>
5:13 pm - Monday April 19, 7943

ዕድሳቱ ያልተጠናቀቀ ‹ወንጀለኛ ድርጅት› አስተማሪና መካሪ የመሆኑ ስላቅ (ከይኄይስ እውነቱ)

ዕድሳቱ ያልተጠናቀቀ ‹ወንጀለኛ ድርጅት›

አስተማሪና መካሪ የመሆኑ ስላቅ

ከይኄይስ እውነቱ

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰሞኑን የወያኔ ጉባኤ በጥሞና የተከታተለው የወያኔ አገዛዝ በተከለውና ባስፋፋው መርዛማ የጎሣ ፖለቲካና የዚሁ ውጤት የሆነው ‹ክልል› የተባለ ዲያቢሎሳዊ አጥር ምክንያት የተፈጠረው ሥር የሰደደ ጥርጣሬ፣ አለመተማመን፣ ጥላቻ፣ የታመቀ የቂምና በቀል ስሜት፤ እንዲሁም በሽብርተኛው ሕወሓትና ለሱ በመሣሪያነት በሚያገለግሉ ጽንፈኛ መንደርተኞችና በጥቅም የታወሩ ቡድኖችና ግለሰቦች እየተፈጸመ ያለው በዓለም ደረጃ አስደንጋጭ የሆነ የዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል (ሞት፣ የአካል ጉድለት፣ እንግልትና ባይተዋርነት) እየከፋ መምጣትና ያስከተለው አሳሳቢ የአገር አለመረጋጋት፤ ይኸውም በአገር ህልውናና አንድነት ላይ የደቀነው አደጋ ወያኔዎች በሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ምክንያት ወደለየለት መተላለቅ እንዳይሻገር እንጂ ለወያኔ/ኢሕአዴግ ካለው በጎ አመለካከት ወይም የ27 ዓመታቱ የግፍ አገዛዝ ሳያንስ ዳግም በዚህ … ድርጅት ለመገዛት ከመፈለግ አለመሆኑን ሕዝብም ወያኔዎቹም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

አለመታደል ሆኖ ለሦስት ዐሥርት ለሚጠጉ የሰቆቃ ዓመታት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ያዋረደው፣ ሊማር ሊመከር ያልፈቀደው በአመዛኙ የደናቁርት ሎሌዎች ስብስብ፣ በየትኛውም መመዘኛ ኢትዮጵያን ለመምራት ብቃት ያልነበረው/የሌለው ነውረኛና ወንጀለኛ ድርጅት የኢትዮጵያን መጻዒ ዕድል ወሳኝ ሆኖ ብቅ ማለት መጪውን ጊዜ በጥርጣሬና በደበዘዘ ተስፋ እንዳየው አድርጎኛል፡፡

መቼ ይሆን በቃኝ ማለትን የምንማረው? 27 ዓመታት የደረሰብን ግፍና በደል በቂ አይደለም ወይ? አረመኔውን ሕወሓት በውስጡ ባቀፈውና ገዢ ‹ግንባር› ነኝ በሚለው አካል በድርጅትና በግለሰብ ደረጃ ያሉ አእላፋት ወንጀለኞች ለፍርድ ሳይቀርቡ፤ ብሔራዊ ዕርቅና ይቅርታ ሀገር አቀፍ ተቀባይነት ባለው ደንብና ሥርዓት ሳይከናወን ራሱን የኢትዮጵያ ታዳጊና ‹ጀግኖች› ስብስብ አድርጎ (2ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ዜጎች በተፈናቀሉበት አገር) ከበሮ ሲደልቅ የሰነበተው፤ 3 የጎሣ ሎሌ ድርጅቶችን ፈጥሮ በእነዚህ መሣሪያነት የአገራችንን ማኅበረ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ምስቅልቅሉን ያወጣው፣ ሲዖልን በምድር ባለማመደ የተራ ወንበዴዎች ስብስብ በሆነው ሕወሓት ሲመራ የቆየ ድርጅት ነው እኮ ስሙን…. ይጥራውና ኢሕአዴግ ተብሎ የሚታወቀው፡፡

