>
5:13 pm - Saturday April 18, 5131

“ቅንጅት” ዳግም ይወለድ (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

“ቅንጅት” ዳግም ይወለድ

 

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

 

ግሩምና ድንቅ የሆነ አማራጭ የኢትዮጵያ ፓርቲ እንዲወለድ እስካሁን የሚታይ አንድ ምዕራፍ ፈቀቅ አለመባሉ ያሳዝናል።  ተስፋ በተቆረጠበት ወቅት ላይ ቆመን ሳለን፥ ዶ/ር አብይ ብቅ ብለው ላለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ተአምር አሳዩን። ዛሬ ደግሞ ይህንን ለውጥ ዳር የሚያደርስ አደራ ተቀባይ ፓርቲ ጠፍቶ፥ በስጋት ጨለማ ባለንበት በአሁኑ ሰዓት፥ ብርሃን የሚፈነጥቅ ባለ አደራ ታሪካዊ ፓርቲ ተቀናጅቶ በምድራችን ብቅ ብሎ የሚያስገርመን መቼ ነው?  በድህረ ዶ/ር አብይ ጊዜ መሠራት ያለበትን ሥራ፥ ዛሬ ዶ/ር አብይ ካልሰሩ ብሎ ከማዋከብ፥ ዓይናችንን ከእርሳቸው ላይ እናንሣና ወደ የራሳችን ስራ እንግባ።

ዶ/ር አብይ ለሁላችንም ዲሞክራሲን አዋልደው፥ ፈረሱም ይሄው ሜዳውም ይሄው ከማለት ያለፈ ሃላፊነት የለባቸውም።  ምክንያቱም ፓርቲያቸው ሊሰራው የሚችለው ዕጣና ፈንታው ሽግግር መሆን ብቻ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው ፓርቲያቸው ሲጀመርም ለተስፋይቷ ኢትዮጵያ እንዲመጥን ተደርጎ ስላልተሰፋ ነው።  በዚህ ምክንያት ትልቁ አንገብጋቢ ቁምነገር አንድ ብቻ ነው። ያም ዲሞክራሲ ኢትዮጵያን ሲያሻግር፥ የተስፋይቷ ኢትዮጵያ አደራ ተቀባይ የሚሆን ተቀናጅቶ የጊዜው ፓርቲ ለመሆን የሚችል መገኘቱ ነው።

ዶ/ር አብይ አህመድ የዲሞክራሲ አዋላጅ ለመሆን ታሪክ የጠራቸው ሰው ናቸው።  ያንን ጥሪያቸውን ከብቃት በላይ በመወጣት ላይ ይገኛሉ። ያመጡትን ዲሞክራሲ ተጠቃሚ እየሆንን፥ ነገር ግን በዚህ ዲሞክራሲ ምክንያት የሚከሰተውን ውጣ ውረድ እንደ እርሳቸው ድካምና ችግር መቁጠር ነውር ነው።  ዲሞክራሲና ነፃነትን ማስተናገድ መቻላችንን ማሳየት የሁላችንም ሃላፊነት ነው። የማያግባቡን ነገሮች ቢበዙም፥ በሥራ የሚተገበረው ሀሳብ፥ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዳኝነት የሚመረጥ ስለሆነ ዲሞክራሲ ፍቱን መፍትሄ ነው።  ያም ሆን ይህ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዲሞክራሲ እየደመቀ ይሄዳል እንጂ አይደበዝዝም። ምክንያቱም የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጠባቂ ከአምላክ በታች የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ስለሆነ ነው።

ተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ዶ/ር አብይ የተጫነባቸው ዓይነት የኢህአዴግ ቀንበር የለባቸውም።  በዚህም ምክንያት ለተስፋይቷ ኢትዮጵያ ለመታጨት ነፃ ናቸው። ነገር ግን የኢህአዴግን አጀንዳ እያራመዱ ከኢህአዴግ የተሻለ ፓርቲ ነኝ ብሎ መንቀሳቀስ ከእውነት ስለሚርቅ አይጠቅምም።  ከኢህአዴግ የተሻለ ፓርቲ ለመሆን ዜግነትን አማክሎ መነሳት ይጠይቃል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ በይዘትም ሆነ በህልውና ልዩና የላቁ መሆን አለባቸው። ለአሮጌ አስተሳሰብ ያረጀው ፓርቲ ምናለና።

ዶ/ር አብይ የዲሞክራሲ መንገዱን በትጋት እየጠረጉ የራሳቸውን ሃላፊነት እየተወጡ ይገኛል።  ለዚህም የውጭ ሀገር ዜና ሳይቀር በማድነቅ ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ ሀገራችን ደግሞ በመንገዱ ላይ የሚሄድ አማራጭ የኢትዮጵያ ፓርቲ ባቡር በመጠበቅ ላይ ትገኛለች።  ጥያቄው ሌሎቻችን “ቅንጅት” ዳግም እንዲወለድ ምን ያህል ድርሻችንን እየተወጣን ነው?

 

ፈጣሪ ይርዳን!

 

ኢሜል፡   Z@myEthiopia.com

Filed in: Amharic