>

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ!
አስተዳደራዊ እና የማንነት ጥያቄዎች በሚያነሱ ዜጎች ላይ በየትኛውም መንገድ የሚወሰድ የኃይል እርምጃ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው !!!
የአዲስ አበባ ህዝብ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ትግል ምዕራፍ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ጉልህ ሚና ያለው  የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ፣ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዲጸና እና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከተደረጉት ህዝባዊ እንቢተኝነት ጀምሮ ሰፊ ህዝባዊ ትግል ውስጥ የእራሱን አስተዋፅኦ ሲያደርግ የኖረ ሕዝብ ነው ፡፡ በዚህ ትግል ውስጥም ከህይወት መሰዋትነት ጀምሮ ይህ ቀረ የማይባል ተሣትፎ አድርጓል ፤አሁንም እያደረገም ይገኛል ፡፡ ይሁን እንጂ መሰዋትነት የከፈለው የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄያቸው በአግባቡ ተመልሶ፤ የከፈለለትን መሰዋትነት የሚመጥን ቦታ ማግኘት እንዲችል አልተደረገም ! እየተደረገም አይደለም !!!
የአዲስ አበባ ሕዝብ አምባገነን ገዢዎችን እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚሸረሽር የትኛውንም ዓይነት እንቅስቃሴ እምቢ በማለት የገታው ነገር የለም፤ወደፊትም አይኖርም !!! የአዲስ አበባ ሕዝብ የኢትዮጵያ የቋንቋ ፣የባህል ፣የታሪክ ነፃብራቅ ቢሆንም ፤ በግልፅ በአደባባይ ይህ አኩሪ አገራዊ ማንነት የበለጠ ጎልቶ እንዳይወጣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአገራችን ለመጣው ለውጥም የበኩሉን አስተዋፆኦ በማድረግ ድጋፉን በአደባባይ የገለፀ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ጠብቆ ሰንደቁን ከፍ አድርጎ በማውለብለቡ በተለይ የአዲስ አበባ ወጣት እየተገፋ ይገኛል፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ ሕዝብ በቁመናው ልክ መብቱን የሚያስከብርለት ፣ የልማት ተጠቃሚነቱን ፣ የዴሞክራሲና የነፃነት ባለቤትነቱን በተግባር የሚያረጋግጥ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ባለፉት ሣምንታት የተለያየ መንፈስ እና ፍላጎት ያላቸው ሰዎችና ድርጅቶች የአዲስ አበባ ነዋሪ የአገሩ ባለቤት ሣይሆን ተፈቅዶለት በይሁንታ እንደሚኖር በተደጋጋሚ መገለፁ ይታወሣል ፡፡ ከዚህም መንፈስ ባልራቀ መልኩ የአዲስ አባበ ነዋሪ መብቴ ተገፍቷል ማለቱን ተከትሎ ፤በፖሊስ የተወሰደው እርምጃ ብሎም ከሕግ አግባብ ውጪ በማሰር ለማሸማቀቅ  የተደረገው ፍፁም ሥርዓት የጣሰ፣ ያለፈውን መንገድ በብዙ መልኩ እንድናስታውስ እና ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርግን ኩነት ሆኖ አልፏል ፡፡
በተለይ ቋንቋን መሰረት ያደረገው የፌዴራል ሥርዓት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች መካከል ለግጭት ዋንኛ መንስሄ በመሆን ለሞት እና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ የፌዴራሉ አወቃቀር ባለፉት 27 ዓመታት ያመጣውን አስከፊ ችግር አስመልክቶ ሰማያዊ ፓርቲ በተደጋጋሚ ሥጋቱን ብቻ ሣይሆን አማራጭ ሐሳቡ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሁን ላይ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች የአስተዳደር እና የማንነት ጥያቄ በማንሳት ላይ ይገኛሉ፤ ለሚያነሷቸው የማንነት ጥያቄ መንግስት በወቅቱ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በማጓተት ለሚነሱ ጥያቄዎች የኃይል እርምጃ በመውሰዱ የችግሩ አሳሳቢነት ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በራያ አላማጣ ዜጎች ለሚያነሱት ጥያቄ የፌዴራል መንግሥት እንዲሁም የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠታቸው የንጹሃን ዜጎች ሞት አስከትሏል፡፡ በተለየም የፀጥታ አካላት በሚውስዱት ተገቢና ተመጣጣኝ ያለሆነ የኃይል እርምጃ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ የአስተዳደር እና የማንነት ጥያቄዎች በጠመንጃ ሃይል ምላሽ ለመስጠት የሚደረገው የትኛውም አካሄድ ከሕግ ወጥነቱ ባሻገር በምንም መልኩ ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚያመጣ አይደለም፤ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲህ አይነቱ የዜጎችን መብት የሚደፈጥጥ  ማናቸውንም አካሄድ አጥብቆ ያወግዛል፡፡