እንደሚታወቀው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ (ከወያኔ ትግሬ፣ በአሽከርነት ካደሩለት 3 የጎሣ ድርጅቶችና በነዚሁ ዙሪያ የተሰባሰቡ ሆድ አደሮች በስተቀር) የወያኔ/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመናትን የሚያስታውሰው ጨለማና ድንቁርና የሠለጠነበት፣ የዋይታና እሮሮ ጽዋ ሞልቶ የፈሰሰበት፣ በማኅበረ ኢኮኖሚና በፖለቲካው የማይጠገኑ/ለጥገና እጅግ አዳጋች የሆኑ ድቀቶች የተስተዋሉበት፣ የዕሤት ሥርዓቶቻችን ባስደንጋጭ ሁናቴ የተናጉበት፣ ፋሽስት ጥልያንን ማረኝ ያሰኘ በታሪክ ጥቁር መዝገብ ሠፍሮ የሚኖር የባከነ ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡

የዶ/ር ዐቢይ አገዛዝ የሚነግረን ገና ዕድሳቱ ያላለቀለትን፣ የወያኔ ትግሬ መክሥተ ደደቢትን ‹ሕገ መንግሥት› ብሎ የተቀበለ፣ አገርን በሚያጠፋ የጎሣ ፌዴራሊዝም÷‹ክልል› የተባለ የጸብና ጥላቻ ግድግዳን በመላው ኢትዮጵያ ገድግዶ በአትድረሱብኝ መንደርተኝነት መርዘኛ አስተሳሰብ የተበለከውን፣ ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› የሚባል ጣዖት አቁሞ ቀን ከሌት በመስገድ የወገኑን ሰውነትና ዜግነት ያልተቀበለውን÷ በዚህም ምክንያት በሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ባገራቸው ባይተዋር የሆኑበትን፣ ሥር በሰደደ ንቀዘት የበሰበሰውን፣  የስድስት ወር ዕድሜ ያለውን ጨቅላ የጎሣ ግንባር ከሆነ ያስተዛዝበናል (የ27 ዓመታቱን ከሆነ ደግሞ እንኳን ባደባባይ ሊኩራሩበት መደበቂያ የሚፈልጉለት ነው)፡፡ ከዚህ አንፃር ዶ/ር ዐቢይ በአዋሳ ያደረገው ንግግር ለሱ ስብእና የማይመጥን÷ ከቅንነት ፖለቲካ (የሚባል የለም ካልተባለ በስተቀር) ጋር የማይሄድ ÷ውኃ የማይቋጥር ‹‹የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተብዬው›› የሚደሰኩረው ዓይነት ግልብ የፕሮፓጋንዳ ንግግር ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ‹ቆሻሻ› መሆኑን እያወቅንና እየተናገርን መልሰን መላልሰን እዚያው ‹ቆሼው› ውስጥ ለምን እንገኛለን? ወይስ ይህ ቆሻሻ ፖለቲካ የእስካሁኑ አገራዊ ጥፋት ሳያንስ እንደ አዲስ አበባው ‹ቆሼ› በላያችን ላይ ተንዶ ጨርሶ እስኪያጠፋን ነው የምንጠብቀው?

