>

ሩቅ እያሰብን ቅርብ እንዳናድር! (ቴዎድሮስ ሀይለማርያም)

ሩቅ እያሰብን ቅርብ እንዳናድር!
ቴዎድሮስ ሀይለማርያም
አብዮታዊ ዲሞክራሲ እዚህ ግባ የማይሉት የገማ እንቁላል ነው።  ያለው አማራጭ ይህን በተግባር የወደቀ የማጭበርበሪያ እሳቤ አርቆ መጣል ብቻ ነው!
   * በአንጻሩ ኢህአዲግ  የመደመር ፍልስፍና ያመቀውን  የአዎንታዊነት ፣ የአካታችነትና የሀገር ግንባታ አቅም አንጥሮ  ወደተሟላና የጠራ ርዕዮተ ዓለም ማበልፀግ ለነገ የማያድር ስራው ነው!
     ከጥቂት ወራት በፊት አምርረን ስንፋለመው የነበረው ኢህአዲግ ዛሬ በተአምር ሚናውን ገልብጦ ቢያንስ በከፊል የሀገርና ህዝብ መድህን ሆኗል። ወደድነውም ጠላነው ሀገሪቱን ከአጠራጣሪ  መስቀልያ ወደተሻለ እርከን እንዲያሻግር በአንክሮ እንከታተለውና ውሎና አዳሩ ያስጨንቀን ጀምሯል።
     የኢትዮጵያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ፍቅሩንና  አጋርነቱን የገለፀለት የጠ/ሚ አብይ መንግሥት ባለፉት ስድስት ወራት በተስፋና በስጋት መካከል ሲያንገዋልለን ከርሟል።
     አዲሱ አገዛዝ በዚህች አጭር እድሜው በዘመናት የማናልማቸውን ለውጦች እንዳሳየን አይካድም። ሆኖም እዚህም እዚያም የወያኔ ጭራቃዊ ገፅታዎች ብልጭ እያሉ አስደንግጠውናል። በየአቅጣጫው የጥፋትና የጨለማ ሃይሎች ተፅእኖ እየጎላ ፣ ዜጎችን በመቶ ሺዎች እያፈናቀሉ ፣ እየዘረፉና እየገደሉ ቀጥለዋል። ከናካቴውም ከህግም ከመንግሥትም  በላይ ነን የሚሉ ሥርዓት አልበኞች የልብ ልብ ተሰምቷቸዋል።
    መንግሥት ለህዝብ ጥያቄዎች  ምላሽ ለመስጠት ማመንታትና ዳተኝነት በማሳየቱ ምክንያት በብቃቱና ቁርጠኝነቱ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ እድል ሰጥቷል። የለውጡ አቅጣጫ ፣ የለውጡ መሪዎችና  ባለቤት ማንነት ላይ ጥርጣሬ አሳድሯል።
    በዛሬው አለት የተገባደደው የኢህአዱግ 11ኛ ጉባኤ መንግሥት  ውስጣዊ ችግሩን ፈትቶ የለውጡን ሂደት የሚያጠናክርበትንና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ገደማ እጣፈንታችንን የሚወስንበትን እድል ሰጥቶታል። ይህንን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ቢያንስ ሶስት መሰረታዊ እርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል።
    በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት  ከርዕዮተ ዓለም ውዥንብር መውጣት አለበት። አዲሱ ለውጥ የሚመራው በቀደመው ሥርዓት ውስጣዊ ኃይሎች መሆኑ ዋነኛው ተግዳሮት  የማንነት ውዥንብር ነው።  ዶ/ር አብይ  በቀጣይ የመንግሥታቸውን የስብእና እንቆቅልሽ የሚፈቱበት መንገድ የሽግግሩን ባህሪና የሀገራችንን  አጣፈንታ ይወስናል።
     በጠ/ሚሩ የትናንት ተምሳሌት ብንገልፀው አብዮታዊ ዲሞክራሲ እዚህ ግባ የማይሉት የገማ እንቁላል ነው።  ያለው አማራጭ ይህን በተግባር የወደቀ የማጭበርበሪያ እሳቤ አርቆ መጣል ብቻ ነው።
    በዚህ ፋንታ ኢህአዲግ  የመደመር ፍልስፍና ያመቀውን  የአዎንታዊነት ፣ የአካታችነትና የሀገር ግንባታ አቅም አንጥሮ  ወደተሟላና የጠራ ርዕዮተ ዓለም ማበልፀግ ለነገ የማያድር ስራው ነው።
