>

ማዕበሉ ከብዷል ዋኝቶ የሚያሻግር ፖለቲከኛ  ካላገኘ የአዴፓ መርከብ ይሰጥማል !!! (የሽሀሳብ አበራ)

ማዕበሉ ከብዷል ዋኝቶ የሚያሻግር ፖለቲከኛ  ካላገኘ የአዴፓ መርከብ ይሰጥማል !!!
የሽሀሳብ አበራ
ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያዋቀሩት ካቢኔ ወቅቱን እና የታመመውን ፖለቲካ የሚፈውስ አይደለም፡፡እሳቸውን ንጉስ አድርጎ ሌላው የእሳቸውን ፊት እያየ የሚኖር ብቻ ይመስላል፡፡ይህ ከሆነ አምባገንነት  ሳይወዱት በግድ ይመጣባቸዋል፡፡ አዛዥ ብቻ ይሆናሉ፡፡ይህ እንዲሆን ግን ያደረጉት እሳቸው አይደሉም፡፡ አንዱ አዴፓ ነው!!
“የውስጤን ደብቄ ፈገግ ያልኩት መንግስታችን ተነካ ብለው በቡራዮ፣በሱልልታ፣በለጋጣፎ ያሉ ሰዎች እየመጡ ስለነበር ነው”
ጠሚዶ አብይ
 ….
ሰባት ሚሊየኑ የአዲስ አበባ ህዝብ መንግስታችን ተነካ አይልም? ከምኒሊክ ቤተመንግስት ስር ያለው አዲስ አበቤ  ጠቅላይ ሚኒስተሩን አይፈልጋቸውም?”
 …
ነገሩ ሌላ ነው፡፡ጃዋር አምባገነኑን የወያኔ ስራዓት ደርመሰነዋል፡፡የቀጣይ የቄሮ ስራ ፀረ መፈንቀለ መንግስት ወታደራዊ ስልጠና መውሰድ ነው፡፡Anti coup የሚል መፅሃፍም እያከፋፈለ ነው፡፡ ሁለተኛው መንግስት ቄሮ የመንግሥት  ዘበኛ ነው ብሏል፡፡ ዶክተር አብይ በዚህ ታመኑ፡፡
 …
ጃዋር ለምን ፀረ መፈንቀለ መንግስት ስልጠና ለቄሮ ያሰጣል?!
” አማራ እና ትግሬ ኢትዮጵያን ለ 3 ሺ ዘመን ገዝቷል፡፡ ቀጣዮ 3 ሺው ዘመን የኦሮሞ ነው” ብለው ነበር፡፡ ሌንጮ እንደተመኙት ይሆን ዘንድ ቄሮ የመንግሥት ጠባቂ መሆን አለበት፡፡
 …
ቀጣየ ዘመን የነ ሌንጮ ከሆነ ኢትዮጵያ ቀለሟ መቀየር አለባት፡፡ቅየራው የሚጀምረው ከአዲስ አበባ ነው፡፡እናም?
” ህገወጥ የመሬት ወረራ ባዲስ አበባ ተስፋፍቷል” የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር
 ምን ማለት ነው?!
