>

እኔስ የነገን ፈራሁት! (አለማየሁ ማ/ወርቅ)

እኔስ የነገን ፈራሁት!
አለማየሁ ማ/ወርቅ
ለምን? ግን ለምን? የአዲስ አበባን ልጅ???
 የአ.አበባ ወጣት ኢትዮጵያን ባለ፤ 
ክብሬን ኩራቴን ፤ በአለም ፊት መገለጫዬን ባንዲራዬን ባለ፤
 ከባርነት ከግዞት የታደጉኝን የነጻነት አርማዬን እምዬን አትንኩ ባለ፤
ዘር ሀይማኖት ሳይከፋፍለው በኢትዮጵያዊ ወገኑ ላይ ዘሩ ተቆጥሮ እየደረሰበት ያለው  አሰቃቂ ግድያና ከገዛ አገሩ መጤ እየተባለ መፈናቀሉ አስቆጥቶት ውስጥ ውስጡን ያንገበገበው ቁጭነት ገንፍሎ ፍትህ አገኝ ብሎ አደባባይ ቢወጣ የጥይት እራት ሆነ መቁሰሉ መሞቱ እንኳ በክብር እንዳይሆን ” ቦዘኔ” “ዘራፊ ” ” በሱስ የናወዘ…” ሌላም ሌላም ስም ለጠፉበት ፡፡ ልጅየው ቀማኛ አባትየው ዳኛ ከሆኑበት አገር ከዚህ የተሻለ ፍትህ ከወዴት ይምጣልን!!
በቅርቡ እንኳን መሳሪያ አንግበው የጥቅማጥቅም ጥያቄ ላቀረቡ የሰራዊቱ አባላት የታየ ታጋሽነት ፣ ፍጹም አፍሪካዊ ባህርይ የሌለው አርቴፊሻል ዴሞክራትነት፣ እስከ ግብር ማብላት የደረሰ ለጋ ስንት ፤ ህገወጥነታቸውን ለማለባበስ የተሄደበት ያ ሁሉ ለትዝብት የሚዳርግ የቁልቁለት መንገድ ምነው ለአ.አባባ ልጆች ሲሆን:-
– አርቴፊሻል ዴሞክራትነቱም አምባገነነት
– ለጋስነቱም ንፉግ ነት
– የቁልቁለት መንገዱም ዳገት ሆነባችሁ???
አዎ እውነት ነው የአዲስ አበባ ልጅ ዘሬ ተጠቃ ብሎ የሚቆምለት ባስ ካለም ነፍጥ የሚያነሳለት የጎጥ ፓርቲ አልያም ግምባር በሉት ድርጅት የለውም፤
አዎ እውነት ነው የአዲስ አበባ ልጅ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወገኑ እንጂ ጠላቱ አይደለምና ጠላት አለኝ ብሎ አልተደራጀም አልታጠቀም፤
አዎ እውነት ነው የአዲስ አበባ ልጅ ማንም ከየትም መጥቶ ይግዛ ያስተዳድረው ይምራው የእርሱ ጥያቄ ለቦታው ይመጥናል ወይ? ፍትሕ ያሰፍናል ወይ? በእኩል አይን ይመለከተናል ወይ? ይህው ነው።
 ማንንም በአስተሳሰቡ እንጂ በዘሩ የማይመዝን መሆኑ ፤ የመጣውን ሁሉ የእኔ ዘር ሳይሆን የእኛ ልጅ የአገር ሰው ብሎ የክብር ስፍራ መልቀቁ… እኒህና መሰል ” ወንጀሎች” ተደራርበው ነው የምንፈልገውን እየነገሩን የሚፈልጉትን በሚሰሩ፣ አፋቸው እና ልባቸው አንድ ባልሆነ  የጊዜው ፈርዖኖች በግፍ ተግዘው በየ ወታደራዊ ካምፑ ታጉረው ለይስሙላ እንኳ ፍርድ ቤት የመቅረብ ሰብአዊ መብታቸው ተገፎ የስቃይ ሰቆቃ ህይወት እንዲገፉ የተፈረደባቸው።
እናውቃለን ብንናገር ደግሞ መከራ ይደርስብናል ከሚሉ የቅርብ የግፉ ሰለባዎችን ተመልካቾች የሚሰማው መረጃ ጆሮ ጭው ያደርጋል።
እውን በዛ ሁሉ የተሽሞነሞኑ ቃላት ስለ አንድነት ፣ስለ ፍቅር ፣ሥለ መደመርና የዜጎች ሰብአዊ መብት የሰበከን ” የለውጥ ሀይል” ነው ይህን ግፍ በዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለው? የሚለውን ለማመን ያዳግታል።
***
ቁጥራቸው ከ 9 የሚበልጥ ከአዲስ አበባ የታፈሱ ወጣቶች በጦላይ ካምፕ ውስጥ በቢጫ ወባ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ቁጥራቸው ያልተገለጸ ወጣቶች በወባና ውሀ ወለድ በሽታዎች ተጠቅተው ለብርቱ ስቃይ እንደተዳረጉ ለማወቅ ተችሏል።
በጤና ያሉትም ከአቅም በላይ የሆነ ወታደራዊ ቅጣት እንዲሁም ሰብአዊነት የጎደለው እስከ አካል ማጉደል የደረሰ አስከፊ ድብደባ እየተፈጸመባቸው ለመሆኑ በፎቶ የተደገፉ ማስረጃዎች እየወጡ ነው።
***
በእውነት ሚልዮኖች ተስፋ ካደረጉት ስርአት ሊያውም በወራት እድሜ ይህንን ግፍ የምናይ የምንሰማ ከሆነማ አመታት ባስቆጠረ ጡንቻውን ባፈረጠመ ጊዜማ እንደምን ያለ የመከራ ዘመን ያመጣብን ይሆን? የነገን ፈራሁት!
ፍትህ ለአ.አበባ ልጆች!!!
Filed in: Amharic