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቆሻሻነት ታሪክ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም አገራዊ የጋራ ዕሤቶችን፣እምነቶችንና ባህሎችን ያላገናዘበ፣ መጠላለፍና ጥላቻ፣ ዱለትና መጠፋፋት፣ ተንኮልና ፍረጃ፣ ድንቁርናና ባዶ መፈክር፣ ሐሰትና ዕብለት፣ በሥልጣን ፍትወት መስከርና መታወር፣ የግል ጥቅምና መተዳደሪያ መሣሪያ መሆን፣ ከሕዝብ ጥቅም በተቃራኒው መቆም፣ ወዘተ መገለጫዎቹ ሆነው፤ እነዚህ የዕብደት መገለጫዎች ከተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ጀምሮ እየጎላ መጥቶ በዘመነ ወያኔ ትግሬ (በከፋፍለህ ግዛና መሬት ወረራ) አገርና ሕዝብን መጥላት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ለመሆኑ ባለፉት 27 ዓመታት በነበረው የወያኔ ትግሬ አገዛዝ ባገር ውስጥ ትርጕም ባለው መልኩ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ማኅበራት ነበሩ ወይ? ኢሕአዴግ የሚባለውን ሽፋን ትተን በመላው ኢትዮጵያ ሲፈነጭባት የከረመው ከትግራይ ክ/ሃገር የበቀለ አንድ አናሳ የጎሣ ድርጅት አልነበረም ወይ? ቆሻሻ በሆነው የፖለቲካ ባህላችን ምክንያት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች የራሳቸው ግዙፍ ድክመት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚህ ድርጅቶች በጭራሽ እንዳይላወሱ እግር ተወርች ቀፍድዶ እያሳደደ÷ እያሰረ÷እየሰወረ÷እየገደለ (በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ) በውጭ አገር ጭምር በአገዛዙ የግል ደኅንነቶች አማካይነት የተሠራውን የሽብርና ውንብድና ተግባር ከቶ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በተቃራኒው ወያኔ ትግሬ በኢትዮጵያ ሕዝብና ሀብት አሉ በተባሉ ጎሣዎች ቊጥር ልክ የጎሣ ፓርቲ አቋቁሞላቸው÷ ላንዳንዶቹም ታማኝ ሆድ አደሮች በ‹ኅብረ ብሔራዊነት› ሽፋን ፋይናንስ እያደረጋቸው ባገር ውስጥ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ኢትዮጵያ በተባለች ግልጽ እስር ቤት የነበሩትንና እውነተኛ ተቃዋሚ ለመሆን የሚጥሩትን ያኮላሸው ማነው? ወያኔ አይደለም? ዛሬ ደርሶ በወንጀል ተጠያቂ የሆነ ድርጅት ተቃዋሚዎችን በድክመት ለመክሰስ፤ አልፎ ተርፎም ልምከራችሁ፣ ልምዴን ላካፍላችሁ፣ ላሠልጥናችሁ/ላስተምራችሁ የሚለው የትእቢት ንግግር ታላቅ ስላቅ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ይህ ወያኔ/ኢሕአዴግን በእጅጉ ሊያሳፍር ይገባል፡፡ ወያኔ/ኢሕአዴግ ማለት እኮ ትናንት አመራር ላይ ብቅ ያሉት ለማና ዐቢይ ብቻ አይደሉም፡፡ ዝርዝሩ ውስጡን ለቄስ ወይም ለማያውቁሽ ታጠኚ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ድርጅታችሁና የማይገባ ጥቅም ያገኙ ደጋፊዎቻችሁም እንዲሁ፡፡ ከጎሣ ከለላ ወጥታችሁ በአሳብ ገበያ ተወዳደሩና እንያችሁ፡፡ በጎሣ ፖለቲካና ፖለቲካን በዚሁ መሠረትነት የሚያራምዱ ቡድኖች (ከመነሻው የ‹ፖለቲካ ፓርቲዎች› ባለመሆናቸው) መካከል የምርጫ ውድድር የሚባል ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም የወድድሩ መሠረት የእኔ ነገድ/ጎሣ ካንተ ይበልጣል የሚል ድንቁርና ነውና፡፡ እንዲህ ከሆነ በጎሣ ከተደራጁ የፖለቲካ ቡድኖች ምንድን ነው የምንማረው? የጎሣ ፖለቲካ ቡድኖች እንኳን ታላቋን ኢትዮጵያ፣ ነገድ/ጎሣቸውን የሚወክሉ ድርጅቶች አይደሉም፡፡ ለዚህም ለአንድ ጎሣ ጎሣውን እንወክላለን የሚሉ በርካታ ድርጅቶች መኖራቸው ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ጎሣዎች እንዳሏት ይነገራል፡፡ በትንሹ ለእያንዳንዱ ጎሣ ሁለት ድርጅቶች ቢኖሩት 160 የጎሣ ፖለቲካ ድርጅቶች ሊኖሩን ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ተቃዋሚዎቹን ሰብሰብ በሉ ብሎ ከመምከሩ አስቀድሞ የጎሣ ድርጅቶችን በራሳቸው የሚተማመኑና ለሥልጣን ተገቢ ያልሆነ አቋራጭ መንገድ ከሚፈልጉ በአሳብ ዙሪያ ተሰባሰቡ ቢል የቀና ነበር፡፡

