>
5:13 pm - Friday April 20, 8863

ትንቢተ ሼህ ሁሴን ጂብሪል (ስንዱ አበበ)

ትንቢተ ሼህ ሁሴን ጂብሪል

 

ስንዱ አበበ

 

ልጅ እያለሁ ቤተሰቦቼ ቤት በእጅ ፅሁፍ የተጠረዘ ደብተር የሸህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢቶችን እንደ ትልቅ ሰነድ ሲንከባከቡት እኔም አልገባኝ እያለ ደጋግሜ አነበው ነበር ።

ጋዜጠኛ ሆኜ ማሻን ና መቅደላን ከአካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት ጋ ለስራ ሄጄ በነበር ወቅት ስጎበኝ አንዲት አዛውንት እናት ስለ ሽህ ሁሴን ና ስለ ሽህ እንዳሻው ” እነ እነነዬን እናንተ ከተሜዎችም ታቁዋቸዋላችሁ ? ” ብለው ተደንቀው ብዙ አስደናቂ ታሪክ አውግተውኛል ።

በተለይ የሸህ ሁሴን ና የሸህ እንዳሻው ሙግቶችን ።

በርግጥ እዛ አካባቢ ብዙ ጥናቶች ሊደረጉ ይገባል ።

ስለ ሸሆቻችን 

ስለ “አብሽ ለምኔ ” ጤፍ 
ስለ—

( ስለዚህ ድንቅ ጉዞ የፃፍኩት 115 ገፅ ዘገባ የራድዮ ፋና ስራስኪያጅ ቆልፈውበታል ። ይሰማል አቶ ወልዱ ? )

ከሽህ ሁሴን ጅብሪል ፍርድ ይችን ክፍል መርጫለሁ ።

ፍርዱ ይፈፀምስ ዘንድ ግድ ነው ?

ፍርድን መቀልበስ ወይም ማረቅ ይቻላል ?

ግጥማቸው እነሆ፦

“በስምንተኛው ሺህ በስተመጨረሻ
ከሰሜን የመጣ ነገረኛ ውሻ
ነጥቆ ይወስደዋል ፤ የመሆኒን መሬት ፤ የራዮችን እርሻ።

ጠጉራቸው ጨበሬ ቋንቋቸው የግራ
አፋቸው ሙጎጎ ፤ ቀልባቸው ወንጋራ
ጋግረው ያበሉናል ፤ የተንኮል እንጀራ።

አጥንትና ወገን ጎጥ እየቆጠሩ
በደረቅ ቀልባቸው እየተማከሩ
በድፍድፍ እጃቸው ቂጣ እያነኮሩ
መቼም ላንድ ሰሞን ፤ ይጠፋል ሃገሩ።

ወሎ ቡን ይወዳል አቦል እስከ ቶና
ዛሬም ዱኣ ያውቃል እንደትላንትና
እነዚያ ጨበሬዎች ቀኑ ሲከዳቸው
አርከባስ እያለ ወሎ ነቀላቸው።

በሁለት ሺህ አመት ደግሞ በሃስራ ሃንድ
እንዲያው ላንድ ሰሞን ፤ ደፍረስረስ ይልና የጦቢያ መንገድ
ዱኣው በጦሳ ላይ መልሶ ሲወርድ
መለይካ ሚመስል ፤ ዘሩ ከነአህመድ
ከጅማ ይዘልቃል ፤ ሊያረገን ዘመድ።

መልኩ እንደ ኢያሱ ነው ንግግረ ሸጋ
ምላሱ መድሃኒት ፤ ነገሩ የረጋ
በሱነው ጨለማው ቶሎ የሚነጋ።

እሱ በነገሰ በሶስተኛ አመት
የጎበዞቹ ሃገር ራያ ሚሉት
መሬቴን መልሱ እያለ ይነሳል
እምቢ ያሉት እንደሁ ፤ ና ውረድ እያለ ጎራውን ያፈርሳል።

ያኔ ያች ተሃት ቀልቧን ታዞራለች
መርዝ እንደቀመሰ አይጥ ትውለበለባለች
ራያ መሬቱን አለቅም ትላለች።

ያኔ ነው እድሜዋ ቶሎ የሚያበቃ
አልመልስም ስትል የሰው መሬት ሰርቃ።
ያኔ ነው የተሃት የሚያልቀው ነገሯ
ራያ ሜዳ ላይ ይቆፈራል ቀብሯ.”

***** በዚህ ትንቢታዊ-ግጥም ውስጥ ሁለቱ ተፈጽመዋል አንዱ ነው የቀረው እሚሉም አጋጥመውኛል

Filed in: Amharic