>
5:13 pm - Wednesday April 19, 0980

ዶ/ር አብይ በአውሮፓ ጉብኝታቸው ወቅት በአማርኛ መናገራቸው ከሰነፎች ሰፈር ጫጫታን ፈጥሯል!!!

 ዶ/ር አብይ በአውሮፓ ጉብኝታቸው ወቅት በአማርኛ መናገራቸው ከሰነፎች ሰፈር ጫጫታን ፈጥሯል!!!
ኤርሚያስ ቶኩማ
ይቺን የኮሎኔል መንግሥቱ ንግግር እንዳስታውስ ያደረገኝ የአውሮፓ መሪዎች ለዶክተር አብይ እየሰጡት ያሉትን ክብር መመልከቴ ነው። 
ከዚህ ቀደም ለነበሩን የኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በሙሉ የአውሮፓ ሐገራት መሪዎች አቀባበል የሚያደርጉላቸው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ነው ይኸውም አንድም ከንቀት ሲቀጥል አምባገነናዊ ስርአት ለሚመሩ ግለሰቦች ክብር ስለማይሰጡና መሪዎቻችንም በራሳቸው ክብረ ቢስ ስለነበሩ ነው። ጓድ መንግሥቱ በገነት መፅሀፍ ላይ ስለጉዳዩ ሲገልፁ እንዲህ ነበረ ያሉት
“አሜሪካኖች ደካማ አይወዱም:: ድክመቱን ካዩ መጫወቻ ነው የሚያደርጉት:: ዛሬ ጊዜና ሁኔታው ተለውጦ ያሉትን ገዢዎች ከግራ ከቀኝ እንደ ቴኒስ ኳስ ይጠልዙዋቸዋል እንጂ ሌላ ጊዜማ ይፈሩን ነበር::
እኛን <እንዲህ አድርጉ እንዲህ አታድርጉ> ብለው ትዕዛዝ ሊሰጡን እንደማይችሉ ስለሚያውቁ አክብረውን ነበር የሚኖሩት::<መጐብኝት ይቻላል ወይ? ትፈቅዱልናላችሁ ወይ? ፕሬዝዳንቱን ለማነጋገር የሚመጣው ማነው?> ብለው አስቀድመው ይጠይቃሉ:: አንድ የመምሪያ ኋላፊ ወይም ዳይሬክተር ከሆነ እኔ ጋር አያቀርቡትም:: ፕሬዝዳንታችሁ ወይም ሌላ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቢያንስ የሚንስትር ደረጃ እንኳን የሌለው እንዴት የኛን ፕሬዝዳንት ማነጋገር ይችላል ብለው ነው ከአየር መንገድ የሚመልሷቸው::
ለምሳሌ ከዚህ ከአይሁዲው በፊት የነበረው የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እሱም ራሱ አይሁዲ ነበር <ፕሬዝዳንቱን ላነጋግር እፈልጋለሁ> ይላል <ና> ይሉታል:: እሳቸውን ማነጋገር እንደምችል  ይረጋገጥልኝ እና ልምጣ> ይላል:: <አይ እንግዲህ ከፈለክ ና:: ከመጣህ በኋላ አንተን የማነጋገር ያለማነጋገር ጉዳይ የሳቸው ውሳኔ ነው> የሚል መልስ ይሰጡታል:: ሲመጣ <አሁን ምጽዋ ጉብኝት እያደረጉ ነው የሉም ሲሉት <መንግስቱ ኋይለማርያም እኔን ላለማነጋግር ሆን ብሎ ያደረገው ነው> ብሎ ሌላም ሌላ ብዙ ተናገረ:: የውጭ ጉዳይ ሰዎች እነብርሃኑ ባየህ ናቸው:: <አንተ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ነህ ማነጋገር የምትችለው አቻህን ግፋ ቢል ሌሎችን ሚኒስትሮች እንጂ ፕሬዝዳንቱ ጋር ምን አንጠለጠለህ? እኛ ለተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ኒውዮርክ ስንመጣ የናንተ ፕሬዝዳንት ተቀብለው ያነጋግሩናል ወይ? ማን አስተናግዶን ያውቃል? አንተ ዘለህ ይህን እንዴት ልጠይቅ ተደፋፈርክ?