>

ማን ለምን ይታጠቃል? መቼ እና ለምን ትጥቅ ይፈታል ?!? (ስዩም ተሾመ)

ማን ለምን ይታጠቃል? መቼ እና ለምን ትጥቅ ይፈታል ?!?
ስዩም ተሾመ
በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ታጥቀዋል በሚል ሰበብ ትጥቅ አልፈታም ማለት ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም የተጠቀሱት አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የጦር መሳሪያ የታጠቁት በግል ያለባቸውን የደህንነት ስጋት ለመከላከል እንጂ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ አይደለም!!
ከመንግስት ፍቃድና እውቅና ውጪ ዜጎች የጦር መሳሪያ ሊታጠቁ የሚችሉበት አንድ ብቸኛ አጋጣሚ አለ። እሱም መንግስት፣ 1ኛ፡- በነፃነት የማሰብና ሃሳብን የመግለፅ መብት፣ 2ኛ፡- በነፃነት የመስራትና የመንቀሳቀስ መብት፣ 3ኛ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ከተሳነው፣ እንዲሁም በእጁ ላይ የተሰጠውን ስልጣንና ጦር መሳሪያ በመጠቀም የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚፃረር ተግባር ሲፈፅም ዜጎች የጦር መሳሪያ በመታጠቅ ሰላምና ደህንነታቸውን በራሳቸው ማስከበር ይችላሉ። ይህ ደግሞ በመንግስት አመሰራረት ሂደት ውስጥ ሁሉም ዜጎች በጋራ ስምምነት ለመንግስት የሰጡትን ስልጣንና ውክልና በማንሳት የሚደረግ ነው።
ከላይ በተገለጸው መልኩ ዜጎች በግል ወይም በቡድን የጦር መሳሪያ የሚታጠቁት፤ አንደኛ፡- በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የዜጎችን መብትና ነፃነት ማስከበር ስለተሳነው ነው፣ ሁለተኛ፡- መንግስት በራሱ ወይም በሌላ ምክንያት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ስለተሳነው ነው። ይህ ከሆነ መንግስት ዜጎች በጋራ ስምምነት የጣሉበትን ግዴታና ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ተስኖታል። በመሆኑም ዜጎች በግል ሆነ በቡድን የጦር መሳሪያ የሚታጠቁት የተጣለበትን ግዴታና ኃላፊነት መወጣት የተሳነውን መንግስት ከስልጣን በማስወገድ አዲስ መንግስት ለማቋቋም ነው።
የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) የትጥቅ ትግል የጀመረበት መሰረታዊ ምክንያት የኦሮሞን ተወላጆች መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ሰላምና ደህንነት ማስከበር የተሳነውን መንግስት በማስወገድ አዲስ መንግስታዊ ስርዓት ለመዘርጋት ነው። ሆኖም ግን አሁን በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ድርጅቱ ወደ የትጥቅ ትግሉን በማቆም በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ቤት ገብቷል። ይህ፣ አሁን ባለው ሁኔታ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ያስከብራል፤ ኦነግ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ በሚያደርገው የፖለቲካ ትግል የኦሮሞን ህዝብ መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋል በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው።
በዚህ መሰረት የጠ/ሚ አብይ አህመድ አመራር መንግስት ሲሆን ኦነግ ደግሞ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ይሆናል። ቀደም ሲል በተገለጸው መሰረት መንግስት ባለበት ሀገር የጦር መሳሪያ የታጠቀ የፖለቲካ ቡድን ሊኖር አይችልም። ኦነግ ትጥቅ አልፈታም የሚል አቋም ካለው በሌላ አነጋገር በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት አልተቀበለም ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ከስምምነቱ በኋላም የድርጅቱ ዓላማ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በማስወገድ አዲስ መንግስት መመስረት ነው። በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ታጥቀዋል በሚል ሰበብ ትጥቅ አልፈታም ማለት ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም የተጠቀሱት አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የጦር መሳሪያ የታጠቁት በግል ያለባቸውን የደህንነት ስጋት ለመከላከል እንጂ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ አይደለም። በመሆኑም ትጥቅ አልፈታም የሚለው አካሄድ በምንም አግባብ ተቀባይነት የለውም።
Filed in: Amharic