>
5:13 pm - Tuesday April 19, 6895

የ"ኦሮማራ"ነገር፡- " አንዱን ጥሎ፤ሌላውን አንጠልጥሎ" እንዳይሆን!?!  (ቹቹ አለባቸው)

የ”ኦሮማራ”ነገር፡- ” አንዱን ጥሎ፤ሌላውን አንጠልጥሎ” እንዳይሆን!?!
ቹቹ አለባቸው
*  “ከኦሮ-ማራ” ጽንሰ ሃሳብ አንጻር፤ የአግላይነት ባህሪ እንዳይላበስ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡ የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት እና፤ አንድነት ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት እጅግ የሚደገፍና የሚበረታታ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ሃሳብ በጥንቃቄ ካልተያዘ በስተቀር፤ በሌሎች ብሄረሰቦች ላይ የሚፈጥረው የአግላይነት ስሜት በቀላሉ የሚታይ አይደለም!!
*
1. መንደርደሪያ፡-
ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ አዳዲስ ሃሳቦችን እየተለማመድን ነው፡፡ ከነዚህ አደዲስ ሃሳቦች መካከል፤”ኦሮ-ማራ” እና “መደመር ” የሚሉት ጽንሰ ሃሳቦች ዋና ዋና ዎቹ ናቸው፡፡ኦሮ-ማራ ፤ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ቀደም ብሎ የተጀመረ ነገር ሲሆን፤መደመር የሚለው ሃሳብ ደግሞ የሰውየውን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ፤የመጣ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ በነገራችን ላይ፤ እኔ በግሌ የሁለቱም ፤ጽንሰ ሃሳቦች ደጋፊ ነኝ፤ይሄንን እምነቴንም ካሁን በፊት፤ በተለያየ መልኩ ገልጫለሁ፡፡
የእነዚህን ጽንሰ-ሃሳቦች ወደ መድረክ መምጣት ተከትሎ፤በድጋፍም ሆነ ፤በተቃውሞ ሃሳቦች መንሸራሸር፤ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ በእኔ እምነት፤አንድ አዲስ ሃሳብ እንዲህ ወደ መድረክ ሲመጣ፤ የልዩነት ሃሳብ መስተናገዱ ክፉ ነው አልልም፤ አደጋ የሚሆነው፤ ሃሳቡን እንዳለ መቀበል፤ወይም እንዳለ መቃወም መፈለግ የታየ እንደሆነ ነው፡፡ሃሳቡ በድጋፍም ሆነ፤በተቃውሞ የሚገለጽ ከሆነ እጅግ ጠቃሚ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ ስለሆነም፤መደመርን ሆነ፤ ” ኦሮማራ”  የሚሉትን ሃሳቦች፤መደገፍም ሆነ መቃወም፤ጤኛ አመለካት እንጅ፤ ጎጅና ወንጀል ተደርጎ መታየት የለበትም እላለሁ፡፡ ጎጅ ሆኖ የሚገኘው፤አንዱ ወገን፤የኔን ብቻ ስማ ፤ያንተው ሃሳብ ትክክል አይደለም፤የሚል ለ”ያዥና ገራዥ” የሚያስቸግር  አመለካከት ይዞ የመጣ እንደሆነ ነው፡፡ መሆን ያለበት፤ “ኦሮማራ” እና ” መደመር “የሚሉት ሃሳቦች፤ጠቃሚ ናቸው ብሎ የሚያምን ሰው ማሳመኛ ነጥቦቹን፤እንዲሁም እነዚህ ሃሳቦች ጠቃሚ አይደሉም ብሎ የሚያምን ወገን ደግሞ፤እንዴት እንደማይጠቅሙ፤ ውሀ የሚቋጥሩ ሃሳቦችን በማንሳት ሌላውን ወገን ለማሳመን መሞከር አለበት፡፡ ዝም ብሎ በድፍኑ፤እነዚህን ሁለት ሃሳቦች መደገፍም ሆነ፤መቃወም፤የትም አያደርስም፤ነገርም ከልኩ አያልፍም፡፡
