>
5:13 pm - Friday April 19, 1252

በማስተዋል እንራመድ (አሰፋ ታረቀኝ)

በማስተዋል እንራመድ

አሰፋ ታረቀኝ

“ጠላቶችህ ሁሉ ሲገፉ ሲገፉ የብረት ምሰሶ አርገውህ አረፉ”

በመጽሐፈ ምሣሌ ምዕ. 6 ቁጥር 17 “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው ፤ ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጠየፈዋለችይልናበወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚዘራይለዋል፡፡ የእግዚአብሔር ነፍስ የምትጠየፈው ጉዳይ እንደጽድቅ ተቆጥሮ የኢትዮጵያ ህዝብ የጥላቻን ስብከት በህውሃት አማካኝነት 40 ዓመት ተጋተ፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ በመሆኑ የተሰበከበትን የጥላቻ ዘመቻ ያህል አደጋው አልከፋም፡፡ በዚህ ጥላቻ እንደፍቅር በግልጽና በተቀነባበረ ሁኔታ ይሰበክበት በነበረበት የኢትዮጵያ ህዝብ 21ኛው ክፍለ ዘመን ያጋጥማል ተብሎ ለመገመት በሚያስቸግር አፈና ውስጥ በነበረበት ወቅት፤ኢሣትየተባለ የዜና ማሰራጫ ማእከል ብቅ አለ፡፡ በዓለም ዙሪያ የተበተነው ኢትዮጵያዊ ስለሀገሩ መረጃ የማግኘት እድል ተፈጠረለት፡፡ የሐገራቸው ያልተቋረጠ አደጋ ውስጥ መውደቅ ያሳሰባቸው ጀግኖች ተሰባስበው ያቋቋሙት ኢሣት ወቅታዊ መረጃ በማቀበልና ምሁራንን በማወያየት ስለሀገራችን በይበልጥ እንድናውቅና ራሣችንን መጠየቅ እንድንጀምር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ለመሰሪውና መንደርተኛው ህውሃት በተለይ ፣ ኢትዮጵያና ታሪኳን በተንሸዋረረ ዓይን የሚያዩትን ሁሉ በአጠቃላይ ፣ በማጋለጡ በኩል መጭው ትውልድ በባለውለታነት የሚመዘግበው ትልቅ ሥራ ሰርቷል፡፡

ኢሣት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ይዘርፍ የነበረው ህውሃት ያደርስበት የነበረውን ቁሳዊና ፖለቲካዊ ጫና ሁሉ ተቋቁሞ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል፡፡

“ጠላት ከሩቅ ሀገር መች ይገሰጋሳል

ከዚሁ ከቅርብህ ከጓሮ ይነሳል”

እንዲል የሐገሬ ሰው ፤ በሚገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ ሲታሰሩ የጮኸላቸው ፤ መልእክታቸውን እንዲያስተላልፉ መድረክ የሰጣቸው የጎሳ ፖለቲካ ምርከኞች ፤ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተውበታል፡፡ ብሎ ሲጀምር ከትግረኛ ተናጋሪው፣ ከአማርኛ ተናጋሪው በቅርቡም ከኦሮምኛ ተናጋሪው በኩል የስም ማጥፋት ዘመቻ በኢሣት ላይ ተከፍቶበታል፡፡

ሦስቱም ጎሰኞች በኢሣት ላይ በጋራ መዝመታቸው  እኔን መሰል ሰው አንድ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ያስገድዱታል፡፡ ለሶስቱም የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ያልተመቸች እውነት ኢሣት ጋር አለች ማለት ነው፡፡ ያቺ እውነት ደግሞ በጎሳ ፖለቲካ እብቅ ውስጥ ተሸፍና እንድትቀር የምትፈለገውና ኢሣት አዘውትሮ የሚወተውትላት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ አንድነት ናት፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያ አንድነት ደግሞ፤ የእብቅና የገለባ ብዛት ሸፍኖ የማያስቀረው ምርጥ ፍሬ ነው፡፡

በኢሣት ላይ የተከፈተውን ዘመቻ ለመለካት ካርል ማርክስ ተናገረው ተብሎ በተማሪነት ዘመኔ ይነገር የነበረ አባባል ትዝ አለኝ፡፡አንድ ነገር ሰርቼ አውጥቼ የቡርዣው ጋዜጦች ከተንጫጩ አንድ የሚጠቅም ሥራ ሠርቻለሁ ማለት ነው፤ ዝም ካሉ ግን ልፋቴ ከንቱ ሆኗል ማለት ነው፡፡ራሣቸውን የጎሳቸው  ፊት አውራሪ አድርገው የሚያቅራሩ ሁሉ ኢሣትን አይንህን ላፈር እያሉ ነው፡፡ ለፕሮፌሰር ህዝቅኤል ጋቢሳና ለአቶ በቀለ ገርባ ኢሣትፀረ ኦሮሞና ከፋፋይነው፡፡ OMN እና ጁሃር መሃመድ እየሰበኩ ያሉትመንግስተ ሰማያትን ነው፡፡ፕሮፌሰር ተባልክ ዶክተር ተባልክ ትምህርቱ አንተን ካለወጠህናሰውየተባለውን ፍጡር በሰውነቱ ሳይሆን በቋንቋው የምትመዝነው ከሆነ የለፋህበት ዘመንና የተሰጠህ የምስክር ወረቀት ከንቱ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ተምሮ ለመሰሉ የሰው ልጅ የሚጠቅም ሥራ ሰርቶ ካላለፈ ሰው ለም ይለፋል? ከከብት እረኝነት ለማምለጥ! አያድርስ ያሰኛል፡፡

ዘመቻው በበዛበት ልክ የኢሣት እየተጠናከረ መሄድ አንድ የሃገሬ ገበሬ አይበገሬ ለሆነ ጓደኛ የገጠመው መወድስ ትዝ አለኝ፡፡

“ጠላቶችህ ሁሉ ሲገፉ ሲገፉ

የብረት ምሰሶ አድርገውህ አረፉ፡፡”

ኢሣት በመላእክት የሚመራ ሳይሆን እንደማንኛችንም ሥጋ ለባሾች ድካም ባለባቸው፣ መሣሣት በሚችሉ የሰው ልጆች የሚመራ ነው፡፡ መርሀቸው ግን አንድና ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳን በሚደረገው ትግል ውስጥ ድርሻቸውን መወጣት ሲሣሣቱና ከመስመር ሲወጡ ያለርህራሄ መተቸት ማቅናት ከዚያ ውጭ ከሆነ ፤ ዝቅ ሲል መሃይምነት ፣ ከፍ ሲል ምቀኝነት ብቻ ይሆናል፡፡

 

 

Filed in: Amharic