>
5:13 pm - Wednesday April 18, 6114

ኢትዮጵያዊው ናዚ የአዶልፍ ኤክማንን ጽዋ የሚጎነጫት መቼ ይሆን??? (አበበ ግዜ)

ኢትዮጵያዊው ናዚ የአዶልፍ ኤክማንን ጽዋ የሚጎነጫት መቼ ይሆን???
አበበ ግዜ
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በጀርመን የስለላ መዋቅር ሥር “የአይሁዶች ጉዳይ” በሚባል ስም የተቋቋመ ዋና መምሪያ ነበር። ከዚህ የስለላ ዋና መምሪያ በሚተላለፍ ትዕዛዝ ወደ 6 ሚሊዬን የሚጠጉ አይሁዳውያን እጅግ ዘግናኝ በሆነና ኢሠብአዊም ኢሞራላዊም አኳኋን ተጨፍጭፈዋል። ይህንን ሁሉ ዘግናኝ ድርጊት በበላይነት ይመራ የነበረው ግለሠብና የስለላ መዋቅርና አደረጃጀት ጦርነቱ አብቅቶ የናዚ ወንጀለኞችና ከጭፍጨፋው ያመለጡ አይሁዶች በኑረምበርግ ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እስከሚሠጡ ድረስ ምንም የሚታወቅ ነገር አልነበረም። በፍርድ ሂደቱ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ የስለላ መዋቅሩ አደረጃጀት ሲጋለጥ ያን ሁሉ ጥፋት ሲያቀነባብርና ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ሲያስፈፅም የነበረው  “የአይሁዶች ጉዳይ ዋና  መምሪያ” የሚባል እንደሆነ ተጠርጣሪዎቹ የምስክርነት ቃላቸውን በመስጠት አረጋገጡ። ነገር ግን የዚህን ዋና መምሪያ ሃላፊ በሥም ሆነ በአካል የሚያውቅ እኔ ነኝ የሚል ሠው ጠፋ።  ቀስ በቀስ ግን በፍርድ ሂደቱ ቀርበው የነበሩት ተከሳሾች ተጨባጭ መረጃ በራሳቸው ላይ እየቀረበባቸው ሲመጣ ፍርዱን የሚያቀልላቸው መስሏቸው የግለሠቡን ሥም ይፋ አደረጉ። #አዶልፍ_ኤክማን።
#አዶልፍ_ኤክማን በወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙትና ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል አልነበረም። ሠውየው በጨካኝነቱ ይፈራ ስለነበረ ወንጀሉን ሁሉ ወደ #አዶልፍ_ኤክማ ተጠርጣሪዎቹ መደፍደፋቸው ሞቷል ብለው በማመናቸው እንደነበረ ይገመታል።  #አዶልፍ_ኤክማን ግን የት ነበር እውን እንደተባለው ሞቶ ይሆን? ወይስ ሌላ እውነት? እስራኤል የፍርድ ሂደቱን ሃያ አራት ሰአት ነው የምትከታተለው። የናዚ ወንጀለኞችንም አድኖ በመያዝ እንዲሁ። #የአዶልፍ_ኤክማን መጨረሻ ለማወቅ የሠውየውን ውልደትና አስተዳደግ እንዲሁም አካላዊ ሁኔታና የሥራ ታሪክ ማወቅ ግድ ነበር።  በተደረገውም ጥረት በአካል ከሚያውቁት አይሁድችና ሌሎች ሰዎች እንዲሁም ከናዚ ፓርቲ ዋናው ጽ/ቤት በርካታ መረጃ አገኙ።  ይህንን ወንጀለኛ ግለሠብ አድኖ ለመያዝ እጅግ አድካሚ ስራዎች ተሠርተዋል። አልጀርስ ቦነሳይረስ ውስጥ እንደሚኖር ከተሠማ በኋላ እንኳን #አዶልፍ_አክማን በሚባል ስም የሚጠራ ሰው ማግኘት አልተቻለም ነበር። ነገር ግን በሌሎች መረጃ መሠረት ስሙ ሌላ ቢሆንም #አዶልፍ_ኤክማንን የሚመሥል ሠው ስለነበረ የሚገኙትን የሥለላና የክትትል መረጃዎች በማገናዘብ እያንዳንዷ እንቅስቀሴው ትመዘገብና ትተነተን ነበር።
ሠውየው ቦነሳይረስ የሚኖረው ከቀድሞ የአዶልፍ ኤክማን ባለቤት ጋር እንደሆነ ተረጋግጣል። ሁለት ልጆች ወልዷል። ሦስተኛው የአዶልፍ ኤክማን ነው። ባይረጋገጥም።  ነገር ግን የሚጠራው በሌላ ሥም ስለነበረ አዶልፍ ኤክማን ስለመሆኑ እርግጠኛ ለመሆን ጊዜው ገና ነበር።  የናዚዎች ህቡዕ እንቅስቃሴ ስለነበረ የናዚ አባላትን ወደ ሌላ አገር  በማስኮብለል ዘመቻው ሠውየው ማንነቱን ቀይሮ ሊሆንም እንደሚችል ታምኗል። ያገባበትን ቀን ጨምሮ ያርካታ መረጃዎችን ያውቁ ስለነበር ለመጀመሪያ ጊዜ አበባ ገዝቶ ሲገባ ያጨረሻ ማረጋገጫ የሆነውን መረጃ አገኙ። ያች እለት ከአሁኗ ባለቤቱ ጋር የተጋባባት ነበረች።  ክሌመንት በሚባል ስም ቀይሮ የድሮዋን ባለቤቱን እንደገና በማግባት አዶልፍ ኤክማን ሞቷል ለማስባልና ራሡን ለመደበቅ ነው የተጠቀመበት። ያም ሆኖ ግን የመጨረሻው ሆነ።ስለሆነም ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላ ከ15 አመታት አድካሚ ክትትልና ስለላ በኋላ አርጀንቲና ቦነሳይረስ ውስጥ ቬራ ሊብል (ቬሮኒካ) ከምትባለው ሚስቱ ሲኖር ሳለ ከሥራ ወደ ቤቱ በሚመለሥበት ወቅት መኖሪያው አካባቢ ከተሣፈረባት አውቶቡስ ወርዶ አስፋልቱን ሊሻገር ሲል በእስራኤል የደህንነት ሠዎች ቅንብር በመኪና ታፍኖ አዳኞቹ ወደ አዘጋጁት ቤት ተወሠደ።
ቤት እንደደረሡም ልብሱን አስወለቁት። ነገር ግን አጋጆቹ አልደበደቡትም አላናገሩትም። ሲጠይቃቸውም መልስ አይሰጡትም እርስ በእርሳቸውም በእርሱ ፊት ምንም ነገር ትንፍሽ አይሉም። ድርጊት ብቻ። ትዕዛዝ ብቻ። ግን አሁንም ቃልም ምልክትም አላሳዩትም። ሠውየውን እንደ እንቁላል ነበር መንከባከብ የነበረበቸውና ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስበት ከፍተኛ ጥንቃቄ ነበር ያደረጉት። #አዶልፍ_ኤክማን የሠራውን ወንጀል አስቦ የበደላቸው ሠዎች በእጃቸው  ሥር አድርገውት ምንም አለማድረጋቸው ሲያይ ፍትህና ፍርድ እንጂ ስቃይ እንደማይገጥመው ገብቶታል። በልቡም ለሠራው ወንጀል መጠየቁ ተገቢ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ህይወቱን ሙሉ ራሡንና ቤተሠቡን በበረያውቁና በጥርጣሬ አጥሮ ከመሠቃየት ቁርጡን በማወቁ አሁን እፎይታ ተሠምቶት ነበር። ከአጋቾቹ አንዱ “አንተ ማነህ?” ሲል ጥያቄ አቀረበለት።”ኢሽ ቢን አዶልፍ_ኤክማን” ሲል መለሰ በፍጥነት። ዝምታ፤እርጋታ። አሁን የያዙት ሠዎች ፕሮፌሽናልስ እንደሆኑ ገብቶታል። አማተሮች አይደሉም። ቀጥሎም “አሁን በማን እጅ እንደወደቅሁ አውቄዋለሁ እስራኤሎች ናችሁ አይደል?” አላቸው። መልስ የሠጠው አልነበረም።
ቀጥሎ አጋጆቹ በአይሁዶች ላይ ስለፈጸመው ወንጀል እስራኤል ሄዶ በፍርድ ቤት ቀርቦ ለመመሥከርና ሁሉንም ጥፋቶች ለማጋለጥ ተሥማሞቻለሁ የሚል ጽሁፍ ላይ እንዲፈርም ሠጡት። እርሱም አንብቦ ሲጨርስ “ብዕርና ወረቀት ስጡኝና በራሴ ላዘጋጅ” አላቸው። በብዕሩ ተጠቅሞ ራሱን እንዳይጎዳ ጉዳት ማድረሥ የማይችል ብዕርና ወረቀት ሠጥተውት ከክፍሉ ወጡ። በቅርብ ርቀት የሚጠብቁት የሚከታተሉት አይናቸውን የማይነቅሉ  ቃፊሮች ግን ነበሩ። ለቃፊሮቹ እንደ ጨረሰም ሲነግራቸው አጋቾቹ/መርማሪዎቹ መጥተው የፃፈውን ሲያዩ ማመን አቃታቸው። አዶልፍ ኤክማን በጀርመን በመጨረሻወቹ አመታት ስለፈፀማቸው ማናቸው ጉዳይ በዝርዝር እንደሚገልፅ ይህንንም ተገዶ ሳይሆን በፈቃዱ ያደረገው መሆኑና ለሚመጣው ትውልድ እውነተኛ ስዕል እንዲኖረው በማድረግ የህሊና ሰላም ለማግኘት እፈልጋለሁ የሚል ነበር። አዶልፍ ኤክማን, ቦነሳይረስ, ግንቦት 1960 ዓ.ም።
በመጨረሻም ወደ እስራኤል በሚበሩበት ምሽት ከአርባ አምስት ደቂቃ በኋላ የሚያደነዝዝ እፅ በቡና ሠጡት። ከአርባ አምስት ደቂቃ በኋላ ጋወን አልብሠው የታመመ እድሜ የገፋ ሃብታም ሽማግሌ አስመሥለው ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ገሠገሡ። አውሮፕላኑ ውስጥ ለታማሚው በማለት ብዙ ወንበሮች ተይዘው ነበር ከኋላ። አጋቾቹ ዘመድና አስታማሚ ነርሶች በምሠል የሥራ ድርሻቸውን በደንብ እየተወጡ ነው። በረራው ወደ ምእራብ አፍሪካ አመራ። #አዶልፍ_ኤክማን ሲነቃ በ3 ቴርሞዝ ከያዙት በአደንዛዥ እጽ ከተዘጋጀው ቡና እያቀመሡት ያለምንም ችግር ጉዞው ተጠናቀቀ። ወደ እስራኤል የነበረውም በረራ እንዲሁ ያለምንም እንከን ተጠናቀቀ። እስራኤል እንንደደረሠም ግንቦት 23, 1960 ዓ.ም የክስ መጥሪያና የክስ ዝርዝር እንዲደርሰው ተደረገ። በዚሁ ቀን ከሠአት በኋላ ጠ/ሚ ዴቪድ ቤንጎሪዎን ካቢኔያቸውን አስቸኳይ ስብሠባ ጠርተው ነበር። የካቢኔ አባላትም የተጠሩበትን ጉዳይ ምንነት ለማወቅ ሠግጦ የያዛቸውን ጉጉት ለመገላገል ከመጓጓታቸው የተነሳ ጠ/ሚ ከተቀመጡበት በም/ቤቱ አፈ ቀላጤ ጋባዥነት ንግግር ወደሚያደርጉበት ጥቂት እርምጃዎችን አድርገው እስኪደርሱ ድረስ ያለኮሽታ ትንፋሻቸውን ውጠው የካቢኔ አባላቱ ይጠብቋቸው ነበር። እንዲህም አሉ። ከናዚ የጦር ወንጀለኞች መካከል አንዱ #አዶልፍ_ኤክማን በቁጥጥር ሥር ውሎ በአሁኑ ሠአት እስራኤል ውስጥ ይገኛል። በአጭር ጊዜ ውስጥም በህጉ መሠረት ለፍርድ ይቀርባል። ም/ቤቱ በደስታና በጭብጨባ ሞቀ ደመቀ።
ከሁለት ቀናት በኋላ አዶልፍ ኤክማን ከጭፍጨፋው ተርፈው እና የአይሁድ ጥላቻ ስር ከሠደደበቸው አገሮች በመጡ አይሁዶች ያለሙት ሸለቋማ አካባቢ ወደ ሚገኝ ካምፕ ኢየር ከተባለ ጊዚያዊ ግን ሚስጥራዊ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተወስዶ ቢሮ ቁጥር 06  በሚሠሩ መርማሪዎች በቀን ብዙ ጊዜ የምርመራ ጥያቄ ይቀርብለት ነበር። ፋታ ሲያገኝ ልብወለድ መጽሃፍ ያነባል። በድንገት ያለቅሳል። ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሞትን አምልጠው ያለሙትን ሸለቆ ከፎቅ ላይ ሆኖ እየቃኘ ይደመማል። እርሡ ካደረሠባቸው መከራ አንፃር ሲታይ አሁን የሚኖርበት ቤት እና አያያዝ የማይነፃፀር የቅንጦት ቦታ ነበር። አካባቢውንም ማን እንደለወጠውም ገብቶታል። ወንጀለኛነት ብኩን ያደርጋል ። የኢትዮጵያ አዶልፍ ኤክማን ጌታቸው አሠፋም ተመሳሳይ እጣ-ፈንታ ይጠብቀዋል።
Filed in: Amharic