>
5:13 pm - Wednesday April 18, 1235

"የህዝብ ለህዝብ ግጭት" ዜጎችን ለማፈናቀል የተሰጠ የዳቦ ስም!!! (መሀመድ እድሪስ)

“የህዝብ ለህዝብ ግጭት”  ዜጎችን ለማፈናቀል የተሰጠ የዳቦ ስም!!!
መሀመድ እድሪስ
ራስን በራስ ማስተዳደር ባዶ መርህ አይደለም። በውስጡ የፍትህ እና የተጠያቂነት ጉዳይን በዋናነት የያዘ ነው። የፌዴራሊዝም ስርአት ቅርፅ እየያዘ ከማደጉ በፊት Local democracy ዋነኛ የመታገያ አጀንዳ የነበረው በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦችን እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ለማድረግ ነው። ዴሞክራሲን አንድ ደረጃ ወደማህበረሰቡ በስፋት ማዳረስ ሊባል ይችላል። በዚያ ውስጥ ግን ማእከላዊው መንግስት አጎደለው የሚባለው ፍትህ እና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የአካባቢው አስተዳዳሪዎችም እንዳያጎድሉ የሚያግድ የተጠያቂነት ጉዳይ መቼም የማይነጠል የዴሞክራሲ ክፋይ አብሮት አለ።
በሀገራችን እራስን በራስ ማስተዳደር በቅድሚያ”ማስተዳደር” የሚለውን ሀላፊነት የዘነጋ ነው። ክልሎች በስራቸው ያሉ ዜጎችን የልማት እና የፍትህ ጥያቄን እያሟሉ ከማስተዳደር በላይ ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዳሻቸው የመሆን መብት አድርገው ይወስዱታል። ለዚያም ነው የዜጎች መፈናቀል የአስተዳደር ጉድለት ሆኖ ከማስጠየቁ በፊት የህዝብ ለህዝብ ግጭት ተደርጎ የሚነገረንና እኛም እንደዛ አድርገን መውሰዱ የሚመቸን።
በአስተዳደር በደል ውስጥ በየ እርከኑ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት አሉ። የፍትህ ስርአቱ ጠንካራ ባልሆነበት ሁኔታ ግን የአንዱ አስተዳደር መዋቅር ተጠያቂነት ከደሙ ንፁህ ባልሆነው በሌላው መዋቅር ሊሸፋፈን የሚችልበት እድል በመኖሩ የማይታሰብ ይሆናል። የዜጎች ግድያ እና መፈናቀል የዜጎቹ የራሳቸው ችግር ነው እንባላለን። ዜጎች “እራሳቸውን በራሳቸው የማፈናቀል መብት” የማስከበር ስላቅ!
እራስን በራስ በማስተዳደር ሽፋን ማስተዳደር የተሳናቸው አካላት በዜጎች ላይ ለሚደርሰው ግድያ እና መፈናቀል “የህዝብ ለህዝብ ግጭት” በሚል የዳቦ ስም ብዙሀኑን ህዝብ እያሞኙ ፍትህ አልባ ስልጣናቸውን ያጠነክራሉ።
ጓዶች፣ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ የሚደረግ ትግል አቋራጭ መንገድ የለውም!
Filed in: Amharic