>

የወልቃይት ነገር. . .  (አቻምየለህ ታምሩ)

የወልቃይት ነገር. . . 
አቻምየለህ ታምሩ
የትግራይ ቴሌቭዥን የውሸት ትርክት በመፍጠር  «ወልቃይት የትግራይ  አካል እንደነበረች» የሚናገሩ ነውረኛ  ካድሬዎችንና  ከወያኔ የድንጋይ  መፈልፈያ ፋብሪካቸው የተመረቱ   የእውቀት ጾመኛ  ስመ ዶክተርና ፕሮፌሰሮችን  እያቀረበ እልቆ ቢስ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛና  የፈጠራ ትርክታቸውን  እውነት ሲያሳክል፤ ንጉሡ ጥላሁን በሚባለው ሰውዬ የሚዘወረው «የአማራ ቴሌቭዥን» የሚባለው ተቋም ግን  ዐቢይ አሕመድ በኦሮምኛ የማይደግመውን የአማርኛ ዲስኩር  ሕዝቡን  እስኪሰለች በመጋት ተጠምዶ ላይ የአማራ ጉዳይ በሆነው በወልቃይት ታሪክ  ዙሪያ አንድም ሰው አቅርቦ  ሕወሓት በየሜዲያው  እያሰራጨው ባለው የውሸት ታሪክ ዙሪያ ምሁራዊ አስተያየት እንዲሰጥ ሊያደርግ አልቻለም።
እኔ እንኳ በአቅሜ ከሁለት ዓመት በፊት ከ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ የጎበኙ  የውጭ አገር አሳሾች የጻፏቸውን ማስታወሻዎችን፣ ከዘመነ መሳፍንት በፊት ጀመሮ  ትግራይን  ያስተዳደሩ ገዢዎች የጻፏቸውን የግዛት  ሰነዶች፣ የካርታ ማስረጃዎችና ልዩ ልዩ  ዶሴዎችን በመሰብሰብ «Forceful Annexation, Violation of Human Rights and Silent genocide: A Quest for Identity and Geographic Restoration of Wolkait-Tegede, Gondar, Amhara, Ethiopia» በሚል የጻፍሁትን  ባለ 52 ገጽ ጽሑፍ አቅርቤ  ነበር። አንድም ቀን ግን  ይህንን  ወልቃይትን አስመልክቶ ብዙ የተለፋበትና የተከማቸው የታሪክ ማስረጃን  የብአዴኑን ልሳን «የአማራ ቴሌቭዥን» አይን  ስቦ  ወልቃይትን በሚመለከት ፕሮግራም እንዲሰራበትና የትግራይ ቴሌቭዥን የሚያሰራጨውን ነጭ ውሸቶች  ለመሞገት ተጠቅሞበት አያውቅም።
ሌላው ቢቀር   የቀድሞው የትግራዩ ገዢ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም በአሜሪካ ድምጽ  የአማርኛው ክልፍ ቀርበው ስለ ወልቃይት የተናገሩትን  እውነት እንኳ በንጉሡ ጥላሁን  የሚዘወረውን «የአማራ ቴሌቪዥን»  ቀልብ ስቦት አያውቅም። ንጉሡ ጥላሁን የጌቶቹን ትዕዛዝ እየተቀበለ  በበላይነት የሚዘውረው  ይህ «የአማራ ቴሌቭዥን»  ስለ ወልቃይት ፕሮግራም ሰራ ከተባለ «በሕገ መንግሥቱ መሠረት  የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ሊመለስ ይገባል» የሚል ሰልፍ ተካሄደ የሚልና  የሕዝብን ድምጽ አዛብቶ የሚቀርብ ብቻ ነው። ልብ በሉ! የአማራ ሕዝብ «ሕገ መንግሥቱ እኔ አይወክለኝም፤ ይቀየር»  በማለት ከጫፍ እስከ ጫፍ  ሰልፍ እያካሄደ፤  የብአዴኑ ልሳን «የአማራ ቴሌቭዥን»  ግን የወልቃይት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ  መሠረት ይመለስ  ተባለ በማለት  ወያኔ ከአማራ አንጻር ለጻፈው ሕገ አራዊት  በአማራ ስም እውቅና  የሚሰጥ  ዜና ይሰራል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተብዮው  ወያኔዋ አፈጉባኤ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ   ባግባቡ  ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አልቀረበም ስትል በተደጋጋሚ በአገዛዙ ልሳን እየቀረበች ተናግራለን። የወልቃይት የማንነት ጥያቄ  ግን  ሕግ በተባለው መሠረት  እንኳ መጀመሪያ  ትግራይ ክልል፤ ትግራይ ክልል  የይስሙላ እንኳ መልስ አልሰጥም ሲል ደግሞ  የሰበሰቡትን  የሀምሳ ሺህ ሰዎች ፊርማ የተያያዘበት ሰነድ መርጀው  ለፌዴሬሽን ምክር ቤት  አስገብተው ነበር።  የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ተብዮዋ   የወልቃይት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አልቀረበም እያለች በተደጋጋሚ ስትዋሽ የአማራ ቴሌቭዥን የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮምቴ አባላትን አቅርቦ በሴትዮዋ ውሸት ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ማድረግ ይችል ነበር። ሆኖም ግን ንጉሡ ጥላሁን የሚባለው የበረከት ሰምዖን የመንፈስ ልጅ  የሚመራው የአማራ ቴሌቭዥን የተፈጠረው ለአማራ ድምጽ ለመሆን  ስላልሆነ  የወልቃይትን የአማራ ማንነት ጥያቄ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስገቡትን እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱና አታላይ ዛፌ እንኳ  አቅርቦ ሊጠይቅ አይቻለም።
