>

"ከሞኝ ደጃፍ ነዳጅ ይቀዳል! ብረቱም ሲሚንቶውም ይጋዛል!  (ዘመድኩን በቀለ)

“ከሞኝ ደጃፍ ነዳጅ ይቀዳል! ብረቱም ሲሚንቶውም ይጋዛል! 
ዘመድኩን በቀለ
* ጠቅላያችን ከብልጧ ጎረቤታችን ከኤርትራ ጋር ያደረጉት ግብታዊና የተጣደፈ፣ የተንቀዠቀዠ፣ የተዋከበ፣ የተካለበ፣ የፈጠነ፣ ውሉ የማይታወቅ፣ ውሉም የማይታይ፣ ውልና ስምምነት አሁን የከፋ ጉዳትና ዋጋም ማስከፈል ለመጀመር በዋዜማ ላይ ይገኛል!
~ እንደኔ እንደእኔ ” ኤርትራ ” አራዳ አራዳ ከምትጫወት አንድፊቱኑ ወደ እናት ሀገሯ ብትመለስ ይሻላት ይመስለኛል። የሚሻላትም እሱ ነው። እናቷን ክዳ ጎጆ ከወጣች በኋላ የምን አሁንም ከካደቻት እናቷ ቤት ሽሮና በርበሬ መለመን?  ኧረ ምንሼ ነው? አሉ ዶሮማነቂያዎች። ኢንዴዢያ ነው።
~ ይሄን ዜና ሰምተው አንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች “ዐቢቹአችን” ጉድ ሳይሠራን አይቀርም በማለት እንዳይነበጫበጩብኝም እሰጋለሁ።
~ የሞኟ ሀገራችን የላሜ ቦራዋና የጥገት ላሟ ኢትዮጵያችን መሪ የሆኑት የተከበሩ ክቡር ጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ ከብልጧ ጎረቤታችን ከአራዳልጇ የኤርትራ መሪ ከሆኑት ከአይተ ኢሳይያስ አፈውርቂ ጋር ያደረጉት ግብታዊና የተጣደፈ፣ የተንቀዠቀዠ፣ የተዋከበ፣ የተካለበ፣ የፈጠነ፣ ውሉ የማይታወቅ፣ ውሉም የማይታይ፣ ውልና ስምምነት አሁን የከፋ ጉዳትና ዋጋም ማስከፈል ለመጀመር በዋዜማ ላይ ይገኛል እየተባለ ነው። ምልክቶችም እየታዩም ነው።
~ ላሜ ቦራዋ ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያውያኑ የትግሬ ቦለጢቀኞች 24/7 ስትታለብ መክረሟ ይታወቃል። የትግራይ ቦለጢቀኞች የነበራቸውን ገደብ የለሽ ሥልጣን ተጠቅመው የስኳር፣ የግድብ፣ የማዳበሪያና የብድር ብር ሳይቀር ሙጥጥ አድርገው ሲያበቁ ትግራይ በፋብሪካና በኢንዱስትሪ እስክትሰምጥ ድረስ መገንባታቸውም ይታወቃል። እነ በረከት ስምኦን እንኳ  ” እኛ በተሰጠን በጀት መጠቀም ስላልቻልን የተሻለ የአፈጻጸም ብቃት ላላት ትግራይ በጀቱ ይተላለፍላት” በማለት የዐማራን በጀት ለትግራይ ሲያዞሩት መክረማቸውም ይታወቃል። እናም ከዚህ የተነሳ ዐማራ ጨለማ ውጦት ዳዋ ለብሶ ከርሟል። ኦሮሞም እንደዚያው ሌሎችም እንደዚያው።
~ አሁን ደግሞ ኤርትራውያኑ ትግሬዎች ባለተራዎቹ እኛ ነን ያሉ ይመስላሉ። በለፉት 20 ዓመታት ስለተጎዳን እስክናገግም ኢትዮጵያን እንጋጣት የሚል አቋም ይዘው ላሜ ቦራዋን ኢትዮጵያችንን መጋጥ መጀመራቸው እየተነገረ ነው።
~ ዕደለ ቢሷና ምስጋና ቢሷ ላሜ ቦራዋ ኢትዮጵያችን አሁን ደግሞ በአፈ ቅቤው ጠሚያችን በዶኮ ዐቢይ አህመድ መሪነት ለሌላ የተራበች በላተኛ ሚጢጢ ሀገር ተላልፋ የተሰጠች ይመስላል።
~ ላሜ ቦራዋ ኢትዮጵያችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሐገር ቤት የምታስገባውን ነዳጅ የበዙ የኤርትራ መኪኖች ድንበር እያቋረጡ መጥተው ከሀገራቸው ውጪ ሌላ ሰው እንኳ በማያውቀው ዋጋው ከነጭ ወረቀት እኩል በሆነና ናቅፋ የሚል ስያሜ በተሰጠው ገንዘብ እንደልብ እየቀዱ ወደ ኤርትራ ይመለሳሉ የሚል ዜና ወጥቷል።
~ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ጣውላም በገፍ ወደ ኤርትራ እየተጋዘ መሆኑም እየተነገረ ነው። ኤርትራውያኑ መጀመሪያ አካባቢ የትግራይ ነጋዴዎችን ዕቃ ለመውረስ ሞክረው የነበረ ሲሆን ኋላ ላይ ግን ሲያስቡት ቤታቸው ድረስ በስሎ ገበታቸው ላይ የቀረበላቸውን ምግብ እንደመግፋት ቆጥረው ነው መሰል ነገሩ ችላ ብለው እንደውም ባለ በሌለ ኃይል የኢትዮጵያን ምርት ወደ ኤርትራ በገፍ ማስገባቱን ተያይዘውታል።
