>

እዉነታ ላይ እንጣበቅ ወይንስ ወደ እዉነት እንንፏቀቅ? (ኢብራሂም ሙሉሸዋ)

እዉነታ ላይ እንጣበቅ ወይንስ ወደ እዉነት እንንፏቀቅ?
ኢብራሂም ሙሉሸዋ
«ኦነግ ጎጃም ፣ አብን ደግሞ አርሲ ሄዶ ሰላማዊ ሰልፍ የመጥራት ሙሉ መብት እንዳለው ካወቅን ግንቦት 7 ሀረር የጠራውን ሰልፍ መከልከል  ሊታገሱት የማይገባ በደል ነው። ስለጠላን መብት መንፈግ አንችልም!!!» 
በማህበራዊ ድረ ገፆች የማቀርባቸው መጣጥፎቼ ላይ ለሚሰጡኝ አስተያየቶች ምላሽ የምሰጥባቸው እንደ ግለሰብ አስተያየት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን አመለካከት የሚወክሉ አስተያየቶች እንደሚሆኑ በማሰብ ነው። ከላይ የጠቀስኳቸውን ድርጅቶች አንድ ላይ አድርጌ ማቅረቤንና ድጋፍ የሌላቸው ቦታዎች ላይ ሰልፍ መጥራት አለባቸው ማለቴ ላንዳንዶች እጅግ ተቀባይነት የሌለው ሊሆን ይችላል።
አንዳንዶች «አብን» አርሲ መገኘት ቀርቶ ለመምጣት የማሰብ ነፃነት እንዳለው ማሰቤን እንደ እብደት ሊቆጥሩት ይችሉ ይሆናል። «ኦነግ» ላይ የተያዘውን የዘንድሮ ዘመቻ ከወሰድን ደግሞ ኦነግን ጎጃም ላስገባው በመሞከሬ አንዳንዱ «እንኳን ኦነግ አንተ እራስህ ጎጃም ትደርሳታለህ!» ሳይል አይቀርም። የእነዚህ ምልከታዎች ዋናው ሰበብ መቻቻል የማይታይበት የጥላቻ ፓለቲካችን መሆኑ ግልፅ ቢሆንም ሌላም ወሳኝ የሆነ መንስኤ እንዳለ አምናለሁ። የእውነታና የእውነት መደበላለቅ ጉዳይ።
ከተሰጡኝ አስተያየቶች መካከል ትኩረቴን የሳቡት በጣም ቅን ከሆኑ እና ለኢትዮጵያችን የሁለ መና እድገት ከሚጨነቁ ወንድሞቼ የተሰነዘሩት ናቸው። ይህ ፅሑፍም በከፊል ለእነዚህ ብርቅዬ የሀገሬ ልጆች የተሰጠ መልስ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። እነዚህ ወዳጆቼ እኔ ያልኩት ነገር ለዲሞክራሲያዊ እድገት ወሳኝነት ያለው እንደሆነና እንደሚቀበሉት ግና አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁናቴ እኔ ያልኩትን ማስተናገድ እንደማይችልና ሀሳቤ ከልፋት የዘለለ የሚፈጥረው ነገር እንደሌለ ነግረውኛል። ለነሱ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ዲሞክራሲን እኔ ባልኩት መንገድ ስለማያስተናግድ ሊተገበር የማይችል ነው።
በአሁኑ ግዜ በሀገራችን መቻቻል ላይ ያልተመረኮዘ ፓለቲካ በተጨባጭ የሚታይ መሆኑ ብዙዎቻችንን ከዚህ አይነት አስተሳሰብ መውጣት እንደማንችል አሳምኖናል። ይህ ተጨባጭ ሁናቴ ልንቀይረው የማንችል እውነት እንደሆነ እያሰብን እንገኛለን።  ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች የነሱ አመለካከት ያልሆነን ነገር ለመገንዘብ ከመጣር ይልቅ በአንዴ ወደ ማውገዝ የሚሄዱ በመሆናቸው ይህንን ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብና እሴትን ለማዳበር የሚደረግ ጥረትን ዋጋ ቢስ እንደሆነ የሚያምነው የትየለሌ ነው።