በዛሬዋ፤የተመጠነች፤ አርቲክሌ፤በጉዳዩ ላይ( ኦሮማራ) ያለኝን፤ የግል አስተያየት እሰነዝራለሁ፡፡ጉዳዩን ከብዙ አቅጣጫ የተመለከትኩት ሲሆን፤ከአማራ ህዝብ ጥቅም አንጻርም ለመመልከት ሞክሪያለሁ፡፡
2. “ኦሮማራ” ጥንቃቄ የሚሻው ጽንሰ ሃሳብ ነው፡-
እንዲሁ በግላጭ ሃሳቡን ለሚመለከተው ሰው፤ኦሮማራ የሚለው ሃሳብ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው ብሎ መደምደሙ አይቀርም፡፡ በርግጥ ጽንሰ-ሳቡ በእውነተኛ መርህ የሚመራና፤እውነተኛ መሪ ካገኘ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡በተለይም ይሄ ሃሳብ፤ከፓርቲ አመራሮች ግንኙነት ወረድ ብሎ፤ ወደ ህዝብ ለህዝብ የሚወርድ ከሆነ፤ አስፈላጊነቱ ወደር የለውም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ፤ይሄ አባባል፤ ለይስሙላና፤ለፓርቲ መሪዎች ወዳጅነት ማጥበቂያነት ብቻ የሚውል ከሆነ ደግሞ፤እጅግ አደገኛ መሆኑ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም፤የመሪዎቹ፤እውነተኛ  ፍላጎት፤የርስ በርሳቸውን ወዳጅነት በማጠናከር፤ስልጣን እድሚያቸውን ለማደላደል ከሆነ፤ፋይዳ የለውም፡፡ ስለሆነም እውነተኛ “የኦሮማራ”ግንኙነት ሊገነባ ከሆነ፤ግንኙነቱ፤  በኦሮሞና አማራ ህዝቦች መካከል በሚገለጽ እውነተኛ ግንኙነት ላይ እንጅ፤በመሪዎች ሰፈር ታጥሮ በሚቀር ወግ መሆን የለበትም ማለት ነው፡፡
ሌላውም  “ከኦሮ-ማራ” ጽንሰ ሃሳብ አንጻር፤ አንድ ሌላ መሰረታዊ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነገር አለ ብየ አምናለሁ ፡፡ ይሄውም፤ ይሄ ጽንሰ ሃሳብ የአግላይነት ባህሪ እንዳይላበስ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ እውነት ነው፤ ኦሮሞና አማራ የዝችን አገር፤ ከ70- 75% የህዝብ ሽፋን፤ እንዲሁም አብዛኛውን የሀገሪቱ የቆዳ/ የመሬት ሽፋን፤ እንደሚወክሉ ታውቆ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም፤የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት እና፤ አንድነት ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት እጅግ የሚደገፍና የሚበረታታ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ሃሳብ በጥንቃቄ ካልተያዘ በስተቀር፤ አፍራሽ የሆነ ሚናም ሊኖረው ይችላል፡፡ለምሳሌ፤ ይሄ ሃሳብ ፤በሌሎች ህዝቦቻችን( ከኦሮሞና አማራ ውጭ) ዘንድ፤ እንዴት ይታያል? በበጎ ጎኑ? ወይስ በስጋት? ይሄ ጉዳይ በሚገባ መጤን አለበት፡፡ ስለሆነም፤እኛ  “ኦሮማራ” ስንለል፤ሌሎቹ ህዝቦች፤የመገለል ስሜት ሊያድርባቸው አይገባም፡፡ ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን የ”ኦሮማራን” ግንኑነት፤ አንድም  በበጎ እንዲመለከቱት  ማድረግ፤ ያለበለዝያም የሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መድረኩን ማመቻቸት ይገባል፡፡ ከ25-30 % የሚሆንን ህዝብ አግለህ፤በሁለቱ ታላለቅ ህዝቦች መካከል ብቻ የሚካሄድ የወንድማማችነት ጨዋታ፤ ለዘላቂ ሰላም አያግዝም፤ሁሉንም ደስተኛ ያደረገ ስርአት በመገንባት በኩልም፤ሚናው ደካማ ይሆናል፡፡
ስለዚህ ጉዳይ ፤ በቅርቡ ፤ Miky Amhara  የተባለ  አንድ አማራዊ አክቲቢስትና፤የፖለቲኮ-ኢኮነሚ ተንታኝ፤ በሚገባ ሂዶበት ተመልክቸዋለሁ፡፡ በተለይም፤ይሄንን አርቲክል ያነበበ ሰው፤ “ኦሮማራ” የሚለው ጽንሰ ሃሰብ በጥንቃቄ ካልተያዘ በስተቀር፤ የሚኖረውን የአግላይነት ሚና ጥሩ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ፤ልጁ በስፋት ስለሄደበት፤እኔ ሱን ሃሳብ መድገም አይኖርብኝም፡፡ በአጠቃላይ ግን፤ከ Miky Amhara ትንታኔ፤ መረዳት እንደምንችለው፤”ኦሮማራ” የሚለው ሃሳብ፤ በጥንቃቄ ካልተያዘና፤ግንኙነተቱም፤ ከመሪዎች ወርዶ፤ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ ካልተመሰረተ በስተቀር፤ነገሩ ሌላና አላስፈላጊ ውጤት ሊያስከትል የሚችል መሆንኑ ነው፡፡
3. የ”ኦሮማራ” ግንኙነት፡- ከአማራ ህዝብ አንጻር፡-
አንዳንድ ሰዎች፤ስለ አማራ ህዝብ ሲያወሩ፤(ብዙዎቹን በዚህ የማልከሳቸው ብሆንም)ነጥባቸው በአማራ ክልል ውስጥ ስለሚኖረው ህዝብ ብቻ እንጅ፤ከክልሉ ውጭ ስለሚኖረው የአማራ ህዝብ ጉዳይ ትዝ አይላቸውም፡፡ስለሆነም፤አፋቸው እንዳመጣ፤ የሚባለውንም፤ የማይባለውንም፤ በሆድ ብቻ ሚያዘውንም፤ብቻ ሁሉን ነገር አውጥተው ሜዳ ላይ ይዘረግፉታል፡፡ እነሱ የሚናገሯት እያንዳንዷ ቃል፤በአጠቃላይ በአማራ ህዝብ ላይ በተለይም፤ከክልሉ ውጭ እንደሚኖር በሚገመተው በአስራዎቹ ሚሊን በሚቆጠረው የአማራ ህዝብ ላይ፤ሊያስከትከው የሚችለውን አወንታዊና አሉታዊ ሚና መመዘን ላይ ሲሳናቸው አያለሁ፡፡
በእኔ እምነት፤ይሄ አካሂያድ፤በፍጥነት ልናርመው የሚገባ መሰረታዊ ችግራችን ነው ብየ አምናለሁ፡፡ ስለ አማራ ጉዳይ ስናነሳ፤ሁሌም መዘንጋት የሌለብን  አንድ መሰረታዊ ነገር ፤ከክልሉ ውጭ   ሰለሚኖረው አማራ ሁኔታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ፤እጅግ ሲበዛ በጥንቃቄ መራመድ ካለበት፡ አማራ ቀዳሚውን መውሰድ አለበት ባይ ነኝ፡፡ እኛ አማራዎች የምንጨነቀው፤አማራ ክልል ውስጥ ስለሚኖረው አማራ ብቻ አይደለም፤በመላ ኢትዮጵያ ተሰራጭቶ ስለሚኖረው አማራ ጭምር እንጅ፡፡ ስለሆነም፤የኛ ነገር “የመንታ እናት ተንጋላ ሞተች” እንደሚሉት አባባል መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ይሄም ማለት፤ከዚህ፡ በክልሉ ውስጥ የሚኖረው የአማራ ህዝብ ጥያቄ አለ፤ወዲያ ማዶ ደግሞ፤ ደህንነታቸው ሁሌም የሚያሳስበን፤በሚሊየን የሚቆጠሩ አማራዎች አሉ፡፡
