>
5:13 pm - Sunday April 20, 7732

ሸገርን እንደ ኢየሩሳሌም!! ...  (ኤፍሬም እሸቴ - ቀሲስ)

ሸገርን እንደ ኢየሩሳሌም!!
በኤፍሬም እሸቴ (ቀሲስ)
ማንነትን የማያስከብር የማንነት ፖለቲካ!
የፖለቲካ ቁማሩን የሚጫወቱት ሰዎች ከሸገር ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ሳይሆኑ ቴክሳስና አረብ አገር ተቀምጠው በኢየሩሳሌም ጉዳይ ጦር እንደሚሰብቁት ሰዎች ያሉ ናቸው!!!
የዘመናዊት ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባይቱ ሸገር በተለያዩ ሕዝቦችና እምነቶች የይገባኛል ጥያቄ ተወጥራ የምትኖረውን ኢየሩሳሌምን ወደመሆን እየሄደች ይሆን?
ኢየሩሳሌም በይሁዲውም፤ በክርስቲያኑም፤ በሙስሊሙም ቅድስት አገር ሆና ለብዙ ሺህ ዓመታት የዘለቀች ምድር ናት። ቦታውም በዘላቂነት ለመያዝ ለሺህ ዓመታት ብዙ ጦርነቶች ተካሂደውባታል። በዚህም ሰበብ በብዙ መንግሥታትና እምነቶች ስትተዳደር ኖራለች። የዓለም ፖለቲካ ሙቀት መለኪያ ሆና እንደዘለቀችም ነው።
ስለ ኢየሩሳሌም አተኩሮ የተመለከተ ሰው በሙሉ የሚረዳው አንድ ሐቅ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና ባለ ይዞታዎች ሕይወትና ዕድል በመላው ዓለም የሚገኙ ነገር ግን ጉዳዩ በቀጥታ የማይመለከታቸው ብዙ አካላት ተጽዕኖ ሰለባ መሆኑን ነው። ቴክሳስ ገጠር ያለ አንድ ሰባኪ ምእመናኑን ኢየሩሳሌም የማን መሆን እንዳለባት ያስተምራል። የመንግሥት ተመራጩ የሱን ሐሳብ በሕዝብ ተወካዮችና በሴኔቱ እንዲያራምድለት ገንዘብ ይሰበስባል። በፈንታው ደግሞ በአረብ አገር ያለ ሌላ ሰው ተመሳሳይ ሥራ ለፍልስጥኤሞች ይሠራል። አንዱ አይሁድን ደግፎ ሌላው ደግሞ ፍልስጥኤምን ደግፎ ጦሩን ይሰብቃል። ውጤቱ አገር የሚያውቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው።
ተመሳሳይ ጨዋታ ወደ ሸገርም እየመጣ ነው። የፖለቲካ ቁማሩን የሚጫወቱት ሰዎች ከሸገር ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ሳይሆኑ ቴክሳስና የአረብ አገር ተቀምጠው በኢየሩሳሌም ጉዳይ ጦር እንደሚሰብቁት ሰዎች ያሉ ናቸው።
በአዲስ አበባ ባለቤትነት ላይ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱ ሰዎች የሸገርንና የትውልዷን ማንነት የማያውቁ ሰዎች ናቸው።
ሸገር አንድ ደረቅ ማንነት የላትም። በረዥም ዘመን ውስጥ ያለፈ በብዙ ማንነቶች ተደራርባ (በኮት ላይ ካፖርት ዓይነት) ያጌጠች አንዱን ብቻ ለይታ እንድትወስድ መገደድ የሌለባት ከተማ ናት። የሸገር ማንነት በጠቅላላው የኢትዮጵያ ማንነት እና ባለቤትነት ትእምርት (symbol) ነው።
ሸገር ማዕከላዊነቷ በመልክዐ ምድር (geography) ብቻ አይደለም። በታሪክም እምብርት ናት። ሸገር የዘማናዊት ኢትዮጵያ ምልክት ናት። የሸገር ፖለቲካን መረዳት የተለያዩ ማንነቶችን ተቀብሎ አዋሕዶ የሚሄደውን የሸዋን “ማዕከላዊ” ፖለቲካ መረዳት ነው።
እንግዲህ እውነቱን እንናገር ከተባለ ያለፉት 40 ዓመታት የኢትዮጵያ ችግር ይህንን ማዕከላዊነትን እና አካታችነትን የሚቀበለውን የሸዋና የሸገር ፖለቲካን የማያውቅና የማይረዳ የዳር አገር ፖለቲካ ሰለባ መሆናችን ነው። ይህ የዳር አገር ፖለቲካ (peripheral politics) ዳርነቱ በመልክዐ ምድር (geography) ብቻ ሳይሆን በሥነልቡናም (psyochology)  ጭምር መሆኑን እያስመሰከረ ነው።
