>

መንግስት የጀመራት ድብብቆሽ የእረኛውን እና የቀበሮውን ታሪክ እንዳታስከትል ከወዲሁ ይታሰብበት!! (ያሬድ ሀ/ማርያም)

መንግስት የጀመራት ድብብቆሽ የእረኛውን እና የቀበሮውን ታሪክ እንዳታስከትል ከወዲሁ ይታሰብበት!!
ያሬድ ሀ/ማርያም
* ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፓርላማ ውስጥ ስለ ቤተመንግስቱ የወታደሮች ወረራ ክስተት የሰጡት ማብራሪያ መንግስት ከሕዝብ ጋር የጀመረውን ድብብቆሽ ማሳያ ነው!
 
* ሕዝብ እናረጋጋለን፣ ሰላም እናወርዳለን፣ ደም መፋሰስን እናቆማለን እየተባለ በመንግስት በኩል ለሕዝብ የሚቀርቡት የማደናገሪያ እና የተሳሳቱ መረጃዎች ሁለት አደጋ ያስከትላሉ!
– የመጀመሪያው ሕዝብ አንዳንድ ክስተቶችን ተከትሎ መንግስት ወዲያው የሚሰጣቸውን መግለጫዎችምም ሆነ የማረጋጊያ ዘገባዎች እውነት ነው ብሎ እንዳይቀበል ያደርጋል። መንግስት መግለጫ በሰጠ ቁጥር ሕዝብ ግልባጩን እንዲያስብ ያደርጋል። ሕዝብ በመንግስት ተቋማት ላይ ዱሮም እምነት የለውም አሁን ደግሞ የበለጠ እምነት እንዲያጣ ያደርጋል። ፖሊስ ውሸታም ተደርጎ በሚታይበት አገር ለማረጋጋት ተብለው የሚዋሹ እና ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ የሚገለጹ እውነቶች ይምታቱና ሕዝቡንም ያምታታሉ ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስም ያማታሉ። በመስቀል አደባባይ ቦንብ በፈነዳ ጊዜ፣ በቡራዩ እልቂት እና በቤተ መግስቱ የወታደሮች ወረራም ወቅት የሆነው ይሄው ነው። በዛ ላይ ሁሉም ባለስልጣናት በአንድ ጉዳይ የተለያየ ውሸቶች ሲዋሹ እና የተለያዩ እውነቶችን ሲገልጹ ሕዝብ ማንን ማመን እንዳለብትም ይቸገራል። በቡራዩ ጉዳይ እንኳ የፖሊስ እና የመንግስት ባለሥልጣናት እስካሁን የሚሰጧቸው መረጃዎች ወጥነት የሌላቸው፣ እርስ በእርስ የሚጋጩ እና አንድ እነሱ የሚያውቁትን እውነት ለመደበቅ የታሰቡ ነው የሚመስሉት።
– ሁለተኛው አደጋ የማይተማመን ሕዝብ እና መንግስት አብሮ አደጋን ለመከላከል የማይችልበትን ሁኔታም ይፈጥራል። መንግስት ሊቆጣጠራቸ የማይችሉ እና የሕዝብ ድጋፍ የሚጠይቁ አደጋዎች በመጡ ጊዜ ሰሚ ያጣና  አገርን ለቀበሮ መንጋ አሳልፎ መስጠትም ይመጣል።
አደጋን መከላከል፣ አደጋን በጥንቃቄ ማስቆም እና ነገሮች እስኪረጋጉ ደረስ ሕዝብ እንዲረጋጋ ማድረጉ እንዳለ ሆነ መዋሸት ግን ዋጋ ያስከፍላል። የመንግስት ውሸቶችን በሚያስተላልፉ ሚዲያዎችም ላይ ሕዝቡ እምነት እንዲያጣ ይደረጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደፊትም ብዙ አደጋዎች ከፊትዎ ሊጠብቅዎች ስለሚችል የመቶ ሚሊዮን ሕዝብን ሕመም ብቻዮን እታመመዋለው ብለው ባያስቡ ጥሩ ነው። ሕዝብን የማረጋጋት ሥራ የሚሰራው አደጋ የመጣ ለት አይደለም። በሰላሙ ጊዜ ሕዝብን እንዳይረጋጋ የሚያደርጉትን አደጋዎች እንደ መንግስት አጥንቶ በጊዜ ቀጠናውን ማጽዳት ነው።
ይታሰብበትi
Filed in: Amharic