የዐቢይ አገዛዝ (የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም በአገዛዝ ሥር ነው ያለው፡፡ ዐቢይ የወያኔ አገዛዝ ተመራጭ እንጂ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሕዝብ ፈቃድ የተሰየመ ጠ/ሚ አለመሆኑ ይታወቃል) በሊቀመንበርነት ከሚመራውና የግፍና ጭቆና ምልክት ከሆነው ‹ግንባር› አሻግሮ እውን አገርንና ሕዝብን የማስቀደም ዓላማ ካለው፣ የሚመራውን ድርጅት ከመንደርተኝነት አውጥቶ በአሳብ÷ በፍልስምናና ርእዮተ ዓለም (‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ› ከሚባለው ተረት ተረት ወጥቶ) የተመሠረተ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ማኅበርነት (የጎሣ ድርጅቶች ውህደት ከጎሠኝነት  አመለካከት መውጣት ማለት አይደለም) በመለወጥ ከሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በእኩል ሜዳ በእኩልነት ለመወዳደር የሚያስብ ከሆነ በእኔ እምነት የሚከተሉትን ዐበይት ተግባራት በቅንነት ማከናወን ይኖርበታል፡፡

1ኛ/ የአገራዊ ጉባኤ አስፈላጊነት

   ስለ ኢትዮጵያ መጻዒ ዕድል ያገባኛል የሚሉ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በማናቸውም መልኩ የተደራጁ ባገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኃይሎችን (ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበራትን፣ የማኅበረሰብ ተቋማትን፣ የእምነት ተቋማትን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ ወጣቶችን፣ የሙያ ማኅበራትን፣ አገር ወዳድ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦችን ወዘተ) የሚሳተፉበት አገራዊ ጉባኤ በመጥራት፣ በተከታዮቹ አንኳር አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጎ ቀጣዩን ጕዞአችንን በማያጠራጥር ሁናቴ የሚያመለክቱና ለፍኖተ ካርታ ዝግጅት ወሳን ግብአቶች የሚሆኑ ውሳኔዎች ቢተላለፉበት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ሀ/ አገርን በአስተማማኝ ሁኔታ ስለማረጋጋት፤ ሽምግልናውንና ስብከቱን ለሚመለከታቸው ተቋማት በመተው ሕግና ሥርዓትን ማስከበር፡፡ የዘር ፖለቲካ ባመጣው ጦስ ከአራቱም ማዕዝናት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ወደኖሩበት ቀያቸው ባስቸኳይ መመለስና ማቋቋም፤ዜጎች የማንም ፈቃድ ሳያስፈልጋቸው ለሕግ የበላይነት ብቻ በመገዛት በመረጡት የኢትዮጵያ ግዛት የዜግነት ወይም የአገር ባለቤትነት ሙሉ ክብራቸውና መብታቸው ተጠብቆ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በፌዴራልም ሆነ በግዛት ‹መንግሥታት› ደረጃ ያሉ የሥልጣን አካላት በኃላፊነት ስሜት እንዲሠሩ፤ ለዚሁ ዓላማ ሌሎች የኅብረተሰቡ (ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና የማኅበረሰብ) ተቋማት በየሚገኙበት አካባቢ በንቁነት የሰላም ዘብ (vigilante) በመሆን ድርሻቸውን ባግባቡ እንዲወጡ ማድረግ፤

