>
5:13 pm - Tuesday April 19, 1008

በሠይፍ ብቻ ሕዝብን መግዛት እንደማይቻለው ሁሉ በሕግ ብቻ ሀገር መምራትም አይቻልም!!! (ፕ/ር መሥፍን ወ/ማርያም)

በሠይፍ ብቻ ሕዝብን መግዛት እንደማይቻለው ሁሉ በሕግ ብቻ ሀገር መምራትም አይቻልም!!!ፕ/ር መሥፍን ወ/ማርያም
ሳምሶን ጌታቸው
ፕ/ር መሥፍን በሀገራችን የምሁርነት፣ የትልቅ ሰውነት፣ የአንጋፋነት ውኃ ልክ ናቸው። ማስመሰል የለ፣ ልወደድ ባይነት የለ፣ ሕዝብ ያጨብጭብልኝ የለ፣ ዕውነት ዕውነቷን ቁጭ ነው። ርዕሳቸውና አላማቸው ሁሉ ሀገራቸውና ሕዝቧ ብቻ ናቸው። በእሳቸው አንደበት የሚደነቅም ሆነ የሚነቀፍ ሰው ለሀገራችን ባበረከተው በጎ ተግባር ወይም በሠራው ስህተት ብቻ ነው። ሌላ ወሬ የለም። አለቀ።
ፕ/ሮ መሥፍን ወልደማርያም ለሸገር ሬዲዮ በሰጡት አስተያየት ሕግ ያለ “ሠይፍ”፣ ሠይፍም እንዲሁ ያለ ሕግ ሊሰራ እንደማይችል ለማስታወስ ተናግረዋል። አሁን በሀገራችን ያለው ሁኔታ ሕግ ብቻውን ያለ ሠይፍ እንደሚገኝ ተናገረው፣ ሁለቱም ተመጣጥነው የማይገኙበት ሀገር፣ ሀገር ሆኖ መቀጠል እንደማይቻለው መክረዋል። (ሰሚ ከተገኘ) በታሪኮቻችን በተጨባጭ እንዳየነው በሠይፍ ብቻ ሕዝብን መግዛት እንደማይቻለው ሁሉ በሕግ ብቻም ሀገር መምራት እንደማይቻል አስታውሰዋል።
እውነት ነው። በየአካባቢው ሁሉም የጎበዝ አለቃ እየሆነ፣ በፍቅር ስብከት ብቻ ሀገርን መምራት እንደማይቻል መታወቅ አለበት። ይህ ሲባል ደግሞ ነገሮችን ሁሉ አጣመው የሚረዱ ሰዎች ይኸው ዴሞክራሲ የሚያንበሸብሽ መንግሥት ሲመጣ፤ ጉልበትህን አሳይ እያሉ የሚወተውቱ ፀረ ዴሞክረሲ ሰዎች አሉ ማለታቸው አይቀርም። ሁሉንም ማስረዳት ስለማይቻል ጠማሞች የራሳቸው ጉዳይ ነው። ዋናው መንግሥት ሠይፉንም ሆነ ሕጉን አመጣጥኖ የመጠቀም መብቱን እንዲጠቀምበት መወትወት ነው። የትኛውም ሠላማዊና የበለፀገ ሀገር ሕግ በሕግነቱም ሆነ በሠይፍ የተከበረና የተፈራ እንደሆነ የታወቀ ነው።
ሌላው ስለ ጠ/ሚ ዐብይ እና አቶ ለማ መገርሳም ሲናገሩ ዘርን እና ጎሳን በተጠየፈና ሀገርን ባስቀደመ የተዋጣለት ዲስኩሮቻቸው እንደተደሰቱባቸው ነገር ግን በተግባር እየታየ የሚገኘው አካኼዳቸው ተመልሶ ወደነበረበት የጎሣ ቅኝት ፖለቲካ እየተመለሰ ለመሆኑ ከሁኔታዎች፣ ከሹመት አመዳደቦች መመልከት እንደሚቻል ተናግረዋል። ፕ/ሩ ለጠ/ሚ ዐብይ አስተዳደር የነበራቸው ቀዳሚው ላቅ ያለ ድጋፍ አሁንም አለ ወይ ተብለው ተጠይቀው፣ መሪዎቹ ቃላቸውን እስካከበሩ ድረስ ብቻ ድጋፋቸው እንደሚቀጥል ነገር ግን እጅግ ተስፋ የተጣለበትን ለውጥ በገዛ ራሳቸዎ እየቀለበሱት እንደሚገኙ ቁርጥ ያለውን ተናግረዋል። ዕድሜና ጤና ይስጥልን።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስለ አገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታው ምን ይላሉ???
ሸገር ኤፍ ኤም 102.1
ኢትዮጵያ የአስተዳደር ሥርዓት አፈፃፀሟን ለማስተካከል ለውጥ ከጀመረች ሰባት ወራት አለፉ፡፡ በእነዚህ ወራት የሃገሪቱን ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ እድገት የሚያጎለብቱ ብዙ ተስፋ ሰጪ፣ አነቃቂና ፈጣን የሚባሉ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡
በሌላ በኩል የርስ በርስ ግጭቶች የህዝቡን አኗኗር የማመሳቀላቸው ነገር የቀን ተቀን ወሬ ሆኗል፡፡ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች አንዱ በሌላው ላይ እየተነሳ የሰው ሕይወት ያጠፋል፣ ንብረት ይወድማል፣ ነዋሪዎች ይፈናቀላሉ፡፡
ሕግ፤ በጉልበተኞች እጅ ሆኖ የፈለገውን ርምጃ ሲወሰድ መንግስት ለውጡን የህዝብን ሰላም ከመጠበቅና ሕግና ሥርዓት ከማስያዝ ጋር ማዋሃድ አቅቶታል እየተባለ ቅሬታ ይሰማበታል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ምሁራን ምን ይላሉ ? ለዛሬው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን አስተያየት ይዘናል፡፡ እንዲያዳምጡ ጋብዘናል…
Filed in: Amharic