>

የጀኔራል መንግስቱ ነዋይ ትንቢታዊ ይዘት ያለው ታሪካዊ ንግግር!!!

የጀኔራል መንግስቱ ነዋይ ትንቢታዊ ይዘት ያለው ታሪካዊ ንግግር!!! መጋቢት 19፣ 1953 ዓ.ም 
አበጋዝ ዘ እንጀቶ
በታህሳስ 3፣ 1953ቱ በመምሬ ነዋይ ልጆች በገርማሜ እና መንግስቱ ነዋይ ጠንሳሽነት ተካሂዶ በከሸፈው የመንፈቅለ መንግስት ሙከራ በህይወት ተርፈው ለፍርድ የቀረቡት ጀኔራል መንግስቱ ነዋይ: መጋቢት 19፣ 1953 ዓ.ም የሞት ፍርድ ከተወሰነባቸው በኋላ የተናገሩት ታሪካዊ ንግግር።.
እናንት ዳኞች የበየናችሁብኝን የሞት ፍርድ ያለ ይግባኝ ተቀብያለሁ፡፡ ይግባኝ ብየ ጉዳየን የሚመለከትልኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ቢሆን ኖሮ ይግባኝ ማለት በፈለግሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ እንደማይሆን አውቃለውና በይግባኝ የአፄ ኃ/ስላሴን ፊት ማየት አልፈቅድም፡፡
 በእግዚያብሄር ስም ተሰይማችሁ ከተቀመጣችሁበት የፍርድ ወንበር ላይ ከመቀመጣችሁ በፊት በእኔ ላይ የምትሰጡትን የዛሬውን ፍርድ ታውቁት እንደነበር ሳስብና ፍርድ እስከዚህ መርከሱን ስታዘብ ሀዘኔ ይበዛል፡፡.
ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት፣ ነፃነትና እርምጃ የተነሳሁ ወዳጅ ነኝ እንጅ ለማፋጀት የተነሳሁ ወንበዴ አይደለሁም፡፡ ይህንን ማድረግ ፈልጌ ቢሆን ኖሮ ማንም የማይወዳደረው ሰራዊትና መሳሪያ ሳላጣ ዛሬ እዚህ ከእናንተ ፊት ለመቆም ባልበቃሁ ነበር፡፡
 .እኔ ከየአፄ ኃ/ስላሴ ድንክ ውሾች ያነሰ ደመወዝ የሚያገኙ ሁለት የተራቡ ወታደሮችን አጣልቼ ለማደባደብና አገር ለማፍረስ አለመምጣቴን የሚያረጋግጥልኝ እናንተ በትዕዛዝ ያገኛችሁትን ፍርድ ለመቀበል እዚህ መቆሜ ነው፡፡ ከእኔ በፊት በግፍ የፈሰሰው ንፁህ የኢትዮጵያዊያን ደም ብዙ ነው፡፡
 .በየአፄ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት ግፍ ሽልማት በመሆኑ እኔ ለመሞት የመጀመሪያው ሰው አልሆንም፡፡ ስልጣን አላፊ ነው፡፡ እናንተ ዛሬ ከጨበጣችሁት የበለጠ ስልጣን ነበረኝ፡፡ ሀብትም አላጣሁም፡፡ ነገር ግን ህዝብ የሚበደልበት ስልጣንና ድሃ የማይካፈለው ሀብት ስላልፈለግሁ ሁሉንም ንቄ ተነሳሁ፡፡
.አሁንም እሞታለሁ፡፡ ሰው ሞትን ይሸሻል፡፡ እኔ ግን በደስታ ወደሞት እሄዳለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅነት ቀድመውኝ መስዋዕት የሆኑትን አብረውኝ ተነስተው የነበሩትን ጀግኖች ወንድሞቼን ለመገናኝት ናፍቄአለሁ፡፡ የጀመርኩት ስራ ቀላል አይደለም፡፡
.አልተሸነፍኩም፡፡ ወገኔ የሆነው ድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመርኩለትን ስራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፈፅሞ ራሱን በራሱ እንደሚጠቅም አልጠራጠርም፡፡ ከሁሉ በበለጠ የሚያስደስተኝ ለኢትዮጵያ ህዝብ ልሰራለት ካሰብኳቸው ስራዎች አንዱ የኢትዮጵያ ወታደር ዋጋና ክብር ከፍ ማድረግ ሲሆን ይህ ሃሳቤ ህይወቴ ከማለፉ በፊት ሲፈፀም ማየቴ ነው፡፡
 .ዛሬ መኖራችሁን በማየቴ ነገ መሞታችሁን ረስታችሁ አሜን ብላችሁ ቀናችሁን በማስተላለፍ በመገደዳችሁ በእኔ ላይ ሳትፈርዱ በራሳችሁ ላይ የፈረዳችሁ መሆናችሁን አላስተዋላችሁም፡፡ እኔ የተነሳሁት ከትክክለኛ ህግና ከህሊናችሁ ውጭ ለመፍረድ እንዳትገደዱ ለማድረግ ነበር፡፡ በአጭሩ በእኔ ላይ ለመፍረድ የቸኮላችሁትን ያህል አስር እና አስራ አምሰት ዓመት በቀጠሮ የምታጎላሉትን ህዝብ ጉዳይ እንደዚህ አፋጥናችሁ ብትመለከቱትና ብትሸኙት ኖሮ የእኔ መነሳት ባላስፈለገም ነበር፡፡ .
ከእናንተ ከዳኞቹና የሞት ፍርድ እንድትበይኑብኝ ካዘዛችሁ ሰው ይልቅ እኔ ፍርድ ተቀባይ የዛሬ ወንጀለኛ የነገ ባለታሪክ ነኝ፡፡ የኔ ከ ጓደኞቸ መካከል ለጊዜው በህይወት መቆየትና ለእናንተ ፍርድ መብቃት የመመዘኑን ፍርድ ለመጭው ትውልድ የሚያሳይ ይሆናል፡፡
 .ዋ ! ዋ ! ዋ ! ለእናንተና ለገዢአችሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚወርድባችሁ መዓት አሰቃቂ ይሆናል፡፡
 .በተለይ የአፄ ኃ/ስላሴ የግፍ መንግስት ባላደራዎች ሆነው ድሀውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገሸልጡት ከነበሩት መኮንን ሀ/ወልድና ገ/ወልድ እንግዳወርቅን ከመሳሰሉት በመንፈስ የታሰሩ በስጋ የኮሰሱ መዠገሮች መካከል ጥቂቶቹን ገለል ማድረጌን ሳስታውስና የተረፉትም ፍፃሜያቸውን በሚበድሉት በኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ላይ መውደቅ ሲሰማኝ ደስ ይለኛል፡፡…
Filed in: Amharic