ለ/ ለድርጅትም ሆነ ለአባላት ውገና ሳይደረግ፣ ባገርና በሕዝብ ላይ የተፈጸሙ በይቅርታ የማይታለፉ ወንጀሎችን – ለአብነት ያህል ማንነትን መሠረት ያደረጉ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን (በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያስጠይቁ የሚችሉ ጭምር)፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን፣ ባገር ክህደትና ኢኮኖሚ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን፣ ድርጅታዊ/መንግሥታዊ ሽብርተኝነትን ወዘተ – ለፍትሕ እንዲቀርቡ በማድረግ ድርጊቱን የፈጸሙ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰብ አባላት ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ በማድረግ ለወደፊቱ ምሳሌ የሚሆን የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና የተጠያቂነትን ባህል ማስፈን፤

ሐ/ ትክክለኛ የመዝጊያ ምዕራፍ (proper closure) ያልተበጀለትን የቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር አስከፊ የታሪካችን ጠባሳ ጨምሮ ባለፉት 27 ዓመታት የተፈጸሙትን ግዙፍ አገራዊ ጥፋቶች ተከትሎ በማኅበረሰባችን መካከል የተፈጠሩ ቁርሾዎችን፣ መቃቃሮችን፣ የቂምና በቀል ባጠቃላይ በጠላትነት የመተያየት ስሜቶች ያየሉበትን የጨለማ ምዕራፍ ዘግቶ ባዲስና ቀና መንፈስ እንዲሁም በብሩህ ተስፋ ለመጀመር ሥርዓት ባለው መልኩ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት በሀገርአቀፍ ደረጃ እንዲፈጸም ማድረግ፤

መ/ በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ረገድ ጥገናዊ ሳይሆን መሠረታዊ ለውጥ ማድረግ፡፡ ይህም ከድርጅታዊ አሠራር የፀዳ መሆኑን ማረጋገጥ፡፡ ተቋማቱን ባዲስ መልክ ከማዋቀር ጀምሮ ዓላማቸውን ባግባቡ ለማስፈጸም የሚመደቡት ኃላፊዎችም ሆኑ ሌሎች ሠራተኞች የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆናቸውን ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡ ከሚቋቋሙት ወይም መልሶ ከሚዋቀሩት ተቋማት ጎን ለጎን እነዚህ የዴሞክራሲ ተቋማት ዘለቄታ እንዲኖራቸውና ያለማቋረጥ እንዲሻሻሉ ለማገዝ በማኅበረሰብ ተቋማት ወይም በግሉ ዘርፍ የፖሊሲም ሆነ በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ድርጅቶችን (thinktanks) ማቋቋም፡፡

ሠ/ ታሳቢ አድርጌ የተነሳሁት የዐቢይ አገዛዝ አገርንና ሕዝብን ያሰቀድማል በሚል መነሻ በመሆኑ፣ በእኔም ሆነ በብዙኃኑ እምነት ካገር የማረጋጋቱ ሥራ ጋር የተፈናቀሉ ዜጎች መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ የማድረጉ ሥራ እና ቢያንስ ለምርጫው ወሳኝ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማትን በጥሩ መሠረት ላይ ቦታ እንዲይዙ ለማድረግ ጊዜ ስለሚያስፈልግ፣ ወያኔ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ሳንታሠር በትንሹ የምርጫውን ጊዜ ባንድ ዓመት ማራዘሙ አሰፈላም ተገቢም ይመስለኛል፡፡

