>

ከፖለቲካ በፊት ሰውነት ይቀድማል!!! (ስዩም ተሾመ)

ከፖለቲካ በፊት ሰውነት ይቀድማል!!!
ስዩም ተሾመ
የጀርመን፥ ፈረንሳይ ወይም የካናዳ መሪዎችን ዛሬ በአካል የማግኘት እድል ባይኖርህ ነገና ከነገ ወዲያ በእቅድ አሊያም በአጋጣሚ ልታገኛቸው እንደምትችል ታውቃለህ። ስለ መሪዎቹ የዕለት ከእለት እንቅስቃሴ መረጃ ብትፈልግ ከብዙ ሚዲያዎች ማግኘት ትችላለህ። በእርግጥ ስለ ኢትዮጵያ መሪዎች በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃ ልታገኝ ትችላለህ። በአካል የማግኘት እድሉ ሲያጋጥምህ ግን እንደ መሪው ይለያያል። እንደ መለስ ዜናዊ ያለ መሪን በአካል የምታገኘው እሱ ሲፈልግ ብቻ ነው። ከፊቱ ላይ የሚታየው ሳቅና ፈገግታም ለአንተ ሳይሆን ለቪዲዮ ካሜራው ነው። ከዚህ በተረፈ ግን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በመኪና ሲያልፉ የመሪዎቹን መልክ በጨረፍታ እንኳን ማየት አትችልም። ምክንያቱም ከገና በመዓት አጃቢዎች የተከብበው መኪና ወደ አንተ እየተቃረበ ሲመጣ ወታደሮችና ፖሊሶች ፊትህን እንድታዞር በጩኸትና በቁጣ ያዋክቡሃል። እንደ መለስ ዜናዊ ያሉ መሪዎችን ልክ እንደ ዛሬው በበርሊን ጎዳና ላይ በድንገት ብታገኛቸው ደግሞ ብሶትና አቤቱታህን በተቃውሞ ለመግለፅ እንጂ አቅፈህ ልትስማቸው አትጣደፍም።
አብዛኞቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ልክ እንደ መለስ ዜናዊ ከህዝቡ በ…ጣ…ም የራቁ፣ በቴሌቭዥንና ራዲዮ ካልሆነ በስተቀር በአካል የማይታዩ፥ የማይጨበጡ፥ የማይዳሰሱ፥ የማይስቁ፥… ወዘተ ናቸው። በሀገር ውስጥ ሆነ በስደት ለሚገኙ ዜጎች የሚናገሩ እንጂ እንደ ሰው የማይናገሩ ናቸው። በእርግጥ የቀድሞ መሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በቅርብ ለሚያቋቸው ሰዎች የሰውነት ባህሪና ስብዕና ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እንደ ፖለቲካ መሪ ግን ከህዝብ የተነጠሉ አስፈሪ ግዑዝ ፍጥረታት ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ምንም ዓይነት የሰውነት ለዛና ወዝ የሌላቸው ግዑዝ ፍጥረታት ናቸው። እንደ ዶ/ር አብይ አህመድ ዓይነት የሰውነት ወዝና ለዛ ያለው መሪ ሲመጣ ታዲያ ሄደህ ጥምጥም ትልበታለህ። ትከሻውን አቅፈህ፣ ጉንጩን እየሳምክ፣ ጸጉሩን እየዳሰስክ፣ የሀገሪቱ መሪ ልክ እንዳንተ ሰው መሆኑን በተግባር ታረጋግጣለህ። የፖለቲካ ብቃትና ክህሎት ቀስ ብሎ ይደርሳል። በመጀመሪያ የፖለቲካ መሪው ልክ እንዳንተ የሚታይ፥ የሚዳሰስ፥ የሚታቀፍ፥… የሰውነት ወዝና ለዛ ያለው ህያው ፍጡር መሆኑን ማረጋገጥ አለብህ። እንደ ልዩ ፍጡር ስሜትህን የማይጋራህ፣ በደልና ጭቆናን ስትቃወም ለእስርና ስደት የሚዳርጉ መሪዎች በነገሱበት ሀገር አዲስ መሪ ሲመጣ በቅድሚያ ልክ እንዳንተ ሰው መሆኑን በአካል አቅፈህና ዳስሰህ ታረጋግጣለህ። ምክንያቱም ከፖለቲካ በፊት ሰውነት ይቀድማል!!!
Filed in: Amharic