>

ለውጡን ከቅልበሳ ለመታደግ የኦሮማራ ጥምረት በእጅጉ ይታሰብበት!!! (ስዩም ተሾመ)

ለውጡን ከቅልበሳ ለመታደግ የኦሮማራ ጥምረት በእጅጉ ይታሰብበት!!!
ስዩም ተሾመ
 በአጠቃላይ አሁን በሀገራችን የታየው ለውጥ መሰረቱ የኦሮማራ ጥምረት ነው። ምክንያቱም የኦሮማራ ጥምረት፡-
1ኛ፡- በሀገራችን አብላጫ ድምፅ ያላቸውን የኦሮሞና አማራ ህዝቦች የጋራ ዓላማ ለማሳካት በትብብር መንፈስ አስተሳስሯል።
2ኛ፡- በአንድነትና ብሔርተኝነት ጎራ ለይተው እርስ በእርስ ሲጠላለፉ የነበሩ የፖለቲካ ልሂቃን በጋራ ጉዳዮች ላይ እንዲተባበሩ አስችሏል።
3ኛ፡- በአማራ ኦሮሞ ተወላጆች መካከል የነበረውን የእርስ-በእርስ ግጭት አደጋ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
4ኛ፡- በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የለውጥ ንቅናቄ ወደ ሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲያድግ አድርጓል።
5ኛ፡- የሕዝቡን የለውጥ ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ ቁርጠኛ በነበሩ የኦዴፓ (ኦህዴድ) እና አዴፓ (ብአዴን) አመራሮች መካከል ጠንካራ ጥምረት ፈጥሯል።
6ኛ፡- ከ1-5 የተዘረዘሩትን ለውጦች መሰረት በማድረግ ኢህአዴግ ውስጥ የአመራር ለውጥ ለማምጣት አስችሏል።
በእርግጥ “የተጀመረውን ለውጥ ስኬትና የወደፊት ቀጣይነት በኦሮማራ ጥምረት ላይ የተመሰረተ ነው” ማለት ለብዙዎች ማጋነን ሊመስል ይችላል። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። የመጀመሪያው የኦሮማራ ጥምረት ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተመሰረተ እንደመሆኑ ለለውጡ ስኬትና ቀጣይነት ቁልፍ ሊሆን አይችልም የሚል ነው። ሌላው ደግሞ አንዳንድ ቡድኖች በለውጡ ሂደትና ቀጣይነት ውስጥ ያበረከቱትን አስተዋፅዖ ማሳነስ፣ በአንፃሩ የኦሮማራ ጥምረትን ያለቅጥ ማወደስ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ሆኖም ግን እኔ የማንንም አስተዋፅዖ የማሳነስ ሆነ የማወደስ ዓላማ የለኝም። ከዚያ ይልቅ፣ የእኔ ፍላጎት የተጀመረው ለውጥ ስኬትና ቀጣይነት የኦሮማራ ጥምረትን በማጠናከር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማሳየት ነው።
በአጠቃላይ በሃዋሳ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮችና አባላት የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ከዚህ አንፃር የተቃኙ ሊሆን ይገባል። ከላይ በዝርዝር ለመግለጽ እንደተሞከረው የኦሮማራ ጥምረት በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ለመጣው ለውጥና መሻሻል ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። በተመሳሳይ የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት ለማስቀጠል የኦሮማራ ጥምረትን አጠናክሮ መቀጠል ምርጫና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። በኦሮማራ ጥምረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ የሚችል ማንኛውም ዓይነት ነገር ለውጥን ከማጓተት ጀምሮ እስከ መቀልበስ የሚያደርስ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
Filed in: Amharic