>

የአስመሳዮች ፖለቲካ!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

የአስመሳዮች ፖለቲካ!!!
ጌታቸው ሽፈራው
~የሚያስመስል ሰው የሚመርጠው ተወዳጅ አጀንዳን ነው። አስመሳዮች አቆሸሹት እንጅ የዜግነት ፖለቲካ ምርጥ ነበር፣ የአንድነት ፖለቲካ ምርጥ ነበር። የዜግነት ፖለቲካ እያሉ ግን ለዜጎች ሲቆሙ አታዩዋቸውም። በዚህ ረገድ አዲስ አበባንም በተበላሸ የፖለቲካ ባህል እያመሱት ነው። ባለፈው በነጋታው ወደቤታቸው የሚመለሱት ቄሮዎች መስቀል አደባባይ ሲያደሩ “ውሃ፣ ዳቦ፣ ቶሎ በሉ” ሲባል “እሰይ፣ ተባረኩ” ብለን ነበር። ደግሞም ትክክል ነበር። ዛሬ የወልቃይት ጠገዴ ወጣቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው አዲስ አበባ ይገኛሉ።  ያ ሁሉ ወከባ የለም። ለዜግነት ፖለቲካ እጨነቃለሁ የሚለው አብዛኛው ፖለቲከኛ ብቅ ብሎ እንኳ አያያቸውም። ምክንያቱም “በአማራነታችን ተጠቃን” ብለው ነው የሚናገሩት። ይህን መራራ ሀቅ ደግሞ መስማት አይፈልጉም። እንዲያውም ይጠሉታል! የዜግነት ፖለቲካ፣ የአንድነት ፖለቲካቸው ቁማር መሆኑ የሚገለጠው የአማራቅ ጉዳይ ሲነሳ ነው። ጥላቻቸው በግልፅ አስመሳይነታቸውን ይናገርባቸዋል!
~ለዜግነት ፖለቲካ ቆሜያለሁ እየተባለ የትግራይ መንግስት ዜጎችን ሲገድል ፀጥ ነው፣ ሲያስር የረባ ድምፅ አያሰሙም፣ ሲያፈናቅል ዝም ነው።  የትግራይ መንግስት ይህን ሁሉ ስቃይ ሲያደርስ ዝምታን የመረጠው ሁሉ እነ ደብረፅዮን ለቁማር መልካም የሚመስል ነገር ሲናገሩ “ተደመሩ” ብሎ ወደሳ የጀመረው ጥቂት አልነበረም። በድርጅት ደረጃ ሳይቀር “ህወሓት ውስጥ የለውጥ ኃይል አለ” ተብሎ ተነግሯል። አጥፊው ህወሓት ሕዝብን እንደ ሕዝብ ፈርጆ ሲያጠቃ ግን ዝምታ ነው።
~ የትግራይ መንግስት በሺህ የሚቆጠር ጦርን በወልቃይና ራያ ሲያሰፍር ዝምታን የመረጠ አስመሳይ “አንድነት” ነኝ ባይ ትናንት የአማራ ወጣቶች ነፍጥ አንግበው ጥየቃ ሄዱ  ብሎ እየየ ይላል።  ጭራሽ የእስር ትዕዛዝ ይውጣ ብሎ የሚወተውትም እንዳለ ታይቷል።  ይህን ጊዜ ነውኮ ጥላቻቸው የሚያጋልጣቸው። የአማራ ሕዝብ መሳርያ ባህሉ ነው። ለጥየቃም ሄደ ለሌላ ጉዳይ መሳርያ ይይዛል።  ወጣቶቹ ያቀኑት ደግሞ አፈና ወደበረታበት ራያ ነው። መሳርያቸው ሕጋዊ ነው።  በእርግጥ ይህም ይተቻል ከተባለ አማራው ሲጠቃ ሲጮህ የነበረ፣ ህወሓት በራያና ወልቃይት የሚፈፅመውን በግልፅ ሲቃወም የቆየ ቢተች ተገቢ ነው።  ትህነግ/ህወሓት ሲገድል ዝም ብሎ፣ ሌላ አካል ሲቸገር “ቶሎ በሉ” እያለ ወልቃይትና ጠገዴ ተፈናቃይ የማይታየው የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ ነኝ ባይ፣ የአንድነት ፖለቲካ አራማጅ ነኝ ባይ ውሸቱን ነው። የአንድነት ፖለቲካውን፣ የዜግነት ፖለቲካው ማስመሰያ እንጅ መርሁ አይደለም! ልንደርስበት የሚገባውን፣ ሀቀኛውን የዜግነት ፖለቲካ፣ የአንድነት ፖለቲካ እያቆሸሸው ያለ ይህ አስመሳይ ኃይል ነው።
የወልቃይት ጠገዴ ተፈናቃዮች የዜግነት ፖለቲካን አቀነቅናለሁ የሚለው ሁሉ የከተመበት  አዲስ አበባ ላይ ሆነው እገዛ እየመጣላቸው ያለው ከደብረብርሃ ነው፣ ከማያስመስሉ የሀይማኖት አባቶችና ግለሰቦች ነው። ሌላ የሚያባብለው አካል  ቢሆን ግን ሸብ ረብ ሲል ባየነው ነበር። እርዳታው መጥፎ ሆኖ አይደለም። ትኩረቱ ክፉ ሆኖ አይደለም። ግን ሁሉንም በአንድ አይን አያለሁ እያለ  ለአንዱ ፊቱን ያዞራል። እንዲያውም በጥላቻ!
Filed in: Amharic