> ይሉታል:: <እንዴ! እናንተ ማን ሆናችሁ ነው እንደዚህ የምትሉኝ? እኔኮ የትም ሀገር ሄጄ ጠቅላይ ሚንስትሮችም ሆኑ ፕሬዝዳንቶች ያለችግር ተቀብለው ነው የሚያናግሩኝ:: በቅርቡ የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትሩም ፕሬዝዳንቱም ተቀብለውኛል> ሲል <እኛ ሕንድ ወይም ሌላ አይደለንም ኢትዮጵያውያን ነን> ብለው ይመልሱታል:: ከዚያ በኋላ ዝም ብሎ ሄደና ኬኒያ ሲደርስ ጋዜጠኞችን ሰብስቦ እኛን ሙልጭ አድርጐ ተሳድቦ ወደ አገሩ ተመለሰ::> ብለው ነበረ።
አሁን ክብሩን የጠበቀ የተከበሩ መሪ በማግኘታችን የአውሮፓ ኃያላን ሐገራት መሪዎች በክብር ይቀበሉናል፤ ዶክተር አብይ ባለፉት 27 አመታት በነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች የተነሣ ክብሯ የተገፈፈውን ሃገራችንን ወደተሰሚነት እየመለሳት ይገኛል፤ ለዛም ነው የአውሮፓ መሪዎች አየር ማረፊያ ድረስ እየጠበቁ አቀባበል እያደረጉለት የሚገኙት። አውሮፓውያንን በቋንቋቸው ሳይሆን በአማርኛ ቋንቋ የሚያናግር ኩሩ መሪ አግኝተናል።
እርግጥ ነው ዶ/ር አብይ በአውሮፓ ጉብኝታቸው ወቅት በአማርኛ መናገራቸው ከሰነፎች ሰፈር ጫጫታን ፈጥሯል :: ጠ.ሚ. በሚመሩት ሃገር ብሄራዊ ቋንቋ መናገራቸው የስብዕናቸውን ከፍታና በራስ የመተማመናቸውን ልክ ማሳያ ነው::
አቶ ጥበቡ የተባሉ ምሁር ስለ አማርኛ ታሪካዊ አመጣጥ ባተቱበት ጽሁፍ ውስጥ እንዲህ ብለው ነበር::
… ጏድ መንግስቱም የመንግስታቸው ቋንቋ አማርኛ ነበር :: ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ለሕዝባቸው የሚናገሩት በአማርኛ ቋንቋ ነበር። ሊግ ኦፍ ኔሽን፣ ጄኔቫ ላይ ያሠሙት ታሪካዊ ንግግርም ሣይቀር በአማርኛ ቋንቋ ነው።
 አጤ ምኒልክም ለሕዝባቸው የሚናገሩት በአማርኛ ቋንቋ ነው። ታላቁን የአድዋ ጦርነትም ያወጁት በአማርኛ ቋንቋ ነበር። የአድዋን ድልም ያበሰሩት በአማርኛ ቋንቋ ነው።
 ከእርሣቸው ቀደም ያሉት አፄ ዮሐንስ እና አፄ ቴዎድሮስም ከሕዝባቸው ጋር በአማርኛ ቋንቋ ነበር የሚነጋገሩት። እናም አማርኛ የመንግሥት ቋንቋ ነው። እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው መሪዎች አማርኛ ቋንቋ ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥር የተደራሽነት አቅሙም ከፍ ያለ መሆኑን አምነን መቀበል ግድ ይላል።  ጠቅላያችንም የሐገሪቱን ብሔራዊ ቋንቋ ተጠቅመው ሀሳባቸውን መግለጻቸው ለእርሳቸውም ለሀገሪቱም ትልቅ ክብርና ሞገስ ነው።
Filed in: Amharic