>

ብሄርተኛ ስትሆን የምታጣው ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሚያመዛዝነውን የአዕምሮህን ክፍል ጭምር ነው!!! (ፋሲል የኔአለም)

ብሄርተኛ ስትሆን የምታጣው ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሚያመዛዝነውን የአዕምሮህን ክፍል ጭምር ነው!!!
ፋሲል የኔአለም

ኦነግን ስትቃወም፣ “የኦሮሞን ህዝብ ስለምትጠላ” ነው እንደሚባለው ሁሉ፣ አብይንና ለማን  ስትደግፍ  ደግሞ “የኦሮሞን ህዝብ ስለምትወድ ነው” መባል ነበረበት።  እንዲህ አይነቱ አመክንዮ በብሄርተኞች ዘንድ አይሰራም፤ ብሄርተኛ ስትሆን የምታጣው ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሚያመዛዝነውን የ አዕምሮህን ክፍል ጭምር ነው።  ብሄርተኛ ጥላቻ ላይ እንጅ ፍቅር ላይ አይኑ አይበራለትም፤ ለዚህም ነው የሌላ ብሄር አባል ሆነህ ፣ የእሱን ብሄር አባል ስታደንቀው ሲሰማህ የሚነስረው። የአንተም ብሄር አባል ቢሆን የሌላውን ብሄር አባል በማድነቅህ በ” ከሃዲነት” ይፈርጅሃል፣ ወይም ሌላ ስም ይሰጥሃል። ኦነግን መቃወም  ታላቁን የኦሮሞ ህዝብ ይቅርና አቶ ዳውድ ኢብሳን እንኳን መጥላት ማለት አይደለም።  የምንጠላው አስተሳሰብን እንጅ አስተሳሰቡን የተሸከመውን ሰው መሆን የለበትም። እኔም ሆንኩ እንደኔ አይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች የኦነግን አስተሳሰብ የምንጠላው፣  አለም ወደ አንድነት እየመጣ ባለበት በዚህ ዘመን፣ “መገንጠል” የሚለውን አጀንዳውን ከፕሮግራሙ ላይ ስላልፋቀ እንድንጠራጠረው ስለሚያደርግን  ነው።

ለማና አብይን የወደድናቸውም ለአፍሪካ የሚበቃ ራዕይ ይዘው ስለመጡ እንጅ ኦሮሞ ስለሆኑ አይደለም፤ ከዚህ ራዕያቸው አፈግፍገው ብንቃወማቸው፣ “ ኦሮሞ ስለሆኑ ተቃወሙዋቸው” ልንባል አይገባም።  ሰው በሰውነቱ፣ ወይም ህዝብ በህዝብነቱ አይጠላም። አንድን ድርጅት ስትቃወም ያንን ህዝብ እንደምትጠላ ተደርጎ የሚቀርበው ፍረጃ በህወሃት ጊዜ አልሰራም፣ ለወደፊቱም አይሰራም። መቆምም አለበት። የፖለቲካ ድርጅት ማለት የተወሰነን ህዝብ ፍላጎት የሚወክል እንጅ፣ የአጠቃላይ ህዝብ ወኪል ነው ማለት አይደለም። እንደሱማ ከሆነ ለዛ ብሄር እንታገለላን የሚሉ ሌሎች ድርጅቶች፣ ዋጋ አይኖራቸውም ማለት ነው። ለምሳሌ እንደ ኦነግ ሁሉ ለኦሮሞ መብት እንታገላለን የሚሉ ከ7 በላይ ድርጅቶች አሉ፤ ኦነግን መቃወም የኦሮሞን ህዝብ መቃወም ተደርጎ ከተቆጠረ፣ እነዚህ ከኦነግ የተለዬ አስተሳሰብ ይዘው የተደራጁ ድርጅቶች የኦሮሞ ጠላት ሊባሉ ነው? ደግሞስ ማን ነው ጠላት፣ ማነውስ ጠላት ባይ?  በዲሞክራሲ መንገድ ከተመረጠ የአጠቃላይ ህዝብ ወኪል መሆን የሚችለው መንግስት እንጅ አንድ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም።

አንድ በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ የፖለቲካ ድርጅት ሲተች፣ ተቺው ኢትዮጵያን ስለሚጠላ ነው ተብሎ እንደማይወገዘው ሁሉ፣ አንድ የብሄር ድርጅት ሲተችም፣ ቲቺው የዚያን ብሄር አባል ስለሚጠላ ነው ተብሎ መተቸት እንደሌለበት  የብሄር ድርጅቶች ለአባሎቻችሁ ማስተማር ይጠበቅባችሁዋል።

Filed in: Amharic