>

አብይን በመደገፌ አላዝንም፤ አልጸጸትም! (ፋሲል የኔአለም)

አብይን በመደገፌ አላዝንም፤ አልጸጸትም!
ፋሲል የኔአለም
 
* ሲያዩት ትንሽ የሚመስለው ብርጭቆ ሲሰበር ይበዛል፤ አገርም እንደ ብርጭቆ ነው። አንዴ ከተሰበረ  ስብርባሪውን ለቅሞ እንደነበረው ለማድረግ ፈታኝ ነው!
አብይ ስሜቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተጎዳ ከዛሬው የፓርላማ ንግግሩ ታዝቤአለሁ።  ህዝብ ካልደገፈው በስተቀር ወንበሩ ላይ መቀጠል እንደማይፈልግም ተናግሯል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በማንኛውም ጊዜ “በቃኝ” ሊል የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። የአብይን የስሜት መዳከም ያዩ ሰዎች፣  በክፉ ድርጊታቸው ተበረታተው እንዳይቀጥሉ እሰጋለሁ። ዳር ላይ ቆመው “ዛፉ ይወድቃል አይወድቅም” እያሉ ሲዋልሉ  የነበሩ ሰዎችም፣ ቶሎ ብለው ለውጡን ከሚቀለብሱ ሃይሎች ጋር ተደምረው ቅልበሳውን እንዳያጡዋጡፉት እፈራለሁ ። በአጠቃላይ የአብይ ስልጣን መልቀቅ  ወይም መድከም  ለኢትዮጵያ ክፉ እንጅ መልካም ነገር ይዞ ሲመጣ አይታየኝም። በዚህ ወቅት ከአብይ የተሻለ፣ በአብዛኛው ህዝብ የተደገፈ አሻጋሪ መሪ ማግኘታችንን እጠራጠራለሁ። አደጋ ሳይደርስ መማርና አደጋ ከደረሰ በሁዋላ ከአደጋ መማር ከፍተኛ ልዩነት አላቸው።
 ሲያዩት ትንሽ የሚመስለው ብርጭቆ ሲሰበር ይበዛል፤ አገርም እንደ ብርጭቆ ነው። አንዴ ከተሰበረ  ስብርባሪውን ለቅሞ እንደነበረው ለማድረግ ፈታኝ ነው።
አብይ ተዳክሞ ባየውም ራዕዩን አለመልቀቁ ገርሞኛል። አሁንም በተደካመ አንደበቱ- “የዘመናችን በሽታ ከሆነው የብሄር አጥር መላቀቅ አለብን”ይላል። አሁንም “ወላይታው በፈለገው ቦታ ሄዶ እንዲሰራ ድንበር ሊገድበው አይገባም” ሲል ይማጸናል።  በዙሪያው ካሉት ሚኒስትሮች ጀምሮ  ያሉት ባለስልጣናት ግን እየሰሙት አይመስለኝም።  የብዙዎቹ ችሎታ ለመብት የሚታገሉትን ማሰር እንጅ ማትጋት አለመሆኑን፣  ትናንት በነጻነት ታጋዮች ዛሬ ደግሞ በእነ  ሄኖክ አከሊሉ እስር አይተነዋል።
አብይ የያዘውን ራዕይ ሳይጥል፣ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ፍላጎት እያዳመጠ እንዲቀጥል እመክረዋለሁ። እንኳን አገር ቤተሰብ ማስተዳደር ቀላል አይደለም። አንዳንድ ባለትዳሮች ችግር ሲያጋጥማቸው ፍችን እንዳማራጭ ወስደው ትዳራቸውን ይበትናሉ፤ ሌሎች ደግሞ እስከመጨረሻው ታግሰው ለማስተካከል ይሞክራሉ። አብይ ሁለተኛውን አማራጭ ቢከተል፣ አገሪቱን ማዳን ብቻ ሳይሆን፣ ለችግር እጅ አለመስጠትን ለወጣቱ አስተምሮ ማለፍ ይችላል።
   አብይን እንዴት ታምነዋለህ የሚሉኝ ሰዎች አሉ። አሁን ባለበት ደረጃ ከቃል ባለፈ በሌላ በምን ላምነው እችላለሁ? ተግባር እኮ የቃል ተሳቢ ነው። ቃል ሳቢ፣ ተግባር ተሳቢ ነው። አብይ ቃሉን ሲለዋውጥ አልሰማሁትም። አሁንም የሚለው ትናንት ሲለው የነበረውን ነው። ዛሬ ቃሉን፣ ነገ ደግሞ ተግባሩን አይቼ እደግፈዋለሁ። ነገ ግን ስንት ነው? እሱን ነገ እነግራችሁዋለሁ። በአጭሩ አብይ ቃሉን በተግባር ካዋለ እሰየው ነው፤ ቃሉን መሬት ላይ ማውረድ ተስኖት “በቃኝ” ቢል እንኳን፣ ትናንት ስለተናገረው ቃሉ  ድጋፌን በመግለጼ እደሰታለሁ እንጅ አላዝንም፤ አልጸጸትም።
Filed in: Amharic