ረ/ ተረፈ-ወያኔዎችን ከአፍራሽ ድርጊታቸው እና የጥላቻ ንግግርና ቅስቀሳቸው እንዲታቀቡ አስፈላጊውን የሕግ ርምጃ መውሰድ፤ በሰላም የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ያለአንዳች ወከባ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ በፈለጉት የኢትዮጵያ ክፍል ተንቀሳቅሰው ሕዝብን እንዲቀሰቅሱ÷ጽ/ቤት እንዲከፍቱ፣ ማናቸውም ሕጋዊ ዓላማዎቻቸውን ሥራ ላይ እንዲያውሉ በፌዴራልም ሆነ በግዛት ደረጃ ያሉ የመንግሥት አካላትና ኃላፊዎቻቸው እንዲሁም ነዋሪው ሕዝብ አስፈላጊውን ዋስትና እንዲሰጣቸውና ጥበቃ እንዲያደርግላቸው፡፡

2ኛ/ የሕግጋት ለውጥ እና ማሻሻያ

ሀ/ የይስሙላው የወያኔ ትግሬ ‹ሕገ መንግሥት›

  ከነጮች እርጥባን ለማግኘት በማሰብ ካካተታቸውና ተግባራዊነት ከሌላቸው ‹የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች› ድንጋጌዎች ውጭ ሕዝብ ወይም ተወካዮቹ ያልተሳተፉበት፤ ኢትዮጵያን ለመበታተን ሆን ተብሎ ታስቦበት የተቀረፀ፤ የአገሩ ባለቤት ማን መሆኑ የማይታወቅበት፤ በሀገረ መንግሥት ምሥረታ ቀደምት የሆነችውን እና ሺህ ዓመታትን ባስቆጠረ የአገር ግንባታ ሂደት ብሔራዊ ማንነትን ከብሔራዊ ቋንቋ ጋር፣ ማኅበረሰባችን የተፈተለበትን ድርና ማግ የሠሩትን መልካም የጋራ ዕሤቶች ከጋራ ሥነልቦና ጋር፤ በውስጥ ፍልሰት÷ በንግድ ልውውጥ÷ በባህል ውርርስ÷ በጋብቻ÷ በግዛት መስፋፋት÷ በውስጥ ግጭት/ሽኩቻ ወዘተ መስተጋብር ተቀይጦና ተዋሕዶ የኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለፍላጎታቸው የተሰባሰቡ የጎሣ ጥርቅሞሽ አድርጎ የሚመለከተውን ‹ሕገ አራዊት› ‹ሕገ መንግሥት› ብሎ መጥራት ተገቢ ባለመሆኑ፤ ለሞት የሚያበቃ ነቀርሳ የሆኑትን የጎሣ ፌዴራሊዝም (ይኸውም ከ50 በላይ የሚሆኑ ጎሣዎችን ‹ደቡብ› ብሎ የአቅጣጫ ስያሜ በመስጠት ያልተሟላና የሐሰት መሆኑ የተመሠከረበት) እና ‹ክልል› የተባለ የአስተዳደራዊ ሳይሆን የመለያያ÷ የመከፋፈያና የጥላቻ አጥር በማኖር÷ በኢትዮጵያ ውስጥ 9 ‹አገር-አከል› ግዛቶችን በመፍጠር ዜጎችን ባገራቸው (ነባር፣ መጤና ሠፋሪ በሚል) ባይተዋር በማድረግ  ለማያቋርጥ የእርስ በርስ ግጭት የዳረገ፤ ወዘተ ባጭሩ ወያኔ ኢትዮጵያውያንን በእጁ ጭብጥ በእግሩ ርግጥ አድርጎ÷ እንደ ሰም አቅልጦ እንደ ገል ቀጥቅጦ ለገዛበት ፋሺስታዊ አገዛዝ መሠረት የሆነ የባርነት ወረቀት (‹‹የዕዳ ደብዳቤ››) እንዴት አገር የሚመራበት÷ ከዜጎች ቃል ኪዳን የሚፈጠምበት የሕገ መንግሥት ሰነድ መሆን ይችላል? ዶ/ር ዐቢይ ይህንን የወያኔ ትግሬ የግል ፕሮግራም ለፖለቲካ ፍጆታ ከሚደረግ ንግግር ባለፈ የ‹ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት› ነው ብሎ ካስተባበለ ትልቅ አደጋ ውስጥ ነን ያለነው፡፡ ተስፋና እምነቴ ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ይህንንም ተስፋ ይዤ ከለውጡ መሠረታዊ ርምጃዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ይህንን የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› ሕዝብ በሚሳተፍበትና በውሳኔ ሕዝብ በሚያፀድቀው አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት የመተካት ዐቢይ ተግባር መሆን ይኖርበታል የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ፡፡ የዐቢይ አገዛዝ (የሚወክለው የጎሣ ‹ግንባር›) አዲስ ሕገ መንግሥት የማርቀቁን ጥያቄ በአዎንታዊ መልክ ካላስተናገደው በነቀርሳነት የሚታዩትን (በተደጋጋሚ በብዙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችና የፖለቲካ ተንታኞች የተነሱትን) ላገር ህልውናና ለሕዝብ አብሮነት ጠንቀ የሆኑ ድንጋጌዎችን ማሻሻል በሌሎች መስኮች ለሚደረጉ የለውጥ ርምጃዎች ኹሉ ወሳኝ መሆኑን ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ይህ አስተያየት ወያኔ ትግሬ ጽፎ ለየግዛቶቹ የሰጠውን የይስሙላ ‹ሕግጋተ መንግሥት› ኹሉ ይመለከታል፡፡

