>

የነዳጅ ፕሮፓጋንዳ ጠጥቶ በስካር ላይ ላለ ህዝብ "መገንጠል መሸነፍ ነው" ይሉት ዲስኩር ፌዝ ነው!!! (ቬሮኒካ መላኩ)

የነዳጅ ፕሮፓጋንዳ ጠጥቶ በስካር ላይ ላለ ህዝብ “መገንጠል መሸነፍ ነው” ይሉት ዲስኩር ፌዝ ነው!!!
ቬሮኒካ መላኩ
”የእኔ ታሪክ እዚህ ላይ ያበቃል። የእናንተ እዚህ ላይ ይጀምራል። የኢትዮጵያን አንድነት መጠበቅ ዳር ድንበሯን ማስጠበቅ ካቃታችሁ ያን ጊዜ የእናንተ ታሪክ ይሞታል።የእኔ ታሪክ ደሞ ይጀምራል፣ያንፀባርቃል።”
አፄ ሀይለስላሴ  በመጨረሻዋ ደቂቃ ከቤተመንግስታቸው በደርጎች ሲወሰዱ  የተናገሯት ትንቢት ነች ።
ዓለም ለብዙ አመታት የአፄ ሀይለስላሴን ንግግሮች   እንደ ትንቢት ሲቆጥራቸው ኖሯል ። ጃማይካኖችም የአፄውን ሰውነታቸውን በመካድ አምላክ አድርገዋቸዋል።ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ጄኔቭ ላይ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት  “ዛሬ እኛ በፋሽስት ስንጠቃ ዝም ብላችሁ ብትመለከቱ ነገ እናንተን የሚያጠፋ ሀያል መምጣቱ አይቀርም ” በማለት በተናገሩ 2 አመት እንኳን ሳይሞላ አዶልፍ ሂትለር አውሮፓን በመውረር በአጠቃላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በጦርነቱ ተቀጥፏል።
ከላይ በመግቢያዬ የጠቀስኩት የቀዳማዊ ሀይለስላሴ ንግግር በደርግ ባይደርስበትም በወያኔ በመለስ ዜናዊ ደርሶበታል። መለስ ኤርትራን እንድትገነጠል ሲፈርም የወያኔ ታሪክ ሲሞት የሀይለስላሴ ታሪክ ደሞ ጀምሯል።
የመለስ አገር የማፍረስ ራእይ  ደሞ አቢይ አህመድ በDouble ዲጂት  እያሳደገው ነው።
ዛሬ የኦጋዴን ነፃነት ግንባር ሶማሌ ክልልን ለመገንጠል  ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ ተስማምቶ አገር ውስጥ ለመግባት ከመንግስት ጋር እንደተስማማ ቢቢሲ በድረገፁ አስነብቧል።
ጠ/ሚ አቢይ አህመድ ብዙ ጊዜ  የቀረበለት ወረቀት ሁሉ በፊርማ መሸክሸክ ነው እንጅ ውሎ አድሮ ህዝብና አገር ላይ ለሚያመጣው ጣጣ  ሁሉ ምንም ጣጣ የለውም።
ዶ/ር አቢይ ግብፅ ሄዶ ተመልሶ ብዙም ሳይቆይ የአባይ ግድብ የኮንክሪትና የሲሚንቶ ቁልል ሆኖ ቀርቷል።  ሳኡዲአረቢያ እየሄደ ምን አይነት ወረቀት እየፈረመ እንደሆነ አይታወቅም ። ዛሬ ደሞ አስመራ ሄዶ የሶማሌ ክልልን መገንጠል ፈርሞ ግሪን ላይት አሳይቷል።
 አቢይ አህመድ ይሄ አደገኛ ስምምነት ሲፈርም ህገመንግስቱ እንኳን ይፍቀድለት አይፍቀድለት ሳያውቅ ነው። በመሰረቱ አንድ ነፃ አውጭ ግንባር ህዝበ ውሳኔ ወይም ሪፈረንደም ለማድረግ መስማማት አይችልም። ህጉም አይፈቅድም ። በኢትዮጵያ ህገመንግስት መሰረት ሪፈረንደም ጥያቄ ማቅረብ ያለበት ክልሉን የሚመራው መንግስት እንጅ ጫካ ገብቶ የሚታገል ነፃ አውጭ አይደለም።
አሁን የሱማሌ ክልል ነዳጅ ተገኝቷል። የዛ ክልል ብዙው ህዝብ የነዳጅ ፕሮፓጋንዳ ጠጥተው በስካር ላይ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተስማማው መሰረት  ህዝበውሳኔው ሲደረግ 99 % ህዝብ መገንጠልን እንደሚደግፍ ምንም ጥርጥር የለውም። ጠ/ሚ አቢይ አህመድም  ወረቀትና  የመናገሪያ ማይክ ይቅረብለት እንጅ “መገንጠል መሸነፍ ነው ” እያለ እየደሰኮረ በተግባር ግን አገሪቱን ቀስ በቀስ  ተረት እያደረጋት ነው።
Filed in: Amharic