በሌላ በኩል የመልካም አስተዳዳር እጦት ታክሎበት እኛ ነን ባዮች ለሕግ እና ለሥርዓት ተገዢ ያልሆኑ ግለሰቦች በፈጠሩት ችግር ሐረር ከተማ ለከፋ ችግር ተጋልጣለች፡፡ ሐረር ከተማ ላለፉት ስድስት ወራት ዜጎች ለዉሃ ጥም የተዳረጉ ሲሆን ከተማውም በቆሻሻ ክምር ተውጣለች ፡፡ ነገሩን በይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ለችግሩ ዋንኛ ምክንያት የተወሰኑ ወጣቶች በቀናት ጊዜ ውስጥ ብር እንዲከፈላቸው በመጠየቅ የውሃ መስመሩን በመስበራቸው እና ቆሻሻም አናስደፋም በማለታቸው ነው፡፡ የሐረር ነዋሪዎች ውሃ እና ቆሻሻ ማስወገጃ መሬት ተከልክለው በነዋሪቹ ላይ የደረሰውን አጠቃላይ ችግር ሰማያዊ ፓርቲ በአንክሮ እየተከታተለው ሲሆን፤የሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳይውል ሳያድር በአስቸኳይ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ በአገሪቱ ውስጥ እየተደረገ ያለውን ለውጥ የሚደግፈው በየትኛውም መልኩ ዜጎችን በእኩልነት የሚያይ ሥርዓት እስካለ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ባለፈው ወራት ውስጥ በአገራችን በተለያየ አካባቢ የተነሱ ግጭቶች በህግ የበላይነት አግባብ ብቻ እንዲፈቱ ሲጠይቀ መቆየቱ ይታወቃል፤ በድጋሚ ፓርቲያችን ዜጎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በህግ አግባብ ብቻ እንዲፈታ አጥብቆ ይጠይቃል ፡፡ዛሬ ላይ የሚታየው የመብት ረገጣ ነገ የምንደርስበትን መንገድ ከወዲሁ መገመት እንድንችል ከዚህ ቀደም ከየት ተነስተን የትኛው ላይ እንደደረስን ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው ፡፡
ስለሆንም ሰማያዊ ፓርቲ 
1. ዜጎች በመሠላቸው በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ መደራጀት መብት እንዳላቸው ያምናል ፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብን ለመደራጀት የሚያደርጉት የትኛውንም ሰላማዊ ጥረት ይደግፍል !
2. አዲስ አበባ ሕዝብ የራሱን መብት በአግባቡ ማስከበር የሚችል ሕዝብ በመሆኑ ከተማውን በመረጠው ወኪል ብቻ የማስተዳዳር እንዲሁም ከተማውም የሕዝቡ መሆኑን ያምናል !
3. በአገራችን የተለያየ አካባቢዎች ዜጎች የአስተዳደር እና የማንነት ጥያቄ በሚያነሱበት ወቅት በመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች የሚወሰደው የሃይል እርምጃ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ በመሆን ፈፅሞ እንዳይደገም !
4. በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ የአስተዳዳር እና የማንነት ጥያቄዎች በምክክር እና በውይይት የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ተደርጎ በመንግሥት በኩል አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ !
5. በንጽሃን ዜጎች ላይ  የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ የሰጡና ነፍስ ያጠፉ የጸጥታ ኃይሎች በሕግ ይጠየቁ ፤ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ተገቢውን ካሳ በአስቸኳይ ይካሱ!
6. በቀደሞ አጠራሩ ሐረርጌ በአሁኑ ሐረር ተብሎ በሚጠራው ክልል የመልካም አስተዳዳር ችግር ተቀርፉ፣ ጥቂት ወጣቶች ተደራጅተው የሚያሳዩት ሥርዓት አልበኝነት የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ሥርዓት አሲዘው ፤ የከተማው ነዋሪዎች ከውሃ እጥረትና ከቆሻሻ ማጠራቀሚያነት ወጥተው ከተማዋ ወደ ቀድሞ ዝናዋ እንድትመለስ፤  ከተማዋን የሚያውኩ ወጣቶች ተለይተው ለሕግ በአስቸኳይ እንዲቀርቡ ሰማያዊ ፓርቲ አጥብቆ ይጠይቃል !
ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር !
Filed in: Amharic