ለ/ ሌሎች ሕጎች

  ወያኔ/ኢሕአዴግ ለግፍና የጭቆና አገዛዙ ሽፋን አድርጎ የተጠቀመባቸው፣ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብሎ በይስሙላው ‹ሕገ መንግሥት› ያካተታቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎችን የሚፃረሩ በርካታ ‹ሕጎች› አውጥቶ በሦስቱም የአገዛዙ የሥልጣን አካላት (በይስሙላ ‹‹ሕግ አውጭው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው››) ‹ሕገ ወጥ ሕጎች› ተግባራዊ ሆነው ዜጎች ቁም ስቅላቸውን አይተዋል፡፤ በተለይም በአገዛዙ አሸባሪ የደኅንነትና ሌሎች የሕግ የሕግ አስከባሪ ተብዬዎች (ቊጥራቸው ቀላል በማይባል የወያኔ ፖሊስና መከላከያ አባላት ጭራቆች (monsters) አማካይነት በየወህኒ ቤቱና ባደባባይ የተፈጸመው ስቃይ ቀደም ሲል በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች÷ በሰመጉና በጥቃቱ ሰለባዎች፣ ድኅረ ዐቢይ አገዛዝ ደግሞ በብዙኃን መገናኛዎች ይፋ ሆኖ ያደባባይ ምሥጢር ሆኗል፡፡ የዐቢይ አገዛዝ ከእነዚህ አፋኝ ሕጎች መካከል እንደ ፀረ ሽብርተኝነት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት የመሳሰሉት ዓዋጆች በማሻሻያ ሂደት ላይ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡ ይህ ክለሳ ሰፋ ብሎ ሌሎች ለዴሞክራሲ ግንባታ እንቅፋት የሚሆኑ ሕጎችን በሙሉ መሸፈን ይኖርበታል፡፡