” በፊንፊኔ  የቤተክርስቲያን  የመሬት ይዞታ ሁሉ መስተካከል አለበት”
ጃዋር አሃዱ ለተሰኘ ኤፍ ኤም ራዲዮ
” ሆርምሳ ፊንፊኔ  ማህበር ተመስርቷል፡፡
ዳሩ ግን አዲስ አበቤ የኢትዮጵያ  ናት ብለው ማህበር ለመመስረት የተዘጋጁት እስር ቤት ገብተዋል፡፡ክሳቸውም አዲስ አበቤን በኢትዮጵያነት ማደራጀታቸው፣አዲስ አበባን የአዲስ አበባ ህዝብ ሳያውቀው በክልል በተወከለ ሰው መመራት የለባትም ማለታቸው ነው፡፡ጉዳዩን እነ አምነስቲ እያወገዙት ነው፡፡
በተደጋጋሚ  ለመፃፍ እንደሞከርነው ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመሃሉ መንገድ  ተጉዘው ኢትዮጵያዊነትን መስበክ ይፈልጋሉ፡፡ደግ ሰውም ናቸው፡፡ከሴራ የራቁም ይመስላሉ፡፡ተፈጥሮአቸው ይሄ ቢሆንም፣የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተፈጥሮአቸው ልክ እንዲሆኑ አያስችልም፡፡ጠቅላያችን የኦዴፓ ወኪል ናቸው፡፡ኦዴፓ ከኦነግ በበለጠ በህዝብ ዘንድ ለመወደድ ኦነግን ያስወደዱትን ነገሮች ያመጣል፡፡ እነዛን ነገሮች ሲያመጣ ኦዴፓ ኦነግ ይሆናል፡፡ ጠሚዶ አብይም ባይወዱትም የኦነግን እሳቤ የመሸከም ዕዳ ይወድቅባቸዋል፡፡ካልሆነ ኦዴፓ አያስቀጥላቸውም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያዋቀሩት ካቢኔ ወቅቱን እና የታመመውን ፖለቲካ የሚፈውስ አይደለም፡፡እሳቸውን ንጉስ አድርጎ ሌላው የእሳቸውን ፊት እያየ የሚኖር ብቻ ይመስላል፡፡ይህ ከሆነ አምባገንነት  ሳይወዱት በግድ ይመጣባቸዋል፡፡ አዛዥ ብቻ ይሆናሉ፡፡ይህ እንዲሆን ግን ያደረጉት እሳቸው አይደሉም፡፡ አንዱ አዴፓ ነው፡፡
 አዴፓ!!
ሚኒስተር  ድልድሉ አማራ እና ደቡብ 25%፣ኦሮሞ 30% ነው፡፡ ይህ ፍትሃዊ ነው፡፡ ነገር ግን አዴፓ የሚኒስትር ቦታ እና ሰው ሲመርጥ ብዙ አልቻለበትም፡፡ሙያ እንጂ ፓለቲካ የማይወዱትን ብቻ መርጦ ላከ፡፡ፌዴራል ላይ አዴፓ የሙያ ተወካይ እንጂ ጠንካራ የፖለቲካ ተወካይ የለውም፡፡በሙያ ፍትህ አይመጣም፡፡አንድ ፖለቲከኛ ሺ ባለሙያዎችን ይመራቸዋል፡፡ሌላው አዴፓ የመረጠው የሚኒስትርነት ቦታም ብዙ የሚያሰራ አይደለም፡፡የሚያሰራ ቢሆን እንኳን አዴፓ ስልጣኑን የመጠቀም ታሪክ የለውም፡፡ አንድ የትህነግ ሰው ደህንነቱን ብቻ ቢይዝ ሃገሪቱን ይመራል፡፡ብዙ ተቋማትን ከመምራት ይልቅ የሚመሩትን ውስን ተቋም በአግባቡ  መርቶ መጠቀም ይበልጣል፡፡አዴፓ አዲስ ትውልድ የለውም፡፡አዲሱን ትውልድ በአሮጌ ሃሳብ እየሞከረ ራሱም ፣የሚመራውን ህዝብም በድጋሜ አስቀድሟል፡፡
በአጠቃላይ በሚኒስትር ሹመት ላይ ጠሚዶ አብይ ተወቃሽ አይደሉም፡፡ አዴፓ ያቀረበላቸውን ሹመዋል፡፡አለቀ፡፡
 ….
