>

መገን ወሎ!!! ይደንቃልኮ ...!! (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

መገን ወሎ!!! ይደንቃልኮ …!!
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
እኔ በግሌ “መሐመድ አሊ መሐመድ ሀሰን ኑሩ በሬንቶ. ..” እስከሚለው አውቃለሁ። ሥማችን እስከ ቅድመ-አያት ሲጠራ ኦሮሞነታችንን ያሳብቃል። አብዛኛው ወሎዬ ወደኋላ ሂዶ አያት ቅድመ-አያቶቹን ሲቆጥር የኦሮሞ ሥም ሊያገኝ ይችላል።
በንግግራችንም በርካታ የኦሮምኛ ቃላት አሉ።
አብዛኞቹ የቦታ ሥሞችም የኦሮምኛ ትርጉምና ተፅዕኖ አለባቸው።
ዘፈኖቻችንን/ዜማዎችንንና የጭፈራ ስልቶቻችንን ወስደን ካየን ደግሞ በእኛና በባቲ/ከሚሴ ኦሮሞች መካከል ልዩነት/demarcation የለም።
ይህ ማለት ግን ኦሮሞዎች ነን ማለት አይደለም። ይልቁንም ሥነ-ልቦናዊ ስሪታችን (psychological makeupኣችን) ለአማራነት ይቀርባል።
በቀድሞው ቃሉ አውራጃ ሥር ከሚገኘው ሀርቡ አካባቢ አንስቶ ደግሞ የአርጎባ ብሔረሰብ አባላት ከሌላው ጋር ተሰባጥረው ይገኛሉ። መቼም አርጎባዎችን ከዚህ – እስከዚህ የሰፈሩ ብሎ ለመግለፅ ያስቸግራል።
ወደ ሰሜን ስንሄድ ደግሞ በላስታ አማራና አገው መካከል ድንበር ማበጀት ከቶ የሚቻል አይደለም። የደቡብ ወሎ ወጣቶች ሳይቀር ሆታና እንጉርጉሯቸው የራያና የሰቆጣ ዜማ ተፅዕኖ አለበት።
ወደሰሜን ምሥራቅ ራያ አካባቢ ደግሞ አማርኛ; ትግርኛና ኦሮምኛ ተቀላቅሎ ይነገራል። የአካባቢው ሰዎች “ራዩማ” ይሉታል።
ከከሚሴና ጨፋ ሮቢት አዋሳኝ አካባቢዎች አንስቶ በባቲ; በጭፍራ; በወረባቦና በቀድሞው የጁ አውራጃ ሥር በነበሩ አካባቢዎች እንዲሁ አማርኛ; አፋርኛና ኦሮምኛ ተቀላቅለው ይነገራሉ።
ወደታች ወደ አውሳ በረሃ ዘልቀን ስንገባም ከሚሌ እስከ ኤሊዳኣር – ዲቾኡቶ; እንዲሁም ሚሌ; ዱብቲ; ዴትባህሪ; አይሠኢታና አፋምቦ ድረስ ሌላው ወሎዬ ከአፋሮች ጋር ተሰባጥሮ ይኖራል። አፋሮችም በባህላቸው/በባህሪያቸው ሌሎችን አቃፊና ሆደ ሰፊ ናቸው።
ወሎ ውስጥ ጋብቻም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች በዘር የተገደቡ አይደሉም። በመሆኑም ሁሉንም ማንነቶችና እሴቶች የሚያንፀባቅርቅ አንድ ቅይጥ ማህበረሰብ ተፈጥሯል። በወሎዬዎች ዘንድ ዘርን መሠረት ያደረገ ልዩነትና አድሎ ብዙም አይታወቅም።
ወሎ ውስጥ ሃይማኖታዊ ማንነትም ቢሆን የመከባበርና የአብሮነት መገለጫ እንጅ ልዩነትን የሚያጎላ ሆኖ አያውቅም። እኔ እንደማውቀው; በወሎ ሰዎች የጤና እክል ሲያጋጥማቸው; ወይም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን በመንፈሳዊ መንገድ ለመፍታት ለፀሎት ይቀመጣሉ። በተለምዶ “ወዳጃ” ተብሎ ይጠራል። በተለይ በጎረቤታሞች መካከል ወዳጃ ሲጠራ በክርስቲያኖችና ሙስሊሞች መካከል ልዩነት አይደረግም። ከወዳጃው ታዳሚዎች መካከል በዕድሜ ገፋ ያለ ሰው; ወይም በዚህ ልምድ ያለው ሰው (አበጋር ይባላል) ምርቃት ያወርዳል። ሌሎቹ በጋራ እጆቻቸውን ወደፈጣሪያቸው ዘርግተው “ይሁን!” ወይም “አሜን” ይላሉ። ከዚህ አንፃር “የዱበርቲ ወዳጃ” ተጠቃሽ ነው። “ዱበርቲ” የሚለው ቃል ኦሮምኛ ሲሆን የአማርኛ ትርጉሙ ሴቶች ማለት ነው። የወሎ ዱበሪቲ በዱኣ/በፀሎት አይታሙም። ማንም ቢሆን “የቂን ብሎ” (ከልቡ አምኖ) “ዱበርቲ መጀን” ካለ ሳይሽርና (ሳይድን) ሐጃው ሳይሞላ (ሳይሳካለት) አይቀርም።
