>

ምድርን ያናወጠ ጩኸታችን ድሉን እንዳያገረኘው እሰጋለሁ! (ሰሎሞን ዳውድ አራጌ - ጎንደር)

ምድርን ያናወጠ ጩኸታችን ድሉን እንዳያገረኘው እሰጋለሁ!

ሰሎሞን ዳውድ አራጌ – ጎንደር     

                                

እንትናችን ውስጥ እንትን ገብቶበት፤

እንትን አምጭልኝ እንትን እልበት፤

አንችም ነይልኝ እንትን ትይልኝ፡፡

ይላል የኔ አባት

ነገሩ እንዲህ ነው፤ የሚዳቋ አደን የተለመደ፣ ትልቅ ግዳይና የቤተሰብ የምግብ ገፀ-በረከት ተደርጎ የሚቆጠርበት አንድ ማሕበረሰብ ውስጥ የሚኖር አንድ አዳኝ ሰው ነበረ፡፡ እናም ይህ ሰው በአንድ አጥቢያ አደን ተግባሩን ሊከውን ወደ አካባቢው ጫካ ወጣ፤ ወጥመዱንም ጣለ፤ የሚዳቋዋንም መምጫ ወይም ወጥመድ ውስጥ መውደቂያ ሰዓት ጠብቆ  ወደወጥመዱ አቀና፤ በለስ ቀንቶትም ኖሮ እኔ ነኝ ያለ የአካባቢው አዳኝ የማይታደለውን የሚዳቋ ሙክት ወጥመዱ ስር ወድቃ አገኘ፡፡

ከዚያም ያገኘውን ግዳይ ለሌላ የሃገሬው ሰው ወይም ጎረቤት ሳያሰማ የምስራቹን ለሚስቱ ብቻ አብስሮ፤ ከሚስቱ ጋር ተጋግዞ ስጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ለማስገባት ሻተ፤ በተራራውም ጫፍ ሆኖ እገሊት ው… ው… ው! ሲል ተጣራ፤ ሚስቱም ምላሽ በሰጠችው ግዜ ፤ እንትናችን ውስጥ እንትን ገብቶበት፤ እንትን አምጭልኝ እንትን እልበት፤ አንችም ነይልኝ እንትን ትይልኝ! አለ ይባላል፡፡

በዘመናችን በርካታ ጉዳዮች አሉ መሰል ቅኔ ተቀኝተን ለነሞረሽ ላናሰማቸው የሚገቡ! ምንም ግዳይ ብንጥል ስንፎክር እየተቀማን ነውና እስኪ ዝም እንበል አልያም እንትናችን ውስጥ እንትን ግብቶበት ብለን እንለፈው! በተለይ ደግሞ የዘመኑ ታጋይ ነን ባዮች (የድል አጥቢያ አርበኞች) እነሞረሽ ሊሰሙት የማይገባውን ነገር ሁሉ እኛ ነን ያደረግነው በማለት ማግሳት አብዝተዋል፤ የግዳዩ ገፀ በረከት ከቤት (ለሃገሬው) ሳይደርስ ተቀራማቹ በዛ ለምን? እንትናችን ውስጥ እንትን ገብቶበት! ብለን በምስጢር ሳይሆን መልዕክት ያደረስነው፤ በአዋጅ ሚዳቋ ግዳይ ጥያለሁ በማለት ነበር የለፈፍነውና የሰራውም ያልሰራውም መጥቶ ይቀራመታል፤ ከላይ የጠቀስኩት የአባቴ ሃገር ሰው ግን ድሉን ለሚመለከተው ሰው ብቻ በውስጠ ወይራ ገሠሠ፤ የድሉንም ፍሬ በድካሙ መጠን አጣጣመ፡፡   

በመጨረሻም ይህችን ቅኔ የተቀኛት ሰውየ ንፉግ ስለሆነ አይደለም፤ ይልቁንም የላቡን ፍሬ ለቤተሰቡ መመገብ አንዳለበት የሚያውቅ ጀግና እንጂ፤ እኛም በልፈፋቸን ከላባችን ፍሬ ተቋዳሽ ሳንሆን እንዳንቀር፤ ምድርን ያናወጠ ጩኸታችን ድሉን እንዳያገረኘው እሰጋለሁ፡፡ ገረኘ ማለት እግር ተወርች አሰረ፡፡  

ምንም ሳንሰራ ነጋሪት ጉሰማው ገደለን፤ እንትና ጀግናው! እንትና አንበሳው! እንትን ቀያሹ፤ ወንዝ አሻጋሪው ጆሯችን ጠነዛ፡፡ ፉከራ ባሕላዊ መገለጫችን ቢሆንም ቅሉ በዘማነችን ግን አግድም ሄደ፡፡ እንትን አካባቢ ነው አሉ፤ ሰውየው ሙስሊም ናቸው፤ እግር ጥሏቸው ከአንድ ብዙ ሰው ከሚፎክርለት ቀረርቶ ሽለላው ከሚነጉድለት ሰው ቀብር ላይ ታደሙ፡፡ እናም አንዱ ፎካሪ ላይ ጆሯቸውን ጣል ቢያደርጉ፤ የጉድ ነው የተባለለት፣ በመንጋው የተጠጨበጨበለትን የፉከራ ስንኞች ሲደረድር ሰሙ፤

በሰሜን ገዳይ፣ በደቡብ ገዳይ፤

በምዕራብ ገዳይ፣ በምስራቅ ገዳይ፤  ….

ይህንም የሰሙት ሼህ የአላህ በየት በኩል የሄዱት ይተርፉ ይሆን! አሉ ይባለል፡፡ ፉከራችን ገደብም ልክም አጣና የፈጣሪ ያለህ እንዳያስብለንም እሰጋለሁ፡፡

Filed in: Amharic