>

መፍትሄ አልባው የሊቁ መሪጌታ ጉዳይና የጠ/ሚር ዐቢይ ምላሽ?!?   (ዘመድኩን በቀለ)

መፍትሄ አልባው የሊቁ መሪጌታ ጉዳይና የጠ/ሚር ዐቢይ ምላሽ?!?  
ዘመድኩን በቀለ
 ምን አለበት የነገሩን ፍጻሜ እንዳያውቁ ተደርገው ለ25 ዓመታት ዕርማቸውን ሳያወጡ ለተቀመጡ ቤተሰቦች ቢታዘንላቸው። ወይ ፍቷቸው፣ ወይ ደግሞ ዕርማቸውን ያወጡ ዘንድ አርዷቸው።
ሐምሌ 12/1986 ዓም ከሚኖሩበት ጎንደር ከተማ በህውሓት ታጋዮች ታፍነው ያለፉትን 25 ዓመታት ያለምንም ፍርድ በኢሰብአዊ ሁኔታ በግፍ ታስረው ስለሚገኙት ስለ አቋቋሙ መምሕር ስለ ሊቁ እንደሥራቸው አግማሴ ጉዳይ በትናንትናው ዕለት ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ከመላዋ አውሮጳ ከተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያንና ከኤርትራውያንና ጋር በነበራቸው የምክክር መድረክ ላይ በአንዲት ጀግና እህታችን አማካኝነት ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።
ለጠሚዶኮ ጥያቄውን ያቀረበችው ደግሞ በ1999 ዓም በፍቅረኛዋ ነኝ ባይ ግለሰብ አማካኝነት በሚያምረው ፊቷ ላይ አሲድ በመድፋት ለከፍተኛ ስቃይ ተዳርጋ በሼህ አላሙዲን እርዳታ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሀገረ ፈረንሳይ ያቀናችው ወ/ሮ ካሚላት መህዲ ነበረች። ከሚላት ጠንካራ ኢትዮጵያዊት ሴት ናት። ያን ሁሉ አሰቃቂ የመከራ ጊዜ አሳልፋ ትዳር ይዛ፣ ወልዳ ልጅም ያፈራች ዕድለኛም ናት።
ከሚላት ጥያቄዋን ስታቀርብ ጥያቄውን እንድታቀርብላቸው ወክለው የላኳት በፈረንሳይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም ገልጻለች። እንደአጋጣሚ ሆኖ የሊቁ እንደሥራቸው የአብራካቸው ክፋይ የሆነች ሴት ልጃቸውም መኖሪያዋ በዚያው በሀገረ ፈረንሳይ ነው። በዚህ አጋጣሚ ይህ ጥያቄ ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲቀርብላቸው ለዳረጉት በፈረንሳይ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።
ጠሚዶኮ በአሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምዕመናን ጋር በነበራቸው ግኑኝነት ወቅት የሊቁ ጉዳይ የሚያነሳ አንድም ሰው ባለመኖሩ በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ ያለፈ ጉዳይ ቢሆንም በትናንትናው ዕለት ግን በእምነት የእስልምና እምነት ተከታይ በሆነችው እህታችን ከሚላት አንደበት ለጠሚው የሊቃችንን ደኅንነትና ነፃነት ሁኔታ በህዝብ ሁሉ ፊት በጥያቄ መልክ ቀርቧል።
የሊቁ ጉዳይ በሰሜን ጎንደሩ ሊቀጳጳስ በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በኩል፣ በደቡብ ጎንደሩ ሊቀጳጳስ በብፁዕ አቡነ ኤልሳ በኩል፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን 6 ተኛ ፓትሪያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በኩል፣ አሁን በዕርቅ ወደ እናት ቤተክርስቲያን በተመለሱት በቀድሞው በስደተኛው ሲኖዶስ አባቶች በኩል፣ በአሜሪካ በሚገኙ ማኅበረ ካህናት በኩል፣ በታዋቂ ሰዎች በኩል በደብዳቤ ጭምር ከዚህ ቀደም ለጠቅላይ ሚንስትሩ መቅረቡ ይታወሳል። በሊቁ ጉዳይ የተለያዩ ዓለምአቀፍ ዘመቻዎች፣ ሰላማዊ ሰልፎችም ተደርገዋል። እንደ ኢሳት ባሉ ሚድያዎችም ሰፊ የሚድያ ሽፋንም ተሰጥቶ ለመንግሥት ጥያቄዎች ቀርበዋል።
