>
5:13 pm - Thursday April 19, 3027

ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ መልስ ሊሰጡን ይገባል!!! (ሀብታሙ አያሌው)

ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ መልስ ሊሰጡን ይገባል!!!
ሀብታሙ አያሌው
እራሳቸውን ኦነግ እያሉ ከሚጠሩት አምስት ድርጅቶች አንዱ የሆነው በቅርቡ አዲስ አበባ የገባው የኦነግ ሊቀመንበር  አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ትጥቅ ለመፍታት  አልተደራደርንም ትጥቅ ፈቺ እና አስፈቺ የለም”  ሲሉ አቋማቸውን ገልፀዋል። ድርድሩ የተካሄደው በአስመራ ሲሆን ከመንግስት በኩል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ  ተደራዳሪ እንደ ነበሩ ይታወቃል። ዶክተር አብይም ጉዳዩን በቅርበት ሲመራ እና ሲከታተል ቆይቷል።
ድርድሩ ምን ነበር ? ኦነግ ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት ሊገባ ቻለ፤ ትጥቅ ሳይፈታ ያሁሉ ያቀባበል ሽርጉድ እንዴት ተሰናዳ ?  የአገር መከላከያ የታጠቀ ኃይል ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ግድያ ሲፈፅም ለምን ዝምታ መረጠ? የአዲስ አበባን ወጣት በአፈሳ አስሮ  ጦላይ ለመጫን፣ ግንቦት ሰባትን ትጥቅ ለማስፈታት  አቅም ያላጣው የዶክተር አብይ መንግስት እንዴት ኦነግን ከነ ትጥቁ አስገብቶ ህፃናት እየመለመለ በባሌና በወለጋ ጫካዎች እንዲያሰለጥን ፈቀደ ? የኦሮሚያ ክልል የገጠር ፖለቲካ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ቂጤሳ ኦነግ ትጥቅ እንዲፈታ ለመማፀን የበቁት እንዴት ነው ?
የጅምላ መደመር ፖለቲካ ደጋፊዎች የመደመርን ፖለቲካ ሌላ ገፅታ እንዴት ታዩታላችሁ? ቃላት በማሽሞንሞን ህዝብና አገርን ከስጋት መታደግ አይቻልም። ህፃናት የሆኑ ተተኪ ትውልዶች በግልፅ እንደዚህ አይነት የዘረኝነት እና የጦረኝነት መርዝ እየተጋቱ እንዲያድጉ እየተደረጉ ይህን ሳያስቆሙ ኢትዬጵያ አትፈርስም በሚል ቃል ህዝብ እያስጨበጨቡ የፖለቲካ ድንዛዜ መፍጠር ጉዳቱ ለሁላችንም ነው።  የህግ የበላይነት ይከበር ህዝብ እየፈጁ ያሉ የኦነግ ወታደሮች ባስቸኳይ ትጥቅ እንዲፈቱ ይደረግ።
Filed in: Amharic