>
5:13 pm - Tuesday April 20, 2280

ከጉባኤው በሁዋላ ህወሃት ወይ ትደመራለች ወይ ትስፈነጠራለች!!! (ፋሲል የኔአለም)

ከጉባኤው በሁዋላ ህወሃት ወይ ትደመራለች ወይ ትስፈነጠራለች!!!
ፋሲል የኔአለም
ሶስቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች የሰናበቷቸውን ሰዎች ማንነት ስናይ፣  ህወሃት በአዋሳው ጉባኤ  ራሷን በራሷ ደግፋ ከመውጣት ውጭ ከሌሎች ድርጅቶች  ደጋፊዎች የማግኘት ህልሟ እንዳከተመ  እናያለን።   አዴፓ ( ብአዴን) ፍሬህይወት አያሌው፣ ከበደ ጫኔ፣ ካሳ ተክለብርሃን፣ ጌታቸው አምባዬና አጠራጣሪ ከሆኑት መካከል አለምነው መኮንን በስልት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዳይሆኑ በማድረግ ጨዋታውን በጥንቃቄ ተጫውቷል።
ደኢህዴንም እንዲሁ  ሽፈራው ሽጉጤና ሲራጅ ፈርጌሳን አሰናብቶ የህወሃትን የደቡብ እጅ ቆርጦታል። ኦህዴድ ስራውን ቀደም ብሎ ሰርቶ አሁን ሽርሽር ላይ ነው። ህወሃት ሶህዴፓን  የኢህአዴግ አባል በማድረግ የሃይል ሚዛኗን ለመጠበቅ ውጥን የነበራት ቢሆንም፣ አብዲ አሌ እስር ቤት ከገባ በሁዋላ፣ በተለይም በእሱ እግር ስር የተተኩትን ትንታግ ወጣቶች ስታይ ጥያቄዋን ከእንግዲህ መልሳ እንደማታነሳው መናገር ይቻላል። አብይ የሰራው ትልቁ ማኪያቬላዊ ስራ የህወሃትን የምስራቅ እጅ መቁረጥ መቻሉ ነው።  ህወሃት ሶስት ለአንድ የሚካሄደውን ጨዋታ እንደማታሸነፍ ብታውቅም፣ በአዳዲስ ጉልበት ተጫውታ የሚገባባትን ጎል እንደመቀነስ፣ በነባር ተጫዋቾች ለመጫወት መወሰኗ በደካማ ዳይሬክተር እየተመራች መሆኑን ያሳያል። ለነገሩ ከስር ያላሳደከውን ተጫዋች በጭንቅ ሰዓት ከየት ታመጣዋለህ??  ከሌሎች ክለቦች በብዙ ገንዘብ ተጫዋች የመግዛት እድሉም ተዘጋ ። ለማ፣ ደመቀ፣ ሙፈርያት የሚባሉት ክፉ ሰዎች ገበያውን ዘጉት።
ጌታቸው አሰፋ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ የሚደረገው ( ከተገኘ ነው) ስለ እያንዳንዱ ሰው  አለኝ የሚለውን “የደህንነት መረጃ” በማቅረብ  ህወሃት ተሰሚነት እንዲኖራት ለማድረግ የተወጠነ ስልት እንደሆነ እገምታለሁ። ጌታቸው  አሰፋ በአብይና ለማ ላይ አለኝ የሚለውን የሃሰት ፋይል ሊያወጣና እርስ በርስ እንዲጠራጠሩ፣ በጉባኤተኛውም አመኔታ እንዳያገኙና  እንዲሸማቀቁ የሚችለውን ሁሉ ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ ውጭ ይህ ሰው አዋሳ ሊሄድ የሚችልበት ምክንያቱ አይታየኝም።  ህወሃት ጌታቸው ረዳን ብዙ አታምነውም፤  ጌታቸውን በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች እንደሚሉት፣ ሰውዬው በነፈሰበት የሚነፍስ በመሆኑ ህወሃትን ወግኖ እስከመጨረሻው ላይቆም ይችላል፤ ኩርፊያውን ለማብረድ ትንሽ ስልጣን ቢሰጡት ከአብይ በላይ አብይ ሆኖ ለመውጣት የማይከበደው ሰው ነው  ይባለል።  ህወሃት ዋና አጥቂ ብላ የምታስበው አስመላሽ ወ/ስላሴን ነው።  እሱም ቢሆን፣ ከአብይ ወይም ከደመቀ አያልፍም። ያም ሆነ ይህ  በዚህ ጉባኤ አብይና የለውጡ ሃይሎች አሸንፈው ይወጣሉ። ።
Filed in: Amharic