አንድ አስተያየት ሰጪ ወንድም ስለ ፅሁፌ «የዋህነት፤ ሚዛናዊነትና ፍትሃዊነት ያጠቃናል! አሁን ይሄ ከአይምሮ ውጭ በገሀዱ ዓለም ሊሆን የሚችል ነው??»ሲል ፅፎአል።
እኔም የሀገሬ ተጨባጭ እውነታ እንዲህ መሆኑን ብገነዘብም እንዲህ መሆን አለበት ብዬ ግን አላስብም። መለወጥ እንዳለበትም በፅኑ አምናለሁ። ለሱም መታገል አለብን እላለሁ። ሀገራችን ዲሞክራሲን ለመገንባት በምትጥርበት ወቅት የገጠማት ትልቁ ተግዳሮት እውነታ እውነትን መሸፈኑ ነው ብዬ አምናለሁ።
እዉነታና እዉነት፡
እውነታ አሁን ያለ ተጨባጭ ላይ ሲያተኩር እውነት ደግሞ መሆን ያለበት ነገር ላይ ያተኩራል። አሁን ባለው ተጨባጭ መሰረት ኦነግን ጎጃም ውስጥ ቅስቀሳ እንዲያደርግ ማድረግ የማይቻል ተጨባጭ ነው። ይህ እውነታ ግን እውነተኛ ዲሞክራሲ ለመገንባት እንቅፋት የሚሆን እንደሆነ እውነት መሆኑን ሊከራከር የሚችል ህሊና ያለው ሰው ሊኖር አይችልም። እውነቱ መንግስት እውቅና ሰጥቶት ሀገር ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ያደረገው አካል በኢትዮጵያ ውስጥ ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ተንቀሳቅሶ ፕሮግራሙን የማስፈፀም መብት አለው። ይህን እውነት በእውነታ ሳንሸፍነው ድብን አድርገን መቀበል አለብን። ዲሞክራሲን ከፈለግን።
ኦነግን አንዳንድ አካባቢ ላይ መንቀፍ ያለመቻል እውነታ ሊሆን ይችላል። መሆን ያለበት እውነት ግን ኦነግን በየትኛውም የሀገራችን ክፍል የመቃወም መብትን ማረጋገጥ ነው። ስለሆነም ይህንን ወይም ያንን እውነታ ማስተጋባት ሳይሆን አንድ የሆነችውን እውነት ማስተጋባት ነው ዲሞክራሲ። በሌላ አነጋገር እውነታን እንደ እውነት መቀበል ሳይሆን እውነትን እውነታ ማድረግ ያስፈልጋል።
«እውነት እንዴት እውነታ ይሁን?» ታድያ ከተባለ። በመጀመሪያ እውነት ከእውነታ የበለጠ ትግል ትጠይቃለች። እውነታ መስሎ ማደርን የሚጠይቅ ሲሆን እውነት ማስተካከልን፣ አይሆንም ማለትን ከፍ ካለም ሌሎችን ማስቀየምን ይጠይቃል። እውነት እንዲያውም የራስን ስሜት እና ጥቅምንም አሳልፎ ሊያሰጥ ይችላል። ባጭሩ እውነት ትልቅ ትግል ይጠይቃል።
ነገር ግን መረዳት ያለብን እውነታ ዘላቂነት ያለው ክብርንም ጥቅምንም አያስገኝም። እውነታ የሚሸነፍ ሲሆን እውነት ግን ሁል ጊዜ ባለ ድል ነው። አለማችን ላይ በታላላቅነታቸው የምናደንቃቸውና የምንከተላቸው ስብዕናዎች በሙሉ ታላቅ ያደረጋቸው ያለውን የተሳሳተ እውነታ በትክክለኛው እውነት እንዲተካ ባደረጉት የተሳካ ተግባር ነው።
