>

የሕወሃት መሪዎች መሰሪ እቅድና በመለወጥ ላይ ያሉት ሁኔታዎች!  (ሀይል ገብርኤል አያሌው)

የሕወሃት መሪዎች መሰሪ እቅድና በመለወጥ ላይ ያሉት ሁኔታዎች! 
ሀይል ገብርኤል አያሌው
ሕወሃት ሲቀምር የኖረው ሃገሪቷን የማፈራረስ መሪ እቅድ በከፊል ቢከሽፍም: አሁንም በየአቅጣጫው መዘርጋት የሚችል እረጅም እጅ አለው:: የጽንፈኛው የዳውድ ኢብሳ ኦነግ ስውር ሃገር የማበጣበጥ ሴራ ዛሬ ገሃድ ሆኖ ከመንግስት ሃይሎች ጋር መታኮሱ ተሰምቷል:: ኦነግ በተለይ መሪው ዳውድ ኢብሳና ጥቂት የባዕዳን ቅጥረኛ የሆኑት ተከታዮቹ ለአማራና ለኢትዮጵያዊነት  ካላቸው መረን የለቀቀ ጥላቻ የተነሳ ከሕወሃት ጋር በመመሳጠር መዐከላዊ መንግስቱን ለማዳከምና የአማራውን ሕዝብ ትግል በተለያየ ግንባር እንዲወጠር በከባዱ ሕወሃት እየሰራችበት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: የለማ መገርሳ ኦዲግ እና አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ግን ከዚህ ተቃራኒ በመቆም የዳውድን ተልዕኮ እንደሚያከሽፍ
ምንም ጥርጥር የለኝም::
የሕወሃት እኛ ከሌለን ሃገር ይፈርሳል የሚለው ነጠላ ዜማዋ ሃገሪቷን በሁሉም ግንባር በሚቀጣጠል የብሄር ግጭት የማበጣበጥ ስትራቴጂ ነበር:: የኢትዮጵያ አምላክ ምስጋና ይድረሰውና ባልተጠበቀ ሁኔታ እየተለወጠ ያለው የፖለቲካ ሃይሎች አሰላለፍና የሕዝቡ ጠላቱን የመለየት አቅጣጫ እየጠራ ሄዶ ትኩረት ወደ ሕወሃት እየሆነ ነው::
 የሕወሃቱ የምስራቅ ኢትዮጵያን የሽብር ክንፍ የሱማሌ ክልል ፕሬዜደንት የነበረው አብዲኢሌ መታሰር የቡድኑ መዳከም አስከትሏል:: ከዚህም በላይ ለሱማሌ ክልል ብቻ አይደለም ሃገር ለመምራት የሚበቃ ተስፋ የሚጣልበት በሳልና አስተዋይ አዲስ የክልሉ መሪ  መሾሙ ለለውጥ ሃይሎች መልካም እድል  ለሽብርተኛው የወያኔ ቡድን ታላቅ ክስረት ሆኗል::
በኢትዮጵያዊነቱ ድርድር የማያውቀው የነሱልጣን አሊሚራ ምድር  አፋር የሕወሃት ቅምጦችን ለማስወገድ ጠንካራ ትግል እያደረገ ነው:: አፋሮች ትግላቸውን በማጠናከር ወደ ትግራይ የሚወስዱ አውራ ጎዳናዎችን እስከ መዝጋት መድረሱን ሚዲያዎች ዘግበውታል::
 በጋምቤላም እንዲሁ የክልል መሪዎች ለውጥ ተደርጏል:: የጋንቤላ ክልል የሕወሃት ሰዎች የሚሾሙና የሚሽሩበት ብቻ ሳይሆን መሬቱን ወረው ሕዝቡን በጅምላ እየፈጁ ያለ ተቀናቃኝ ሲፈነጩበት እንደኖሩ ይታወቃል:: የጋንቤላ  ክልል ለሕወሃት የኢኮኖሚ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የሽብር አላማቸውን ሊፈጽሙበት ያዋቀሩትና እንደልባቸው የሚያዙት የክልሉ ልዩ ሃይል እንደ ሱማሌው ክልል ሁሉ ከእጃቸው ለመውጣቱ እርግጠኛ መሆን ይቻላል:: በጋንቤላ የአመራር ሽግሽግ ላይ የዶር አብይ ሚናም የሕወሃትን ስር የመበጠስ እንደሚሆን አያጠራጥርም::
 አሁን ባለው ተጨባጭ የክልሎች የሃይል አሰላለፍ ውስጥ የጠራ አቅጣጫ ያላስቀመጠው የቤኒሻንጉል ክልል ነው:; ሕልም ሆኖ ቀረ እንጂ ክልሉ የወደፊቷ ታላቋ ትግራይ ግዛት አካል እንደምትሆን እነሁሉ ለኔ ከዚህ በፊት ባወጡት ካርታ አይተናል:: ሆኖም የቤኒሻንጉል ክልል አማሮችን በማፈናቀል የሕወሃትን ትዕዛዝ በጽናት ሲያስፈጽም ቆይቷል:: አሁንም የሕወሃት እጅ በዚህ ክልል አመራርና ታጣቂ ሃይል ውስጥ ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል::
