>

ይህንን በሀገር እና በህዝብ ላይ እየተሰራ ያለውን እኩይ ሴራ ላለማየት የጋረደን ምን ይሆን?!? (አቻምየለህ ታምሩ)

ይህንን በሀገር እና በህዝብ ላይ እየተሰራ ያለውን እኩይ ሴራ ላለማየት የጋረደን ምን ይሆን?!?
አቻምየለህ ታምሩ
 ሕዝባችን ዐቢይ በኦሮምኛ የማይደግመውን በአማርኛ የሚናገረውን  ማጭበርበሪያ እየሰማ እየተካሄደ  ያለውን ደባ ሁሉ  እንዳያይ እንዳይሰማ  ራሱን ጋርዷል።
*  ከአገር በስተጀርባ እየተካሄደ ያለውን ደባ ላለማየት ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ ቀብሮ አንጎሉን ያደነዘዘ ሕዝብ ሁልጊዜ በእንደ ዐቢይ አሕመድ አይነት Con Artists እየተታለለ ያለውን ሲነጠቅ ይኖራል ። 
የኦነግ ቃል አቀባይ ኦቦ ቶሌራ አዳባ «ኦሮምያ» በሚባለው ክልል  ውስጥ የሚገኘው የኦነግ ሰራዊት  ከነ ትጥቁ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና «የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል»  አመራሮች ላይ የተፈጸመው ግድያ በኦነግ ሰራዊት ይፈጸማል ብለው እንደማያምኑ ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ተናግረዋል። «ኦሮምያ» የሚባለው ክልል ቃል አቀባይ ኦቦ አዲሱ አረጋም በትናንትናው እለት በፌስቡክ አካውንቱ ባስተላለፈው መልዕክት ኦነግ ሰራዊቱን ወደ ካምፕ እንዲያስገባ ጠይቋል።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባይገለጥም ከሁለቱ ሰዎች መግለጫ  የምንረዳው ነገር ቢኖር  «ደማሪው» ዐቢይ አሕመድ ኦነግ ኢትዮጵያ ውስጥ  ከነ ትጥቁ እንዲንቀሳቀስ መፍቀዱን ነው። ስለዚህ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ በምትባል አንዲት ሉዓላዊ አገር  ውስጥ የኦነግ መከላከያ  ሰራዊትና «የኢትዮጵያ መንግሥት»  መከላከያ ሰራዊት  በመባል የሚታወቁ ሁለት መከላከያ ሰራዊቶች አሉ ማለት ነው። የኦነግ መከላከያ ሰራዊት «ኦሮምያ» የተባለውን በነ በቀለ ገርባ አገላለጽ «አገር» የሚጠብቅ ሲሆን በዐብይ ዘመን ያለው  «የኢትዮጵያ መከላከያ» ሰራዊት ግን ምን እየሰራ እንደሆነ አናውቅም! ይቺ  ሀገር ወዴት እየሄደች ነው? መታለል የማይሰለቸው ሕዝባችን ዐቢይ በኦሮምኛ የማይደግመውን በአማርኛ የሚናገረውን  ማጭበርበሪያ እየሰማ እየተካሄደ  ያለውን ደባ ሁሉ  እንዳያይ እንዳይሰማ  ራሱን ጋርዷል። ከአገር በስተጀርባ እየተካሄደ ያለውን ደባ ላለማየት ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ ቀብሮ አንጎሉን ያደነዘዘ ሕዝብ ሁልጊዜ በእንደ ዐቢይ አሕመድ አይነት Con Artists አየተታለለ ያለውን ሲነጠቅ ይኖራል ።
ባለፈው ሰሞን  ዎላይታ፣ ሲዳማና ጉራጌ ዞኖች ውስጥ  ሕገ መንግሥት ተብዮው በወለደው «ዘር»ን መሰረት ያደረገ ግድያ፣ ጥቃትና መፈናቀል  ከሞተው፣  ከተጎዳውና ከተፈናቀለው  ሰው  ቁጥር የማይተናነስ ቁጥር ያለው ሕዝብ ቡራዩ ውስጥ በተነሳው  [ሕገ መንግሥት ተብዮው በወለደው] «ዘር»ን  መሰረት ያደረገ ጥቃት ሞቷል፣ ተጎድቷል፣ ተፈናቅሏል። የዎላይታውን፣ የሲዳማውንና የጉራጌውን «ዘር»ን  መሰረት ያደረገውን ግድያ፣ ጥቃትና መፈናቀል  ተከትሎ  በተከሰተው ግድያና መፈናቀል ዐቢይ አሕመድ የሶስቱን ዞኖች  አመራሮቹን ከሥልጣን እንዲወርዱ አድርጎ ነበር።
ሆኖም ግን በቡራዩ፣ በአርሲና በምዕራብ ወለጋ በተከሰተው ሕገ መንግሥት ተብዮው  የወለደው «ዘር»ን  መሰረት  ያደረገ ተመሳሳይ  ግድያ፣ ጥቃትና መፈናቀል እስካሁን በዐቢይ አሕመድ በኩል  አንድም ሰው ከኃላፊነቱ እንዲወርድ አልተደረገም፤ በዎላይታ፣ ሲዳማና ጉራጌ ዞኖች እንዳደረገው ሀሉ በቡራዩ፣ በአርሲና በምዕራብ ወለጋ ለተካሄደው ግድያና ጥቃት የየዞኑን   አመራሮች  ከሥልጣን ትወርዳላችሁ ብሎ  ሲጠይቅ አልሰማንም፤  ከነጭራሹ በዎላይታ፣ በሲዳማና በጉራጌ ዞን አመራሮች ላይ  ያደረገውን  አይነት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ  አንዳች ነገር ትንፍሽ ያለው የለም! ይህ የዐቢይ እንዳልሰማ መሆን  በቡራዩ፣ በአርሲና በምዕራብ  ወለጋ የወደቁት ነፍስ በዎላይታ፣ በሲዳማና በጉራጌ ከወደቁት ስለሚያንስ ነው? ወይንስ  እሱም እንደ መለስ ዜናዊ  “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” ሆኖበት ነው?
Filed in: Amharic