፡ እና ያ የፈረሰው ቤት እንዲህ ነበር የተሰራው፤ ያውም እየተበላ እየተጠጣ፤ አይ ጊዜ….”
ከዚህኛው ወሬ ወደሚቀጥለው እንዴት እንደተሸጋገርን እንጃ፡፡
—- ➋ —-
“….. ከዚያ ደሞ ብርቱካንን እርጉዝ ሆኜ አባቷ …. መቼም ደግ ሰው አይበረከትም ደመወዝ ተጨመረላቸው፡፡ ስንት መሰለህ ደመወዛቸው? 30 ብር ብቻ፡፡ እናልህ ….. የባለፈው ደመወዛቸው ጭማሪ ተጠራቅሞ 140 ብር ደረሳቸው፡፡ እንዳለ አምጥተው ለኔ ሰጡኝ፡፡ … ያኔ ገበያ ሄደህ በሚዛን የምትገዛው ነገር የለም፤ ተይህ ወዲያ ተብለህ ማፈስ ነው፡፡ እንደዛ እህል ምናምን ተገዘና ለእሷ ክርስትና ድ…ል ያለ ድግስ ተደገሰ፤ መንደርተኛው ሁሉ ‹ሌላ ልጅ ስለሌላቸው እኮ ነው እንዲህ የተደገሰው እያለ ተበላ፡ በ30 ብር የጡረታ ጭማሪ……”
 “እኔ ምለው እማማ ብርቱካን በሕፃንነቷ እድለኛ ነበረቻ! ኃይለኝነቷስ በማን ነው የወጣችው?” አልኩና አቋረጥኳቸው፡፡
“ሚሚሻ፤ ኃይለኛ አይደለችም፤ ደግ ናት የዋህ ናት”
“በእሷ!….. በእሷ ወጥቷ ነው!” አለች ኢየሩስ ጣልቃ ገብታ፡፡
በዚህ ጊዜ ከወደ ጥግ የተከፈተው ቴሌቪዥን ዜና ያሰማ ጀመረ፡፡ ዶ/ር አብይ የፕሬዝዳንቱ ሽኝት ላይ ንግግር እያደረገ ነው፡፡ ስለ አዲሷ ፕሬዝዳንት “እናትነት” እየተናገረ ነው፡፡ ለአፍታ ከልብ ካዳመጡት በኋላ፡-
“ይኸውልህ ያ ሁሉ የጭንቅ ዘመን አልፎ እንዲህ ያለ እናት የሆነ መሪ መጣ፡፡ እኔማ ከመጣ ጀምሮ ሁሌ እየፀለይኩለት ነው፡፡…” አሉኝ፡፡
—- ➌ —-
አንዳንድ አጋጣሚዎች ይገርሙኛል፡፡ ብርቱካን ለሁለተኛ ጊዜ ቃሊቲ ተወርውራ “ልትፈታ ነው” የሚል ወሬ የተሰማ ሰሞን እንዲሁ ወደ እነብርቱካን ቤት መጥቼ ነበር፡፡ የ2003 አዲስ አመት ዋዜማ ነበር ያኔ፡፡ “የአመት በዓልን ዋዜማ በእነ ብርቱካን ቤት ከልጇ ሀሌይ ጋር” የሚል ዘገባ ሰርቼ ነበር በወቅቱ፡፡ ያኔ እንዲሁ ቴሌቪዥን ተከፍቶ  እግር ኳስ ጨዋታ እየተላለፈ ነበር፡፡ በመሃል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጎል ገባበት፡፡ “እሰይ እንኳን ገባበት አለች” ሃሌይ፡፡ አባባሏ የልጅነት ነገር ቢሆንም፤ ውስጣዊ መልዕክቱ በእናቷ መታሰር የመከፋት ዓይነት ቃና ነበረው፡፡
ዛሬም ቴሌቪዥን ተከፍቷል፡፡ ዶ/ር አቢይ ስለፕሬዝዳንቷ እናትነት እየተናገረ ነው፡፡
“… ያ ሁሉ የጭንቅ ዘመን አልፎ እንዲህ ያለ ዘመን መጣ” አሉ አሁንም ዜናውን ሰምተው ሲጨርሱ፡፡
—- ➍ —-
“ …. ያኔ ብርቱካንን መጠየቅ እንኳ ተከልክለን ነበር፤ እሷ እንደገና ይቅርታ ጠይቃ ነው ገብታ እንድትጠይቅ የተፈቀደላት” አሉኝ ወደ ኢየሩስ እየጠቆሙኝ፡፡
“… በምን ምክንያት ነበር የተከለከልሽው?”
