>
5:13 pm - Thursday April 19, 0903

ዶ/ር አምባቸው ፕሬዚዳንት ከሆኑ፣ ከፖለቲካ ትግል ጡረታ ይወጣሉ!!! (ውብሸት ሙላት)

ዶ/ር አምባቸው ፕሬዚዳንት ከሆኑ፣ ከፖለቲካ ትግል ጡረታ ይወጣሉ!!!
ውብሸት ሙላት
ዶ/ር አምባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ ድጋሜ ወደ ፖለቲካው ዓለም የመመለስ ዕድል አይኖራቸውም፡፡ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ከአዴፓ ሥራ አስፈጻሚነታቸውም ይለቃሉ፡፡ ምክንያቱን እንዲ ነው፡፡
ስለ ሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት አስተዳዳር ሁኔታ በሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 255/1994 አንቀጽ 6 እና 7 መሠረት ፕሬዚዳንት የሆነ ሰው በሥልጣን ዘመኑም ይሁን ከዚያ በኋላ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነትና ድርጅት መራቅ ይጠበቅበታል፡፡ አሁን ላይ ፕሬዚዳንት ሲሆኑም አገሪቱ የጅምላነቷ ተወካይ ስለሚሆኑ ከየትኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኛነት ማሳየት የለባቸውም፡፡
ዶ/ር አምባቸው በፕሬዚዳንትነት ሰበብ የተወሰነ ጊዜ እረፍት በመውሰድ ከእንደገና ወደ ሥልጣን ሊመለሱ በማሰብ ከሆነ በሕግ ተከልክሏል፡፡ ስለሆነም መመለስ ቢፈልጉም እንኳን ሕጉ ስለማይፈቅድ ላይሳካ ይችላል፡፡
ደ/ር አምባቸው ፕሬዚዳንት ከሆኑ የምትኖራቸው አንዲት ሥልጣን ብቻ ናት፡፡ እሷም የሞት ፍርድ የተላለፈባቸውን ወደ ዕድሜ ልክ እስራት መለወጥ ነው፡፡ ለነገሩ ይችም ብትሆን እየቀረች ነው፡፡ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ፍርዱን ማጽደቅ ከቀረ ቆይቷል፡፡ የሃየሎምና የክንፈ ገብረመድኅን ገዳዮች ብቻ ላይ ነው ፍርዱ የጸናው፡፡
ከዚች በስተቀር ሌሎቹ በግድ የሚፈጽሟቸው ተግባራት ናቸው፡፡ አማባሳደር መቀበልና መሾም ግዴታ ነው፡፡ መንግሥት ያቀረበውን ኒሻን መሥጠት፣የይቅርታ ቦርድ ባቀረበው ዉሳኔ መሠረት ይቅርታ ማድረግ፣ ነጋሪት ጋዜጣን ማወጅ (ካላወጀም ከ15 ቀን በኋላ ሕግ ይሆናል)፣የፓርላማ ስብሰባን መክፈት…የፕሬዚዳንቱ ሥራዎች ናቸው፡፡
እንግዲህ ለተወሰኑ ዓመታት እነዚህን ሥራዎች እየሰሩ ቆይተው ለፕሬዚዳንት ከሚሰጠው ክብርና ጥቅማ ጥቅም ጋር ጡረታ መውጣት ምርጫዎ ከሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡  በዚህ መንገድ ከፖለቲካው መገለልን በራሳቸው ነጻ ሕሊና፣ፍቃድና ፍላጎት  ከወሰኑ ያው የአማራ ሕዝብ በዚህ ወሳኝ እና በቀውስ ጊዜ ጥለውት እንደሸሹ በመውሰድ እንደሚያዝንብዎት መርሳት የለብዎትም፡፡ ምርጫዎ ነውና ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡
ይሁንና ምናልባት ሹመቱን የሚቀበሉት የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን እንደሚሰፋ ተስፋ በማድረግ (በድርጅትና በጓዶችዎ ቡኩል ቃልና ተስፋ ካለ) ከሆነ የሚሻለው ሥልጣኑ ሲጨመር ፕሬዚዳንት መሆን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንዴት እንደሚሻሻል እያወቅነው በአሁኑ ወቅት እንዲህ ዓይነት ማሻሻያ፣ እርስዎ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ፣ ይደረጋል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡
ሌላው ዶ/ር አምባቸው ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ መንግሥታዊ መዋቅሩ ከፓርላማዊ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ይቀያራል በሚል ተስፋና እርስዎም በፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ በማሰብ ከሆነም ሕጉ አይፈቅድም፡፡ በተግባርም አስቸጋሪ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ከአዴፓ ከለቀቁ ለፕሬዚዳንትንት ለመወዳደር በአንድ በኩል የየትኛውም ፓርቲ ሊቀመንበር ስለማይሆኑ እጩ መሆን እንኳን አይችሉም፡፡ በሌላ በኩል አስቀድመው ፕሬዚዳንት ስለሆኑ ወደ ፖለቲካው ዓለም መመለስን ሕጉ ስለሚከለክል በሕግም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
 እንግዲህ ሕገ መንግሥቱ ተሻሻሎ የፕሬዚዳንቱ ሥልጣን እንደሚጨምር በማሰብ ከሆነም ገና “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” ነው ነገሩ፡፡
የሆነ ሆኖ በራስዎ ነጻ ውሳኔ ከሆነ እንደፍላጎትዎ! ነገር ግን ወደ ፊት የተሻለ ሥልጣን በመያዝ ለማገልገል ከሆነ  ወደ ፖለቲካ መመለስ በሕግ ስለተከለከለ የመሳካት ዕድሉ ጠባብ ነው-በያንስ በሕግ ክልክል ስለሆነ፡፡ ሌሎች ወዳጆችና ጓዶችዎ እንዲህ እንዲያደርጉ ከመከሩዎት ይቺ ምክር የወዳጅ ምክር አይደለችም፡፡ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ከፖለቲካው ዓለም ጡረታ ማስወጫ ስልት ነውና!
Filed in: Amharic