 በግልጽ አንነጋገር፤አንዳንዴ፤በህልውናችን ላይ አደጋ እስካልደቀኑ ጊዜ ድረስ፤ የሚያስከፉ ነገሮች ቢያጋጥሙንም እንኳን፤ከክልላችን ውጭ ያሉ ወገኖቻችንን በማሰብ፤አንዳንድ ነገሮችን አይተን እንዳላየን፤ሰምተን እንዳልሰማን፤ሆነን የምናልፋቸው ጉዳዮች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት፤በኢትዮጵያ ፖለቲካ፤በተለይም ለአማራ፤በዚህ መርህ መመራት ምርጫ የሌለው፤አማራጭ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር፤ ዘራፍ ብለን ስለጮክን ብቻ፤ከክልላችን ውጭ ለሚኖሩ ወገኖቻችን ፤ችግርና ስቃይ በወቅቱ እንደርስላቸዋለን ማለት አይደለም፡፡ ከነችግሩም ቢሆን ፈጥኖ የሚደርስላቸው፤እዛው ያለው አስተዳደርና ማህበረሰብ ነው፡፡
ስለሆነም፤ስለ አማራ እንዳጠቃላይ፤በተለይም ደግሞ፤ከክልላችን ውጭ ለሚኖረው አማራ፤”ኦሮማራ” ሃሳብ በተገቢው ከተመራና፤እውነተኛ መሪ ካገኘ፤”ኦሮማራ” የሚለው ጽንሰ-ሰብ ጠቃሚ እንጅ ጎጅነቱ አይታየኝም፡፡ ጎጅ ነው ብሎ የሚመክረኝ ወንድም/እህት ካለና፤በሳይንሳዊ ትንታኔ ላይ ተመስርቶ ሊያስረዳኝ ከቻለ፤እኔ በበኩሌ ለመረዳት ሲበዛ ዝግጁ ነኝ፡፡ ዝም ብሎ ለመቃወም ብቻ ሲባል፤”ኦሮማራ” ለአማራ አይጠቅመውም፤ሃሳቡ አማራን “ለማደንዘዝ” ሆን ተብሎ የተቀየሰ ስልት ነው፤የሚባለው አባባል፤ ለእኔም አንድ ፊደል እንደቆጠረ ሰው፤እንዳለ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡
4. ለመሆኑ  የአማራ ብሄርተኝነት አላማና ግቡ ምንድን ነው?
በዚህ አጀንዳና ነጥብ ዙሪያ መግባባት ላይ ደርሰን ይሆን? በእኔ እምነት፤የአማራ ብሄርተኝነት ሊመራበት ይገባቸዋል ብየ ከማምንባቸው መርሆዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ፤የአማራ ብሄርተኝነት፤ ለኢትዮጵያ አንድነት፡ የሚለው መርሆ  ዋነኛው ነገር ነው፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ፤ የአማራ ብሄርተኝነት፤ከሌሎች ብሄሮች፤ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ለሚኖር ግንኙነት ልዩ ትኩረት ይሰጣል ማለት ነው፡፡ ታድያ በዚህ መርህ ላይ ከተግባባን፤ “ኦሮማራ”  የሚለውን ሃሳብ እንዴት ልንቃወመው እንችላለን፡፡
በዚህ በኩል፤ቅሬታ ያላቸውን ወገኖች ስሜት ተረድቸዋለሁ፡፡ ዋኘናው መነሻቸው፤በኦሮሞዎች ዘንድ( በተለይም ኦነጋዊያን ዘንድ)፤በአማራ ህዝብ ላይ ሲነዛ የኖረው፤የውሸት ታሪክ ሳይታረም ፤”ኦሮማራ” የሚለው ነገር ውጤታማ አይሆንም  የሚል ነው፡፡ከዚህም በተጨማሪ፤ዛሬም ድረስ ኦሮሚያ ውስጥ፤አማራ እተፈናቀለ፤”ኦሮማራ” ማለት፤አማራን ለማደንዘዝ ካልሆነ በስተቀር፤ ማይሰራ  አባባል ነው የሚል ነው፡፡