የአማራው ሕዝብ ከሕወሃት ጋር ግጭት ውስጥ ቢገባ በመተከል በኩል ከቤኒሻንጉል የሕዉሃት ተላላኪዎች ትንኮሳ ሊኖር እንደሚችል ቢገመትም ሕወሃት ዙሪያ ገቡን የማሪያም ጠላት በሆነበት ከበባ ውስጥ ሊያመጣ የሚችለው ተጽዕኖ ያን ያህል አይሆንም::
በሰሜን በኤርትራ በኩል ቢሆን የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም እንዲሉ ለኤርትራ ሕዝብ መጠን የለሽ መጎሳቆል ሕወሃት ምክንያት መሆኑ ጠባሳው ገና አልሻረም:: ሕወሃት ስግብግብና ይልኙታ የለሽ ድርጅት በመሆኑ የአይናቸው ቀለም ያላማረውን የኤርትራ ተወላጆች እራቁት አባሮ በትግራይ ትግርኝ የነተበ ርዕዮት ሊያማልል አይንበረከክም ማለት አይቻልም :; ይሄ የተበላ እቁብ የሆነው የሕወሃት አቅጣጫ በተለያየ መልኩም ሲገለጽ እያስተዋልን ነው::
ኤርትራውያኖች ታኝኮ ከተተፋና ግዜ ካለፈበት ወንበዴ ጋር የሚዳሩ አይመስለኝም:: አይሆንም እንጂ በአግዐዝያን ትንግርት ተይዘው ከሕወሃት ጋር ቢቆሙም ከቶም ከታሪክ ትቢያነት አያድኑትም::
ለብዙዎች ጥያቄና ሃዘን የሚጭረው የትግራይ ወገናችን ከሕወሃት መንጋጋ አለመላቀቅ ነው:: የትግራይ ሕዝብ የመረጃና የሃቀኛ ልጆች እጥረት እንጂ ሕወሃት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከበደለው ባልተናነሰ እንዳውም በበለጠ በደል አድርሶበታል:: የትግራይ ሕዝብ በእስላም ስም የሚነግደውን አይሲስ ስለሚባል አንገት ቆራጭ አውሬ ታሪክ ያውቃል:: በሊብያም ከተሰውት ጥቂቶቹ ከትግራይ የሄዱ ናቸው:: ሕወሃት ማለት አይስስ ነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ:: እንዳውም በጭካኔውና በመሰሪ ተግባሩ ሕወሃት ከጭለማው ጌታ ከዳቢሎስ የሚልቅ እርጉም  ድርጅት ነው:: ትግራይን አይመጥንም::
የትግራይ ሽማግሌዎች እየመጣ ካለው ወጀብ በሰላም እንድናልፍ ይሉኝታችሁን አልፋችሁ ውጡ :: ብጥብጥን መሸከም የሚችል ትከሻ : ጦርነትን የምናስተናግድበት አቅም ማናችንም የለንም:: ነገር ግን ስለፈራንው የሚቀር አንዳችም ነገር የለም:: ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነጻነት በሚል መርሆ ለኖረ ሕዝብ ይቅርና እንስሳት እንኳን ልክ አላቸው:: የአማራው ሕዝብ ጥፍሩ እየተነቀለ ብልቱ እየተኮላሸ ለዘመናት ከኖረበት በግፍ እየተፈናቀለ ሁሉንም መከራ ችሎ ስለ አንድነቱ ሲል ታግሶ ቆይቷል:: ይህ አልበቃ ብሎ የአባቶቹን እርስት ወልቃይት ራያን  እና ሌሎቹን ተቀምቶ በተወለደበት ቋንቋ እንዳይናገር ባደገበት ባህል እንዳይመራ ማንነቱን በመደፍጠጥ የተካሄደበትን በደል መሸከም የማይችልበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል:: ይህ ብሶት የወለደው የሕዝብ ቁጣ ወደ እሳተ ጎመራነት ሳይለወጥ መነጋገር ቢቻል መልካም ነው:: የፖለቲካ ድርጅት አላፊ ጠፊ ነው:: ሕዝብ ግን ዘላለማዊ ነው:: የትግራይ ወገን ይህን ሊያስብ ይገባል:: የሃይማኖት አባቶች ሕዝቡን ሊያስማሙ ግፈኞችን ሊያወግዙ ይገባል::
…አማራ ሕዝብ ጸቡ ሕወሃት ከተባለ የሽብርና የዘረፋ ቡድን ጋር ብቻ ነው:: …..
ጥያቄዬ በሰላም  ይመለስ እያለ ነው:; ሊደመጥ ይገባል :: ቀጣዩ ምዕራፍ ቀላል አይደለምና:: ጆሮ ያለው ይስማ አይምዕሮ ያለው ያስተውል!
እግዚያብሄር መፍትሄውን ያድለን!
Filed in: Amharic