የነብያቶችም ሆነ የአለማችን ታላላቅ የሳይንስ፣ የፍልስፍና እና የፓለቲካ ለውጥ ያመጣ አስተሳሰብን ያመነጩና የተገበሩ ታላላቅ ሰዎች ታሪክ ስንመለከት የምንገነዘበውም ይህንኑ ነው። ነብዮ ሙሴ በመጡበት ዘመን ህዝባቸው የነበረበት ተጨባጭ እውን ሊያደርጉት የተነሱለትን እውነት ለማሳካት የሚያስችል አልነበረም። የሙሴ ህዝብ ለረጅም ዘመናት የኖረበት የባርነት እና የግፍ ህይወት ከባድ ተፅእኖ ፈጥሮበት ስለነበር ይህን እውነታ መቀየር ይቻላል ብሎ ለመቀበል ከብዶት ነብዩ ሙሴን ፈትኗቿል። በመጨረሻ ግን ነብዩ ሙሴ ይዘውት የተነሱት እውነት በዘመኑ ብዙኋን ዘንድ ፈፅሞ ሊቀየር አይችልም ብለው የደመደሙትን እውነታን ድል አደረገ።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ወደዚህች ምድር ነብይ ሆነው በመጡበት ዘመን እውነታው ለእስልምና ሃይማኖት መፈጠርም ሆነ ማደግ የሚያስችል አልነበረም። የቁረይሽ ጣዖት አምላኪያን ከነብያችን ጋር ሲከራከሩ የነበሩት ስለ እውነት ብለው ሳይሆን ስለ እውነታ ብለው ነበር። ለምን አንድ አላህን አትገዙም ሲባሉ መልሳቸው “የምንከተለው የአባቶቻችንን ፈለግ ነው!” የሚል ሙግት ነበር።
ነብያችን ግን የሚሞግቷቸው እውነተኛው አምላክ አላህ ነው ብለው ነበር። በመጨረሻ ግን የጣዖት አምላኪያኑ የእውነታ አምላክ በሙስሊሞቹ እውነተኛ አምላክ ተሸነፈ። እውነታን ለመጠበቅ ያለዉን ማሳየት ብቻ ሲበቃ እውነትን ለማሳየት ግን ትግል ጠየቀ። ብዙም ክፍያ አስከፈለ።
አስታውስ!  ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦቻቸውን ወደ ሀበሻ ሲልኳቸው እውነታን ሳይሆን እውነትን ተማምነው ነበር። ቁረይሾች ግን እውነታን ተማምነው ነው። እንደ ቁረይሽ መሪዎች ስደተኞቹ አንዳች  የሚረዳቸው አካል የሌላቸው ምስኪን በመሆናቸው የተነሳ የሀገር መሪ የሆነ ንጉስ አሳልፎ የሚሰጥበት ፓለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ የነበረበት እውነታን ተማምነው ነው። ይህ እውነታ ስደተኞችን ከሀበሻ ምድር ሊያሰወጣቸው የሚችል ተጨባጭ ነበር። ነገር ግን ፍትሀዊው ንጉስ ከእውነታ አልፎ እውነትን ፈላጊ በመሆኑ እውነታ በእውነት ተሸንፎ ለስደተኞቹ በሀገረ ሀበሻ መጠጊያ ሰጡ። ይህን ድል ለስደተኞቹ ያስገኘላቸው አንድም የያዙት እውነት ሲሆን ሌላው ደግሞ የንጉሱ እውነትን ፍለጋ ነበር።
የዘመነኛይቱ ቻይና የኢኮኖሚና የፓለቲካ አባት የሚባለው መስራች ማኦ ወደ መሪነት በመጣበት ወቅት የቻይና ተጨባጭ ሁናቴ ሀገሪቱን ወደ ታላቅ የአለም ሀገራት መመደብ ቀርቶ እንደ ሀገር ልትቀጥል የምትችልበት እውነታ ላይ አልነበረችም። በረሀብ እና በችግር የተጠፈረችው ቻይና በውስጧ የነበሩ ብሄረሰቦችና ጎሳዎች መካከል ያለው ልዩነት ከውጪ ጠላቶቿ  ጣልቃ ገብነት ጋር