“በቴዲ አፍሮ ምክንያት፡፡ ብርቱዬ በሕልሜ ቴዲ አፍሮ ሲፈታ አየሁ ብላ ነገረችኝ፡፡ ይህንን ሰሙና ማን ስለእሱ አውሩ አላችሁ፤ እንደውም ካሁን በኋላ አትገቢም አሉኝ፡፡ በኋላ በደብዳቤ ይቅርታ ካልጠየቅሽ አሉኝ፡፡ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ እሷ ስንቅ ይዛ መመላለስ አትችልምና የግድ ይቅርታ ብዬ ደብዳቤ አስገብቼ ነው ጥየቃ እንኳ የተፈቀደልኝ” አለች፡፡
—- ➎ —-
እንዲህ እንዲህ እያልን ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል አወጋንና ተሰነባበትን፡፡  አሁን፤ ይህንን የወ/ሮ አልማዝን ወግ እየከተብኩ ብርቱካን ሚደቅሳ በሰኔ ወር 2003 መጨረሻ በዋሽንግተን ዲሲ ፌስቲቫል ላይ ተገኝታ ባደረገችው ንግግር “እውን ኢትዮጵያ የምትወደስ አገር ናት ወይ?” ብላ ጠይቃ የሰጠችው ምላሽ ትዝ አለኝ፡፡ ፡-
“…. ኢትዮጵያ የፍትህ አገር አይደለችም፤ ዛሬም ዜጎቿ በድህነት የሚኖረባት፣ በሃፍረት የሚያቀረቅሩባት፡ የሚሸማቀቁባት፤ ዜጎቿ የሚሰደዱባት ሃገር ነች፡፡ ስለዚህ ‹እናወድሳት ወይ?› ብለን ብንጠይቅ፣ ‹አዎ ማወደስማ አለብን‹ የሚል ነው መልሴ፡፡ ….. ዛሬም ህልም አልማለሁ፤ አጠንክሬ አልማለሁ፡፡ በእናንተ አምናለሁ፡፡ በራሴ አምናለሁ፡፡ በልጄ አምናለሁ፡፡ በሚመጡት የልጅ ልጆች ሁሉ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ታላቅ ሃገር ናት እላለሁ፡፡ ልትወደስ ይገባታል እላለሁ፡፡ እናንተም በዚህ ሃሳብ እንደምትሰማሙ አምናለሁ፤ መልዕክቴ ይኸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ልትወደስ የሚገባት ታላቅ ሃገር ነች፤ ታላቅነቷን ለማየት ግን ሁሌም ተስፋ ይኑረን፡፡ ሁሌም በአንድነት እንቁም፡፡ አንድነታችን ሁላችንንም የሚያቅፍ፤ ሁላችንንም የሚያሰባስብና የኢትዮጵያን የጋራ መኖሪያነት በሚያውቁት ይሁን፡፡….” ነበር ያለችው በዚያ ንግግሯ፡፡
— ➏ —
.
እነሆ በብርቱ መገፋት ውስጥ ሆና ታላቅነቷን የሰበከችላት፣ ፅኑ ተስፋዋን የጣለችባት ኢትዮጵያ ወደ ምድሯ ጠራቻች፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አማካይነት፡፡ እና እየመጣች ነው፡- ሐሙስ ጥቅምት 29  ቀን ጠዋት ቦሌ አየር ማረፊያ ትደርሳለች፡፡
.
– ጀግኒት!!
Filed in: Amharic