>
5:13 pm - Thursday April 19, 0277

ለራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል!!! (ኢንጅነር ግደይ ዘርዓፅዮን) 

ለራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል!!! ኢንጅነር ግደይ ዘርዓፅዮን
በማህሌት አብዱል
 መንግስት የራያ ህዝብ እያቀረበ ያለውን የማንነት ጥያቄ  ህገመንግስቱን ማዕከል በማድረግ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ ጠየቀ፡፡
  የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ኢንጅነር ግደይ ዘርዓፅዮን ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በትግራይና  በአማራ ክልል ውስጥ  ያሉ አንዳንድ የፖለቲካ አመራሮች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በሚነዙት የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ምክንያት የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ አጥቷል፡፡ በዚህም የህዝቡ ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ በመሆኑ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል፡፡
  በህዝቡ የተነሳውን ጥያቄ ሁለቱ ክልሎች ተመካክረው ሊፈቱት ይገባ የነበረ ቢሆንም  ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ባለመስጠታቸው ምክንያት አንዱ ክልል በሌላው ላይ መንገድ እስከመዝጋት የሚደርስ ተግባር የሚፈፀምበት ሁኔታ መኖሩን ምክትልሊቀመንበሩ  አመልክተዋል፡፡
   «ፓርቲያችን በሁለቱም ክልሎች በየጎዳናው የሚደረገው ዛቻና ፉከራ  ለማንም ይጠቅማል ብሎ አያምንም» ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ የራያ ህዝብ ጥያቄ  በህገመንግስቱ መሰረት  ወደ ፈዴሬሽን ምክር ቤት መጥቶ በህግ አግባብ ውሳኔ መሰጠት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
   «እኛ አሁን የምንጠይቀውና ጫና የምናደርገው  የትግራይ ክልል መንግስትን ነው» ያሉት ምክትል ሊቀ መንበሩ ጉዳዩ በሌላ አካል ባይቀርብም እንኳ የክልሉ መንግስት  ራሱ ለፌዴራል መንግስት ጥያቄ በማቅረብ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ የሚጠበቅበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
  ምክትል ሊቀ መንበሩ የሁለቱም ክልል አመራሮች በህዝቦች መካከል ቅራኔ የሚፈጥሩ ትንኮሳዎችን በመከላከል የአገር ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
Filed in: Amharic