~ በዐማራ ክልል በባህርዳር ነዳጅ የለም። በትግራይ አንዳንድ ከተሞችም የነዳጅ እጥረት መኖሩ እየታየ ነው። ኤርትራውያኑ ከፈረቃ መኪና ማሽከርከር ወጥተው አሁን በሰላም እንደልባቸው በዶላር መጥቶ በናቅፋ እየሸመቱ በየጎዳናው ሽር ብትን ይሉበታል። በአንጻሩ ባህርዳር ጎዳናዎች ተሰድረው የሚውሉት መኪኖችና ባጃጆች ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉ ወይም ሰርግ አጅበው ትርኢት የሚያሳዩ እንዳይመስልዎ፤ ነዳጅ አጥተው የቆሙ እንጂ።
 የዐማራ ህዝብ ግብርና ታክስ ይከፍላል። ያውም በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛው ገባሪ ዐማራው ነው። እናም በዐማራው ግብር ተገዝቶ የሚመጣው ነዳጅ ግን መንገድ ላይ ይጠለፋል። አራዳ አራዳ የሚጫወቱት ዐቢቹና ኢሱ ይሄን ነዳጅ ኤርትራውያኑ በናቅፋ እንዲሸምቱት ይደረግና ዐማራ ነዳጅም፣ ወፍጮም፣ መብራትም ኢንጂሩ ይሆናል።
ከዚያ ማለቃቀስ ነው። አከተመ።
~ የትግራይ ክልል መንግሥትም ከምር አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ነገርየውን እንዳይቃወም ” የለውጥ አደናቃፊና የቀን ጅብ” የሚል ስም እንዳይሰጠው ይሰጋል። ፍጥጥ ብሎ ቢቃወም ድግሞ አሁን ከዐማራ ወንድሞቹ ጋር ሊገባበት ለሚያስበው ጦርነት ከወደ ኤርትራ በኩል ድጋፍ እንዳያጣ በማሰብ አንጀቱ እያረረ ምንም ማድረግ ባለመቻሉ በዶላር ተገዝቶ የመጣ ነዳጅ በናቅፋ እየቸረቸረ አንጀቱም እርር እያለ ጮጋ ብሎ ይመለከታል።
~ እነ ጤፍ፣ እነ ቡና፣ ስንዴ፣ አተር፣ ምስር፣ በቆሎና ቅመማቅመም ሁሉ ኤርትራ እየከተሙ ነው። ምንአልባትም በቅርቡ ኤርትራ በዓለም የቡና ላኪዎች ሰንጠረዥ ውስጥ ቶፕ ቴን ሳትገባ አትቀርም እየተባለ ነው። ኢትዮጵያውያን ከኤርትራ የሚያስገቡት ነገር የለም። ገንዘብ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ምጽዋና አስመራ ሄደው ዶላራቸውን ሆጭ አድርገው በውኃ ተንቦራጭቀው ይመለሳሉ። እና ታዲያ ከኤርትራ ምን ይዘው እንዲመጡ ኖሯል የሚል እኮ አይጠፋም። እና እኔስ ምን ይዘው ይምጡ አልኩ። አይ ላሜ ቦራዬ ያልታደልሽ ሀገር።
~ የሚገርመው ኢትዮጵያና ኤርትራ ሲታረቁ የተስማሙት በምን በምን ጉዳይ ላይ እንደሆነ የሚያሳይ የውል ስምምነት ሰነድ እስከ አሁን ለሁለቱም ሀገር ህዝቦች በይፋ አልቀረበም። ቀርቦም ጥቅምና ጉዳቱ ታይቶ አልተተቸም።
~ አሁን እየሰማን ያለነው ነገር ግን እጅግ መረን የለቀቀ ግኑኝነትና ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል እንዳለ የሚጠቁሙ ነገሮች እየታዩ መምጣታቸው እተነገረ ነው።
~ አሁን እኔን ከነዳጅና ጤፉ በላይ የሚያስፈራኝ የኤርትራውያኑ የድንበር መከፈቱን ተከትሎ ልክ እንደ አንበጣና ተምች ወደ ኢትዮጵያ ግርር ብለው መግባትና  በመላ ሀገሪቱ በተለይም አዲስአበባ ላይ ሰፍረው መታየት ነው። ወደፊት ይሄ ነገር ሌላ ዙር ጦርነትና ትርምስ ላለመፈጠሩ ምንም ዋስትና የለም።
ዛሬ ጦማሬን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን ሪሚኪስ በማድረግ በዘፈን ነው መቋጨት የማረኝ። ያዝ እንግዲህ ማነህ ባለማሲንቆ ተቀበልልኝማ !
ድሮም !
ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም፣
ፍቅሬ ፍቅር በዝቷል፣
ዐቢይ ዐቢይ በዝቷል፣
ኢሱ ኢሱ በዝቷል፣
ሻአቢያ ሸአቢያ በዝቷል፣
ዶላር ዶላር በዝቷል፣
ዐረብ ዐረብ በዝቷል፣
ነዳጅ ነዳጅ በዝቷል እኔ አለማረኝም።
ሻሎም !  ሰላም !
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ጥቅምት 16/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic