>
5:14 pm - Sunday April 20, 3400

የግድያው ሙከራና አላማው! (ፋሲል የኔአለም)

የግድያው ሙከራና አላማው!
ፋሲል የኔአለም
 
* ከዚህ ሙከራ ጀርባ ኦነግ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ አክቲቪስቶችና ህወሃትም ሊኖሩበት እንደሚችል አስባለሁ!!!
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድን ለመግደል የተደረገውን ሙከራ አገሪቱ በኦነግ መመራት አለባት የሚል ግለሰቦች እንዳቀናበሩት አቃቢ ህግ ገልጿል።  የግድያው አቀናባሪም ገነት ታምሩ (ቶለሺ ታምሩ) የምትባል ናይሮቢ የምትኖር ሰው መሆኗን አቃቢ ህግ አክሎ አስታውቋል። ይህ መረጃ ትክክል እንደሆነ ባምንም አጠቃላዩን ምስል ያሳያል የሚል እምነት ግን የለኝም። ከዚህ ሙከራ ጀርባ ኦነግ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ አክቲቪስቶችና ህወሃትም ሊኖሩበት እንደሚችል አስባለሁ።
ህወሃት በመቀሌ ለኦነግ ያደረገው አቀባበል ለግድያ ሙከራው የቀረበ የምስጋና ዝግጅት አድርጌ እቆጥረዋለሁ። ህወሃት ኦነግን በአብይ መንግስት ላይ ለማስነሳት እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆዬ ነገር ነው።  በቡራዩና የተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች  የመንግስት ግልበጣው አንድ አካል እንደሆነ ከኦነግ የሁዋላ ታሪክ ተነስተን ብንናገር ‘አላዋቂ” አንባልም።
ከዚህ የግድያ ሙከራ ጀርባ ግን ኦነግ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ “አክቲቪስት” ነን የሚሉትም እጃቸው እንዳለበት መገመት አያዳግትም። በእነዚህ አክቲቪስቶችና በኦነግ መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ ጸብ ነበር። በቅርቡ እንኳን ” ቄሮ የማን ነው?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥረው ሲዘላለፉ እንደነበር እናስታውሳለን። የእነ ዳውድ ኢብሳ ቡድን ለአመታት በእነዚህ “ አክቲቪስቶች” በሚመራው ሚዲያ ቀርቦ አያውቅም ። መግለጫቸውን  ስለማያወጡላቸውም  ኢሳት ነበር የሚያስተናግድላቸው።  ታዲያ እንዲህ ለሞት ይፈላለጉ የነበሩት  ሃይሎች  እጅና ጓንት እንዲሆኑ ያደረጋቸው በአብይ መንግስት ላይ ያላቸው የጋራ ጥላቻ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። እነዚህ አክቲቪስቶች  አብይን “አጭበርባሪ፣ ደካማ፣ አድርባይ” እያሉ በመዝለፍ አብይ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ከፍተኛ ስራ ሲስሩ ቆይተዋል።  እንደነሱ ምኞትማ አብይ አይደለም ጠ/ሚኒስትር የወረዳ አስተዳዳሪ እንኳን እንዲሆን አይፈቅዱለትም ነበር። አብይ ከእነሱ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት ወደ ስልጣን ከመጣ በሁዋላ የተከተሉት አማራጭ ደግሞ አገርቤት ገብቶ ሴራ በመጎንጎን የአብይ ራዕይ እንዳይሳካ ማድረግ ነው።  ኦነግን አካተው 6 ድርጅቶች ያወጡት መግለጫ በኢሳትና በግንቦት7 ላይ ያነጣጠረ ቢመስልም፣ ዋና ኢላማው የአብይ መንግስት እንደሆነ ማንም አይስተውም።  ከዚያም አልፎ “ በአንድ አገር ሁለት መንግስት አለ” እያሉ የአብይን መንግስት ሲንኳስሱ እና ደካማ ተደርጎ እንዲቆጠር ከፍተኛ የቅስቀሳ ስራ ሲሰሩ እየታዘብናቸው ናቸው።
እንደሚታወቀው  የአነግ ዋና መቀመጫ ከአስመራ ቀጥሎ ናይሮቢ ነው።  አንዳንድ አክቲቪስቶች ደግሞ ናይሮቢ ሲመላለሱ እንደነበር ራሳቸው ተናግረዋል። እነዚህ ሰዎች ናይሮቢ የተቀመጠውን የኦነግ ክንፍ ለማነጋገር ካልሆነ በስተቀር ከኬንያ መንግስት ጋር ለመነጋገር ሊሄዱ አይችሉም ። ከኦነግ በተጨማሪ ህወሃትም በናይሮቢ ጠንካራ ህዋስ አለው። ሁለቱ ሃይሎች ናይሮቢ ላይ እየተገናኙ ሊመካከሩ የሚችሉበት እድል ከፍተኛ ነው።  ህወሃት በቀጥታ ከአብይ መንግስት ጋር ከመፋለም ለተለያዩ ጸረ-አብይ ድርጅቶችና ግለሰቦች የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ  በእጅ አዙር ለመፋለም መምረጡን እየታዘብን ነው።
የአብይ መንግስት ሁኔታውን በቅርብ እየተከታተለ  እንደሆነ እረዳለሁ። እነዚህን ሰዎች የሚፋለምበት ትክክለኛ ጊዜ እየመረጠ እንደሆነም አስባለሁ። ጠላትን የምትፋለምበትን ትክክለኛ ጊዜ መምረጥ ተገቢ ነው። ያ ትክክለኛ ጊዜ እስኪመጣ ግን የእነሱ ጊዜ ደርሶ የከፋ እርምጃ እንዳይወስዱ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። በመንግስት መስሪያቤቶችና በጸጥታ ተቋማት ውስጥ ያሉትን  የህወሃትና የኦነግን ህዋሶች መበጣጠስ ቀላል ስራ ባይሆንም በጥንቃቄ ከተሰራ ማጥራት ይቻላል።።
እነዚህ ሰዎች ከልክ በላይ የሚጮኹት ወንጀላቸውን ለመሸፈን መሆኑ ግልጽ ነው። ወንጀል እና እውነት ግን ተደብቆ አይቀርም። አብይ መስቀልን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት ላይ ይህንኑ እውነታ እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “ እውነት የቱንም ያህል ዘመን፣ በምንም ያህል ውሸትና ቅጥፈት- ተንኮልና ሤራ፣ በየትኛውም ስልጣን እና ክፋት ብትሸፈንም በዘላቂነት ልትቀበር እንደማትችል አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜ ፀሐይን እንደሚሸፍን ደመና እውነትን ለተወሰነ ጊዜ መከለል፣ ውሸትንም እውነት ማስመሰል ይቻል ይሆናል፡፡ በመጨረሻ ግን እውነት እንደምታሸንፍና ከተቀበረችበትም ወጥታ ቀባሪዎቿን እንደምታሳፍር ለማስረዳት የክርስቶስ መስቀል ታሪክ ግሩም ማስረገጫ ነው፡፡”
የአብይ ራዕይ ለኢትዮጵያ መድህን ነው።
Filed in: Amharic