አብዛኛው ዳር አገር እንደ ሸዋ እና እንደ ሸገር ውጥንቅጥና ድብልቅ (melting pot) አይደለም። ማንነት ሲባል አንድ ማንነት ካልሆነ ብሎ ድርቅ የሚለው ለዚህ ነው። በgeography ዳር አገር ሆነው ሳሉ በሥነልቡና psyochology ዳር ‘ያልነበሩትን’ እነ ሐረርን፣ ደሴን፣ ጅማን፣ ጎንደርን፣ ደብረ ማርቆስን፣ አምቦን ወይም አዳዲሶቹን ከተሞች እነ አዳማን፣ ሐዋሳን፣ ባህርዳርንና አርባ ምንጭን ወዘተ ከተመለከትን ከተሞቹን ልዩ ያደረጋቸው ብዙ ማንነቶችን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸው ነው። ልክ እንደ ሸገርና ሸዋ።
ሸዋ አንድ አይደለም። አንድ ማንነትም አይደለም። ድብልቅልቅ ነው። ነገር ግን እነዚህን የተለያዩ ማንነቶች ለመቀበል አይቸገርም። የዳር አገር ፖለቲካ የሚያራምዱ ሰዎች ይህንን የሸገር መንፈስ አያውቁም። አይቀበሉምም።
ሸገርነት በከተማው በመወለድና በማደግ ብቻ ሳይሆን ሥነልቡናውን በመቀበልም ይመጣል። የራሴን ታሪክ እንደ አብነት ልጥቀስ መሰል። እኔን ጨምሮ ሦስት እህቶቼ እና ሁለት ወንድሞቼ የተወለድነው ሸገር ነው። እትብቴ የተቀበረው ካዛንቺዝ ግንፍሌ ወንዝን ተገን አድርጎ ነው። 1ኛ ክፍል እስክገባ የመጀመሪያዎቹን ዓመታት ያሳለፍኩት በአዲስ አበባ ነው። 1ኛና 2ኛ ደረጃ ሆለታ ገነት ተምሬ ድጋሚ ወደ ሸገር መጣሁ።
ኮሌጅ የተማርኩትም፣ የሠራሁትም፣ አገሬን ጥዬ እስክወጣ የኖርኩትም ሸገር ነው። እኔ ብቻ ሳልሆን ከሰላሌ ባላባት ከጎጃሜ እናት የተወለደው አባቴ ያደገው፣ አግብቶ ልጆች ያፈራው፤ ክቡር ዘበኛ ሆኖ ኮሪያ ዘምቶ፣ ከጦሩ ከወጣም በኋላ ግብርና ሚኒስቴር አገልግሎ፣ ወደማይቀረው ዓለም ሲያልፍም መቃብሩ ያረፈው በሸገር ነው። የተወለደበት ሰላሌ ሳይሆን ኖሮ ያረፈባት ሸገር የበለጠ አካሉ ናት። እንደ አባቴ ሸገር በጉዲፈቻ ተቀብላ ልጅ ያደረገቻቸው አያሌ ናቸው።
ዛሬ ግን ነገር ተገልብጦ የሸገርን እናትነት የማያውቅ ደፋር ጠያቂ በር-በሯን አንቆ ቆሟል። #NotInMyName ልለው እወዳለሁ። እትብቴ በተቀበረታባት ከተማ ያለኝን ባለቤትነት ልትነጥቀኝ አትችልም ልለው እወዳለሁ። እስከዛሬም በግርምት ነገሮችን ሲመለከት የቆየው ብዙኃኑ የሸዋ ኦሮሞ “አሁንስ በዛ”፤ በእኔ ስም አትነግዱም የሚልበት ጊዜ እየቀረበ ይመስላል።
ከዳር አገር እየጎረፈ የመጣው ሰው እንዳደረገው ስላልተደራጀ ሐሳቡን ጠንከር ብሎ ማቅረብ አልቻለም እንጂ እስካሁንም የተለያዩ ድምጾች በየግል ሲሰሙ ቆይተዋል። በዚህ ግን አይቀጥልም። የጎበና ዳጬን፣ የገረሱ ዱኪን፣ የከበደ ብዙነሽን፣ የጃገማ ኬሎን መንፈስ የያዘው ከሰላሌ እስከ ዝዋይ፣ ከሙገር እስከ ጉደር ያለው ቀድሞም በሜጫና ቱለማ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥቅም የቆመው ሕዝብ ድምጹን ማሰማት ይችላል። በኦሮሞነቱ ሳያፍር ነገር ግን በኢትዮጵያዊነቱ ሳይደራደር በኩራት መኖር የሚችለው የሸዋ ሰው በሸገርም በኢትዮጵያም ከሌላው ወገኑ ጋር በፍቅር ለመኖር አይቸገርም።
ስለዚህ ሸገርን እንደ ኢየሩሳሌም የፕሮክሲ ዎር ማድረግ አይገባም። አይቻልምም። 
Filed in: Amharic