ዛሬ ደግሞ ወያኔዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተብዮው  አፈጉባዔ  የሕዝቡን ፍላጎት ለመጠየቅ  ወደ ወልቃይት «ገለልተኛ  ልዑክ» ሊላክ መሆኑን በዜና ነግራናለች። ይታያችሁ! ወያኔ በወረራ የያዘውን የወልቃይትን ጉዳይ  የሚመረምር  ገለልተኛ ልዑክ  ሕወሓቷ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ  ስታቋቁም! ይህ የወያኔ ቀልድ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በ1983 ዓ.ም. ስቴት ዲፓርትመት ቀርበው በሰጡት ምስክርነት ላይ ኸርማን ኮህን ባዘጋጀው የለንደኑ የሕወሓትና የሻዕብያ ጉባኤ   በኢትዮጵያ ዙሪያ ሁለቱ የኢትዮጵያ ጠላቶች ስለኢትዮጵያ  ሊያደርጉ የሚችሉትን  ምክክር ያቀረቡበትን ምጸት ያስታውሰኛል። እንዲህ ነበር ያሉት. . . “Imagine sir! Imagine Mr. Chairman and member of the comittee! the PLO’s  Yasser Arafat sitting together with to decide on the fate of the State of Isrel without Israle’s participation”  የወያኔዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም  የምታቋቁመው «ገለልተኛ ልዑክ»  ወደ ወልቃይት ተልኮ ወያኔ ነባሩን አማራ እያፈናቀለ፣ እየገደለና እያሳደደ ከመሀል ትግራይ አምጥቶ ያሰፈራቸውን  ወራሪዎችና  ከሕወሓት ጦት ቀንሶ ወልቃይት ያሰፈራቸውን የትግራይ የገበሬ ወታደሮች በመጠየቅ ወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ የለውም የሚል ድራማ ይተውናል። ይህን ሁሉ ቀልድ እነዚህ ነውረኞች በአማራ ሕዝብ ላይ እንዲጫወቱ የሚፈቅደው  መቼም የማይድነው ነውረኛው ብአዴን ነው።
ሌላው ቢቀር ፋሽስት ወያኔዎች በዐፄ ዮሐንስ ዘመን ወልቃይት የትግራይ ነበር እያሉ የሚሰሩትን ነጭ ውሸት የልጅ ልጃቸው ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የተናገሩትን በማቅረብ ወያኔ የጦርነት ነጋሪት እየደለቀ ያለው በፈጠራ ታሪክ እንደሆነ የአማራ ቴሌቭዥን ሚጥጤ ፕሮግራም መሥራት ይችል ነበር።  ዶሴ ከፈለገ ደግሞ  የትግራይ ድንበር ከየት እስከ የት እንደነበር ግን ዐፄ ዮሐንስ ራሳቸው ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስን ገድለው ሥልጣን በያዙ ባመታቸው «የአማራውን አገር ወልቃይትን፣ ጠገዴን፣ . . . ጎጃምን አስገበርሁት» ብለው ለፈረንሳይ መንግሥት የጻፉት ደብዳቤ፤ የአድዋው ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ገብረ ሥላሴ ባርያ ጋብር ጥሊያን እርዳታ እንዲሰጣቸው በጠየቁበት ተማጽኖ «ኢጣሊያ አይዞህ ያለኝ እንደሆነ ድፍን ትግሬ ከተከዜ እስከ አሸንጌ ያለው ሁሉ መኳንንት እንዲያግዘኝ የታወቀ ነው» ብለው የጻፉት ደብዳቤና እንዲሁም ሌሎች እልቆ ቢስ ዶሴዎች በእጃችን አለለት።
ከታች የታተመው ካርታ  በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት  የነበረውን  የሰሜን ኢትዮጵያን ይዞታ የሚያሳይ ነው። የካርታው ማስረጃ  በግልጽ እንደሚታየው በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ወልቃይት የአማራ ነበር። ዶሴው  የተገኝው ካርታውን ከጥሊያኖች ማህደር አግኝቶ  «Ras Alula and the Scramble for Africa a Political Biography: Ethiopia and Eritrea, 1875-1897» በሚል  የPhD ጥናት ውስጥ  ካካተተው ከአፍቃሬ ትግራዩ ከPr. Haggai Erlich ዴዜርቴሽን ነው።
Filed in: Amharic