>

ወለጋ የኦነግ ነፃ ቀጠና መሆኑ ቀጥሏል!!! (ሀብታሙ አያሌው) 

ወለጋ የኦነግ ነፃ ቀጠና መሆኑ ቀጥሏል!!!
ሀብታሙ አያሌው 
የቃላት ጋጋታውን  ወደጎን ትተን መሬት ላይ እየሆነ ያለውን በግልፅ መነጋገር ካልቻልን አደጋው የከፋ ነው። ኦነግ የታጠቀውን ማስፈታት ቀርቶ የአዲስ ወታደር ምልመላ ስልጠና እና ማስታጠቅ እንኳን ለማስቆም እየተሞከረ አይደለም። አልፎ ተርፎ ኦነግ በወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች መንግስት ነኝ የሚለውን አካል እያባረረ በመቆጣጣር በኃይል በመግዛትና አስገድዶ ከህዝቡ ገንዘብ እና መሳሪያ  በመንጠቅ  የኃይል እርምጃውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ኦነግን በተመለከተ የበዛው እሹሩሩ እና ማባበል ልክ ቢኖረው ጥሩ ይመስለኛል። ህዝብ ዝም ካለ መንግስት አሁንም ደርቦ ሊተኛ ይችላልና የህግ የበላይነት  በሌለበት የማባበል ፖለቲካ ከማፍረስ በቀር ሊሰራን አይችልም።  ከቀናት በፊት በወለጋ እና በባሌ ኦነግ የወታደር ምልመላ እና ስልጠና እያደረገ መሆኑን በፌስቡክ ገፄ መለጠፌ ይታወቃል። ቀጥሎ ያለውን የዜና ዝርዝር ግን ከኢሳት ገፅ ያገኘሁት ነው።
“በቄለም ወለጋ ወረዳ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች ኦነግ እንደሆኑ የሚገልጹ ወታደሮች ነዋሪዎችን የግል የጦር መሳሪያዎችን እንዲያስረክቡና ገንዘብም እንዲሰጡ እያስገደዱ ነው ( ኢሳት ዜና መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ/ም ) ኢሳት ያነጋገራቸው በቄለም ወለጋ ደምቢዶሎ አካባቢ ፣ በሰዮ ወረዳ፣ ወልጋይ፣ ቢቢካና ቀስሪ መንደሮች የሚኖሩ በ1977 ድርቅ ወቅት ከወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ሄደው የሰፈሩና በአካባቢው ለአመታት የኖሩ ዜጎች ፣ በአካባቢው የሚንቀቀሳቀሱ ወታደሮች፣ “ከአሁን በሁዋላ አካባቢውን የሚያስተዳድረው ኢህአዴግ ሳይሆን እኛ ነን፣ ኢህአዴግን አናውቀውም፤ የግል የጦር መሳሪያ ያላችሁ፣ መሳሪያችሁን አስረክቡ፣ ገንዘብም ክፈሉ” እያሉ እንደሚያስገድዱዋቸው ገለጸዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት የቀበሌ አስተዳደሩን የኦነግ ታጣቂዎች ተረክበው እየሰሩ ሲሆን፣ የኦዴፓ መሪዎች በአካባቢው ባለመኖራቸው የደህንነት ስጋት ገጥሟቸዋል። መንግስት እውቅና ሰጥቶን ለረጅም ጊዜ የታጠቅነውን የነፍስ ወከፍ መሳሪያ አስርከቡ መባላቸውን የተቃወሙት ነዋሪዎቹ፣ መንግስት ፈቅዶ የታጠቅነውን መሳሪያችሁን አስረክቡ ቢለን ለማስረከብ ፈቃደኞች ነን ብለዋል።
የኦነግ ወታደሮች ህዝቡን እየሰበሰቡ ኢህአዴግ እንደማያውቁትና ማንኛውንም ነገር ለኦነግ ወታደሮች እየነገሩ መፍትሄ እንደሚያገኙ እየተናገሩ መሆኑንም ያነጋገርናቸው በርካታ ነዋሪዎች ተናግረዋል። በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ የመንግስት ሹም አለመኖሩን፣ ትናንት ምሽት የቀበሌውን አስተዳደሪ ይዘው በመምጣት መሳሪያ አላችሁ ወይ እያሉ ሲጠይቁ ማምሸታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። የኦዴፓ የገጠር ዘረፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ኦነግ ትጥቁን ካልፈታ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ መጻፋቸው ይታወቃል።
 
Filed in: Amharic