ተዳምረው ሀገሪቱን የመጨረሻ ኋላ ቀር እና ህልውና አልባ አድርጓት ነበር። ማኦ ግን እሄንን እውነታ በመጋፈጥ ቻይና እጅግ የሰፍ የህዝብ ብዛት ያላት የመሆኑን እውነት ተገነዘበ። ይህንን እውነት ህዝብን ካደረጁ እና ካሰሩ የማይለወጥ ነገር እንደሌለ የሚያሳይ ሌላ ሀቅ ጋር አዳምሮ የቻይናን ተጨባጭ እውነታ ቀየረ። ዛሬ የቻይናን እድገት ለተገነዘበና ማኦ ወደ ስልጣን በመጣበት ዘመን ያለውን እውነታ ላወቀ እውነት እንጂ እውነታ የማይዘልቅ እና የሚሸነፍ መሆኑን ይረዳል።
ሰዎችን ስለ እውነተኛ የዲሞክራሲ ባህሪያት ስትጠይቋቸው ፍትህ፣ እኩልነት፣ የህግ የበላይነት መቻቻል፣ የሌሎችን መብት ማክበር እና የመሳሰሉትን ይዘረዝሩላችኃል። ግና እነዚህን ለማድረግ የሚያስችል ነባራዊ ሁናቴም በሀገራችን ያለመኖሩን ጠቅሰው ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ሊተገበር የማይችል በመሆኑ አርፈን መቀመጥ ያዋጣናል የሚል የሚመስል መልዕክት ይሰጡናል።
አንዳንዶች ደግሞ አሁን ያለውን ነባራዊ እውነታ በመጥቀስ የኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲ የማይገባው እንደሆነ ያረዱናል። አንዳንዱ አክትቪስት ከነጭራሹ በፊት ያሳለፍናቸውን አምባገነናዊ አገዛዞች እንደገና መመለስ እንደሚሻል ሲፅፍም አይተናል። ይህ እውነታ ላይ የተመረኮዘ የጨለምተኝነት አስተሳሰብን በመርጨት ህዝብን በጠባብ የፓለቲካ አስተሳሰብ የማነፅ ተግባር በተለያዩ ቡድኖች እየተሰሩ ይገኛሉ።
እውነትን ከመጋፈጥ ይልቅ በጣም በቀላሉ ስሜት ቀስቃሽ እና እውነታ ላይ የተመረኮዙ ፕሮፓጋንደዎች በመጠቀም ዘላቂ እድገትንና ሰላምን በማያመጡ የፓርቲና የብሄርተኛ አሰላለፍ ተከፍለን ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ መታገልን እንደ ሞኝነት ቆጥረን እውነታን የማይጋፈጡት እውነት ለማድረግ የሚደረግ ሩጫ መጨረሻው የዜሮ ድምር ፓለቲካ ውጤት ነው።
እውነተኛው አካሄድ ግን የሁሉንም የፓለቲካና ብሄርተኛ አመለካከት በእኩልነት ተቀብሎ እና ተሟግቶ መርታትና መረታትን መቀበል ነው። እውነተኝነት ባህርዳር ላይ ተቀምጦ ኦሮሞ ላይ አዳማ ላይ ሆኖ አማራ ላይ መፎከር ሳይሆን ባህር ዳር ላይ ሆኖ የኦሮሞ መብት ይከበር ወለጋ ላይ ሆኖ «የአማራ መብት ለምን ይነካ!?» የሚል ጀግና መፍጠር ነው። እውነታው ይህ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ዲሞክራሲ ከተባለ እውነቱ እሄ ነው።
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እውነታ የዲሞክራሲ ጠላት መሆኑ እውነታም እውነትም ነው። ነገ ግን እውነታችን እውነት እንዲሆን ከመስራት ሌላ ምንም አማራጭ የለንም።
Filed in: Amharic