ወሎ በዘመናት ሂደት የራሱ የሆነ ልዩ የማንነት መገለጫን (unique identity) አዳብሯል። ይኸ ቅይጥ ማንነቱና የጋራ እሴቶቹ ለሌሎችም ጥሩ ምሣሌ (model) ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። The Wollo modelን በአግባቡ ከተጠቀምንበት በሀገር ደረጃም በእኩልነት; በመተሳሰብና በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለመገንባትና ይበልጥ ሊያስተሳስሩን የሚችሉ የጋራ እሴቶችን ለማዳበር ጥሩ መሠረት/መነሻ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተቃራኒው/ወርዶ የወሎን ልዩ የማንነት መገለጫና እሴቶች ለመደፍጠጥና ለማጥፋት መሞከር አግባብ አይሆንም። ቢሞከርም ያልተጠበቁ ማህበራዊ; ሥነ-ልቦናዊና የማንነት ቀውሶችን ከመፍጠር ያለፈ ውጤት አይኖረውም።
ይልቁንም ወሎዬነትን ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንደማጠናከሪያ መሠረትና ሌሎችን እንደማገናኛ ድልድይ ብንጠቀምበት ሁላችንም ብዙ ልናተርፍ እንችላለን። ኢትዮጵያ ውስጥ እርስ በርስ ከመሸነጋገል ባለፈ እውነተኛና ዘላቂ አንድነትን ለመፍጠርና ለማጠናከር ከተፈለገ ከወሎ ብዙ መማርና በአጠቃላይም The Wollo Modelን መውሰድ ይቻላል።
“ወሎ የሀገር ድባብ”
የፍቅር; የአብሮነትና የደግነት ማሳያ;
የሥመ-ጥር ቀሳውስትና መሻሂኾች ምድር!!!
የነኢየሱስ ሞኣ; የነመምህር አካለወልድ. .. ወዘተ አገር;
እነአንይን; እነዳንይን; እነሾንክይን; እነገትይን; እነሸህ ሁሴን ጅብሪልን. .. ወዘተ የፈጠረች ማህፀነ-ብሩክ ምድር – ወሎ!!!
ወሎ የአማራ ማንነት የተቀረፀባት; የኦሮሞው አሻራ ያረፈባት; በሌሎችም የማንነት ህብር የተዋበችና የፍቅር መስህብ ያለባት  – “የሁሉ እኩል ሀገር” ናት ቢባል ስህተት ይሆን?
እኔ ስለወሎ ዘርዝሬ መጨረስ አልችልም። “አባይን በማንኪያ” እንዲሉ ነው – ወገኔ!!!
የሆነ ሆኖ የወሎን ፖለቲካ እዚህ አካባቢ ፈልገው። እንብርቱን ታገኘዋለህ። ወሎዬ ለፍቅርና ለአንድነት ልቡ ቅርብ ነው። ሆዱም ገር ነው። “ወሎ ገራገሩ” የተባለውኮ እንዲሁ አይደለም። አንደምታው ሰፊ ነው – ወዳጄ። ሲያመርም እንደዛው ነው። ሌላው ቀርቶ ዝምታው ያሸብራል። ነገሥታቱም “ወሎ ምን አለ?” እያሉ ሰርክ ይጠይቁ ነበር አሉ። “ምንም አላለም” ከተባለ “ይኸማ ችግር አለ ማለት ነው” የሚል መጠይቃዊ ድምዳሜ ላይ ይደርሱ እንደነበር ይወሳል።
ወሎማ ባህርኮ ነው። ባህር በውስጡ ስንት ነገር አለ መሰለህ? ወዳጄ; ይልቅ ግብዝ አትሁን! “ወሎ ገራገሩ” ቢሉህ በቀላሉ የሚታወቅ አይምሰልህ!!!
ከሞላ ጎደል. .. ይኸው ነው!!!
Filed in: Amharic