የአዴፓው ዶክተር አምባቸው አቶ  ደመቀ  ስልጣን ቢለቁ ኑሮ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆኑ ነበር፡፡ነገር ግን አቶ ደመቀን ፓርቲያቸው እና ህዝባቸው ስለ ፈለጋቸው አሻፈረኝ ቢሉም ቀጠሉ፡፡ዶክተር አብይም አዴፓ ሊቀመንበር ቀይሮ አዲስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲያመጣ መክረው ነበር፡፡አዴፓ በ 1983 መሪ ያደረጋቸውን ህይዎታቸው እስኪያልፍ ይዞ ይቀጥላል፡፡ህይወታቸው ካለፈም ዘመዶቻቸውን ይተካል፡፡እናም አዴፓ ካለ ፍላጎታቸው ቢሆንም አቶ ደመቀን አስቀጠለ፡፡
 ….
ዶክተር አምባቸው ሊቀመንበርነቱን ሳይፈልጉት አልቀሩም፡፡ ቀረባቸው አኮረፉ፡፡ሚኒስተር ላለመሆንም የጣሩ ይመስላል፡፡ ስለዚህ የሃገሪቱ ፕሬዜዳንት ለመሆን አሜን እንዳሉ እየተሰማ ነው፡፡ከ 9 ኙ ስራ አስፈፃሚ መሃል አንዱ በመሆናቸው ያለፈቃዳቸው የሆነ ነገር አለ  ማለት ያስቸግራል፡፡
 …
የአዴፓ መሪ ለአማራ ውሃ የሚቋጥር ስራ አልሰራም፡፡ዶክተር አምባቸውም በስተቀር አይደሉም፡፡ዶክተር አምባቸው ትሁት፣ቀጥተኛ እና አማራዊ ስሜት ያላቸው ናቸው፡፡ነገር ግን ባላቸው ቀናነት  ልክ  የገዘፈ ስራ አልሰሩም፡፡ ምን ሰሩ?! ስለዚህ አዴፓን  ከግለሰብነት ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ አዴፓ በጥቅሉ መሻሻል አለበት፡፡
 ….
አዴፓ እስካሁን አዲስ የተመረጡ የማዕከላዊ  ኮማቴ አባላትን እንኳ አላቀረባቸውም፡፡አዴፓ ከብአዴንነቱ ገና አልወጣም፡፡ ብአዴንነት ደግሞ በግለሰባዊነት እና በአካባቢዊነት ተጠቂ የሆነ ድርጅት ነው፡፡ ብአዴን ገጠር ባለው አካባቢው ተጋርዶ የአዲስ አበባን ሰማይ ሳያየው መሽቶ ይነጋል፡፡ ይህን የቆየ ባህሉን ካልቀየረው ዮጎዝላቢነትን ወይም ሩዋንዳነትን በጉያ በያዘች ሃገር ውስጥ  ራሱ ሰጥሞ ያሳፈራቸውን ህዝብም ባህር ላይ ይደፋል፡፡
የፊታችን ማክሰኞ አዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴውን ይሰበስባል፡፡ሰብስቦ ተገቢ ሹመት እና ተልኮ ካልሰጠ የአዴፓ መርከብ በማዕበሉ ይሰጥማል፡፡ ማዕበሉ ከብዷል፡፡ዋኝቶ የሚያሻግር ፖለቲከኛ  ከማዕከላዊ ኮሚቴው ውጭም ቢሆን ያስፈልጋል፡፡አማራ ሙያዊ እውቀትን እና አመክንዮን በመከተሉ ተጎድቷል፡፡ጨዋ በመሆኑ ተጎሳቁሏል፡፡የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴራ እና ይሉኝታቢስነት ነው፡፡ ልክ ባይሆንም አሸናፊ ያደርጋል፡፡ ነፃ ከማያወጣ እውነት ደግሞ ነፃ የሚያወጣ ውሸት ይሻላል፡፡ እናም አዴፓ የኢትዮጵያን  የፖለቲካ እውነት የሚረዱ ሰዎችን በየተቋሙ ይመድብ፡፡፡
Filed in: Amharic