በአሁኑ ጊዜ በጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ አጠገብ በቅርበት በሚገኘው ወንድማችን በሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የግል ጥረትም ብዙ ተሞክሯል። ሆኖም ግን እስከ አሁን ድረስ ከክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ አንደበት ሊቁን በተመለከተ ግን የተሰጠ ምላሽ አልነበረም። በእኔ በኩል ለጠሚዶኮ ዐብይ ከጎረፉላቸው ጥያቄዎች ብዛት የተነሳ ጉዳዩን ችላ ብለውታል የሚል ግምት የለኝም። ሆኖም ግን ሊቁ የታሰሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሙሉ ኃይላቸውን ተጠቅመው ማዘዝ ባልጀመሩበትና በማይችሉበት ክልል በመሆኑ ሊቁን የማስፈታቱ ጉዳይ ሊሳካላቸው እንዳልቻለ እገምታለሁ። ለጊዜው ከትግራይ እንኳን የታሰረ ሊፈታ ቀርቶ ሠርቆ መቐለ የተደበቀን ሌባን ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ አቅምም ስልጣንም ያለው ባለሥልጣን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። እናም ይኸው ነው።
ለጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ ሊቁን በተመለከተ በከሚላት በኩል ለቀረበላቸው ጥያቄ ጠቅላያችን ሲመልሱ እንዲህ ነበር ያሉት። ” መምህር መሪጌታን በአካል ባላውቃቸውም በነበረው ጥያቄ የተነሳ ስለ እሳቸው ስሰማ ከተጻፈልኝም ጉዳይ ሳነብ ትልቅ ባለ ቅኔ ካህን ፣ ብዙ አዋቂ ጠያቂ ተመራማሪ እንደሆኑ ሰምቻለሁ። … እነዚህ ሰዎች የተለያዩ ቦታ አሉ ሲባል ሰምቼ ብዙ የማፈላለግ ሥራ ለመሥራት ሞክሬያረለሁ። … በተለይ መምህር መሪጌታን በሚመለከት የተጠቆመው ቦታ እዚያ አካባቢ ካሉ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ሰፊ ሙከራ ያደረኩ ቢሆንም እስከአሁን አልተሳካም። ወደፊት ሲሳካ አውነተኛውን ዜና ስናውቅ የምንገልጥላችሁ ቢሆንም እስከ አሁን ባለው ከመላምት ባለፈ እውነተኛ ነገር እኔ የማውቀው እንደሌለ ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ” ነው ያሉት።
ጠሚዶኮ ዐቢይ ላለፉት 20 ዓመታት በአገዛዙ ውስጥ ባለው የደኅንነት ክፍል ቋሚ አገልጋይ የነበሩ ሰው ናቸው። እናም አበው ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም እንዲሉ ጠሚዶኮም የአገዛዙን የደኅንነት መስመር አሳምረው ያውቃሉና ጨከን ብለው ቢገፉበት ውጤት አያጡም ባይ ነኝ። በጎንደር ሊቁን አስሮ ይጠብቅ የነበረ ግለሰብ እዚያው ጎንደር በሰላም እየኖረ ነው። ይህን ግለሰብ እንኳ ጠርቶ የት እንዳደረሳቸው ቢጠየቅ የሊቁን ዳና ለማግኘት ይረዳል የሚል እምነት አለኝ።
ለማንኛውም እንግዲህ ጉዳዩ እዚህ ከደረሰ እኔ ደግሞ ለጠቅላዬ ምክር ቢጤ ልለግስ። የሊቁ ቤተሰቦች ሊቁ ያሉበትን ሥፍራ የሚያውቁና ሊቁንም በቅርቡ በአካል ያዩዋቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ የሆኑ ሰውን ያውቃሉ። የሊቁን በህይወት መኖርም ለቤተሰቡ የነገሩት እኚሁ ሰው ናቸው። እናም የሊቁን ቤተሰብ ወደ እርስዎ አስጠርተው ቢያነጋግሯቸው መልካም ይሆናል። እነሱም ቁርጣቸውን አውቀው እርማቸውን አውጥተው ይቀመጣሉ። እናም 25 ዓመታት ሙሉ አባታችን ተፈትተው ከአሁን አሁን ይመጣሉ ብለው ደጅ ደጁን እያዩ በሰቀቀን እያለቁ ያሉ ቤተሰቦችም እርማቸውን ያወጡ ዘንድ ማድረጉም አንድ ጽድቅ ነው።
እንዲህ በሰቀቀን ምስኪኖችን ያሳቀቁ ግን እነሱም በሰቀቀን መኖራቸው አይቀርም። እኔ የምፈራው ለኃጥአን የታዘዘ በትር ለጻድቃን እንዳይተርፍ ብቻ ነው።
ሻሎም !  ሰላም !
Filed in: Amharic