     አዲሱ አገዛዝ ኢትዮጵያዊነትና ሀገራዊ አንድነት የህልውናው ምሰሶ መሆኑን መሳት የለበትም።  መሪዎች  በኢትዮጵያዊና ብሄረሰባዊ ማንነታቸው መካከል ያላቸውን ውዥንብር ማጥራት አለባቸው።  ከሰሞኑ በተከሰቱት ቀውሶች የፌዴራል ወንበር ላይ የተቀመጡ ሹማምንት ትዝብት ላይ የሚጥሉ ተግባሮችን ሲፈፅሙ የምንታዘበው ይህ ባለመሆኑ ምክንያት ነው።
      በበኩሌ ዶ/ር አብይን በጎሳ መለያ የማላይበትን ቀን እናፍቃለሁ። ይህ ባልሆነበት በፌዴራልና በክልል ፣ በየደረጃው በላይኛውና ታችኛው እርከኖች መካከል ጠንካራ ሰንሰለት ፣ ህብርና መናበብ ሊፈጠር አይችልም።
    ሁለተኛ መንግሥት  ገዥ ህግጋቱ ፣ ሥርዓታቱና ተቋማቱ ርዕዮታዊ ማንነቱን የሚያንፀባርቁ ማድረግ አለበት።   አዲሱ  አገዛዝ በአሮጌው ቁመናው ሊቀጥል አይችልም። የዲያሌክቲክስ ህግ ነው።
    ስለዚህም  የአብይ መንግሥት  ደፈር ያለ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ ምህንድስና ማካሄድ አለበት።  ቁልፍ ህገመንግሥታዊ መብቶችን የሚሸረሽሩ አሰራሮችን ፣ ህግጋትንና ተቋማትን ጠራርጎ ነፃና በህግ የበላይነት የሚዳኙ ማድረግ አለበት። የፓርቲና የመንግሥት መዋቅሮችን ከሌብነትና ዘረኝነት በማፅዳት በችሎታ ላይ መመስረት ይገባዋል።
   በተጨማሪ መደበኛውን  መዋቅር የሚጋፉና  ተጠያቂነት የሌላቸውን ቄሮ ፤ ፋኖ ፤ ወዘተ የሚባሉ መናፍስት  አደረጃጀቶችን ማፍረስ ወይም ህጋዊ ሰውነት እንዲኖራቸው ማስገደድ አለበት።
     በሶስተኛ ደረጃ ከላይ ከተጠቀሱት በተጓዳኝ የብሄራዊ ማህበረሰብ ግንባታው መፋጠን  አለበት። በጋራ ራዕይ ላይ የቆመ ህዝባዊ አስተሳሰብና ባህል ማበልፀግ ለብሄራዊ ህልውናችን ወሳኝ ነው።
    ለውጡ ኢትዮጵያዊነትን የሀገራዊው ትንሣኤ ምሰሶ በማድረግ ብሄራዊ መግባባትን ማፋጠን ፣ ማህበራዊ ወረትን ማዳበር ፣ አድማሱን በመላ ሀገሪቱ ማስፋትና ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ማረጋገጥ  ይኖርበታል።
    መንግሥት ሁሉንም በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ተቀናቃኝ  ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን ለበጎ አላማ አጋር እንዲሆን ማበረታታት ይገባዋል። በሩን ያለልዩነት መከፈቱ ተገቢ ነው።  ነገር ግን ግብዣው የጨረባ ተዝካር እንዳይሆን  መሰረታዊ የመግባቢያ ደንቦች መደንባት አለባቸው።
    ስለመደመርና ፍቅር ፣ ስለእውነተኛ ይቅርታ ሲባል የሀገር አንጡራ ሀብት የዘረፉ ወንበዴዎች ፣ በህዝቦች መካከል መቃቃርና ጥላቻን የሚያራግቡ በአገር ቤትም (በገንዘባችን የሚንደላቀቁ) በውጭም ያሉ ግለሰቦችና ተቋማት ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።
   እስካሁን መሃል መንገድ በመቆማችን የከፈልነው መስዋእት እየከፋ ሄዷል። ህዝብ መንግስቱ ከመልካም ወሬ ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዲሻገር እየጠየቀ ነው። የአብይ አገዛዝ ከእንግዲህ የሚወላውልበት እድል አይኖርም። ለራሱም ህልውና ሲል የሚሰጠው ምላሽ የተጠናና ቁርጠኛ እንዲሆን እንጠብቃለን።
Filed in: Amharic