ይገርማል፡፡ እውነት ነው ነገሮችንና የኦሮሞን ሰፊ ህዝብ ፤ከኦነግና ከአምስቱ  የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች አንጻር ብቻ፤ ካየነው እኔም ስጋቱን እጋራለሁ፡፡ ነገር ግን ኦነግና መሰሎቹ ከአቋማችን ፍንክች አንልም ቢሉን፤ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ወዳጅነት መፍጠር የለብንም ማለት ነው? ነው ወይስ፡ የኦሮሞ ህዝብና ኦነግ አንድና ያው ናቸው ልንል ነው? በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ይሄን ጉዳይ በቅንነት መመልከት ለፈለገ ሁሉ፤ኦቦ ለማ የወሰዱትን  ታሪካዊ አቋም ብቻ በመመልከት፤የ”ኦሮማራ”ን ሃሳብ መደገፍ ይቻላል፡፡ ኦቦ ለማና ቲማቸው ናቸው እኮ ፤በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፤በዝች አገር፤” የብሄር ጭቆና አልነበረም፤ዛሬም የለም” ብለው፤በአደባባይ በመናገር፤በአማራ ህዝብ ላይ ከ50 አመታ በላይ ሲሰበክ የኖረውን የውሸት ትርክት አፈር ድሜ ያበሉት፡፡
ቢያንስ ይሄ ይረሳል? ይሄን ድፍረት የተሞላበት አቋም እኮ፤የኛው አማራዊ ድርጅት ብአዴን /አዴፓ፤ እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ፤ አማራ እንደ ብሄር “ጨቋኝ” ነበር ብየ መታገሌ፤ ስህተት ነበርኩ ብሎ በይፋ መግለጫ አልሰጠም፡፡ በኦቦ ለማ ና ዶ/ር አብይ የሚመራው ኦህዴድ/ኦዴፓ ግን ይህን ታሪካዊ አቋም ወስዷል፡፡ ስለዚህ ፤ስለ ኦሮሞና አማራ ህዝቦች ግንኙነት ስናስብ፤ሁሌም ማሰብ ያለብን፤ስለ ኦነግንና መሰሎቹ የተበላሸ ነገር ብቻ ሳይሆን፤ ስለ ኦቦ ለማና ዶ/ር አብይ ቲም ጭምር መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ እንደዛ ካልሆነ፤ የወዳጆቻችን ቁጥር እየቀነሰ፤የሚጠሉን ኃይሎች ቁጥር ደግሞ እየተበራከተ መሄዱን ልብ ማለት ይገባል፡፡ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሌም ማስተዋስ ያለብን፡ አንድ የማይታለፍ ትልቅ  ቁም ነገር አለ: ይሄዉም “ወዳጅን የማብዛትና ጠላትን መቀነስ” የሚል መርህ ነው፤ ይሄ መርህ ቋሚ ሊሆን ይገባል፡፡
ለሁሉም፤ነገ በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ፤ በተለይም በጎንደር ከተማ በሚካሄደው ሰልፍ ላይ፤ የሚስተጋቡት ሞፈክረች ደርሰውኝ ተመልክቻቸዋለሁ፡፡ ብዙዎቹ ጥሩ ናቸው፡፡ በተለይም የ”ኦሮማራ” ን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል፤ሞፈክር በአማርኛና በኦሮምኛ ተጽፎ ስመለከት፤በ2008 ዓ.ም የጎንደር ህዝብ ” የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው!” በማለት ያስተጋባውን ድምጽ አስታወሰኝ፡፡
በቃ፤   ከእንግዲህ በኃላ ስለ “ኦሮማራ” ስናስብ፤ ኦቦ ለማንና ዶ/ር አብይን፤እንዲሁም ድርጅታቸውን (ኦዴፓን)  እያሰብን እንጅ፤ ኦነግንና አምስቱን የኦሮሞ ድርጅቶች እያሰብን መሆን የለበትም፡፡ ኦነግንና እነዚህን ድርጅቶች እያሰብን ፤የ”ኦሮማራ”ን ነገር ካሰብን ነገር ተበላሸ፡፡
Filed in: Amharic