3ኛ/ በውጩ ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ አስተዋጽኦ

  ዳያስጶራው – በስደት የሚኖረው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ – በኢትዮጵያ ለመጣው ጅምር ለውጥና አንፃራዊ ነፃነት ድርሻው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በቀጣይም በሙያው፣ በዕውቀቱና በገንዘቡ ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ አልጠራጠርም፡፡ ይሁን እንጂ በጅምር ወይም ገና በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የሚገኘውን የለውጥ ሂደት ጠንቃቃና ንቁ (vigilant) ሆኖ መከታተል ይኖርበታል፡፡ በሌላ አነጋገር ፊት ለፊት በምታዩአቸው የለውጥ አመራሮች ሳትዘናጉ የምታደርጓቸው ማናቸውም እገዛዎች (“Diaspora Fund”)ን ጨምሮ ወዳልታሰበና ያልተፈለገ ዓላማ እንዳይውሉ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ደም ተፍታችሁ ያገኛችሁት ገንዘብ እንደ ወያኔ ትግሬ ላሉ ሌቦች ወይም ተባባሪዎቻቸው እጅ እንዳይገቡ የቅርብ ቊጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የፈንዱ ጉዳይ ለተመረጡት ሰዎች ብቻ የሚተው ጉዳይ አለመሆኑን ጠንቅቃችሁ መገንዘብ ይኖርባችኋል፡፡ አገራችን አሁንም ያለችው በወያኔ/ኢሕአዴግ እጅ መሆኑን ከቶውንም እንዳትዘነጉ፡፡ ዛሬ ባገራችን ባሉና ወያኔ ትግሬ ለራሱ ዓላማ ማስፈጸሚያ ባቋቋማቸው ‹ተቋማት› (በካቢኔው፣ መከላከያ ሠራዊት፣ ፖሊስ፣ በደኅንነት/ፀጥታው መ/ቤት፣ ቢሮክራሲው፣ ምርጫ ቦርድ፣ ‹‹በመንግሥት የሚመራው ‹የኢትዮጵያ› የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ››፣ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች፣ ማዕከላዊ ባንክን ጨምሮ በመንግሥት ንግድ እና ልማት ባንኮች፣ በትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ወዘተ) ውስጥ መጠነኛ የግለሰቦች ለውጥ በስተቀር  ከላይኛው እስከታችኛው አመራር በአብዛኛው የሚገኙት የወያኔ ትግሬ አባላት፣ አስተሳሰባቸው በአክራሪ ጎሠኝነት የተመረዙ ግለሰቦች እና ለወያኔ ትግሬ መሣሪያ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ቀጣፊ ዘራፊዎች ባጠቃላይ ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በጋራ ወይም በተናጥል በፈጸሟቸው ወንጀሎች የሚፈለጉ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በተጠቀሱት ተቋማት ያለው ምደባ አሁንም በአመዛኙ በድርጅታዊ አሠራር የቀጠለ፤ የአገር መውደድ፣ ሙያዊ ብቃት፣ የሞራል ልዕልናን እና ቅንነትን ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ከወያኔ አገዛዝ ጋር ተባባሪ ሆነን አገር አናፈርስም በማለት በተለያዩ መስኮች ዕውቀት፣ ልምድ እና ቅንነቱ ያላቸው ዜጎች ባገር ቤት በእንክርት በእንግልት ይገኛሉ፡፡

ለማጠቃለል፣ በነገዳዊ/ጎሣዊ ማንነታችን ሳይሆን በሰውነታችንና በዜግነታችን የምንታይባት÷ በየትኛውም የአገራችን ግዛት ሳንሸማቀቅ ባገር ባለቤትነት በነፃነት የምንኖርባት÷ ለሁላችን እኩል የምትሆን÷ በሕግ የበላይነትና በሕዝብ ፈቃድ የሚመሠረት መንግሥት የሚሠለጥንባት÷ ሠርተን የምንበለጽግባት÷ የኩራትና የክብር ምንጭ የሆነች አገር ለማድረግ አገራችንን የምንወድ ኹሉ በዚህ አስተያየት የተመለከቱትን ነጥቦች በጥሞና ማስተዋሉ ጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

Filed in: Amharic