>
5:13 pm - Wednesday April 19, 1690

የጀብድ ሽሚያ መዘዝ!!! (መስከረም አበራ)

የጀብድ ሽሚያ መዘዝ!!!
መስከረም አበራ
ፖለቲካ እንደ ጉንዳን መንገድ ቀጥተኛ አይደለም፡፡ብዙ ውስብስብ ነገሮች በውስጡ አሉ፡፡አንድ ፖለቲካዊ ሁነት በስሎ እስኪጎመራ የሚመግበው ተዋናይ ብዙ ነው፡፡ በአንድ ሃገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ክስተቶች ምክንያታቸው በሰፊው ለሁለት ይከፈላል- መሰረታዊ(Basic) እና የወዲያው(Immediate) ምክንያት በሚል፡፡መሰረታዊ ምክንያት የሚባለው ፖለቲካዊ ሁነቱ እንዲከሰት ሁነቱ ከመከሰቱ በፊት ራቅ ካለ ታሪካዊ  ጊዜ ጀምሮ ሲሰራ የነበረ ምክንያት ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ አንደኛው የዓለም ጦርነትን  እ.ኤ.አ 1914 ላይ እንዲፈነዳ በ19ኛው ምዕተ አመት አካባቢ ጀምሮ በእንግሊዝ የታየው የኢንዱስትሪ አብዮት ጦር መሳሪያዎችን በገፍ ማምረትን ስላስቻለ፣ ይህ ደግሞ የጦረኝነት ውድድር(Arm’s race) በመፍጠሩ ለአንደኛው የዓለም ጦርነት መከሰት መሰረታዊ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ በተመሳሳይ በ15ኛው ምዕተ ዓመት አካባቢ የታየው የአብርሆት(Enlightenment)እንቅስቃሴ ዲሞክራሲ፣ሊብራሊዝም፣ሃገር ግንባታ የሚሉ ፅንሰ-ሃሳቦችን በማስተዋወቁ ለአውቶማን ቱርክ ኢምፓየር መፈራረስ እና ከፍርስራሹ በርካታ ሃገሮች ዲሞክራሲን አንግበው እንዲገነቡ መሰረታዊ ምክንያት ሆኗል፡፡
ነገሩን በዕለት ተዕለት ኑሯችን ብናመጣው ውሃ ጥደን ለማፍላት ስናስብ ውሃውን የማፍላቱን ወሮታ የሚወስደው ውሃው ሊፍለቀለቅ ሲል ያስገባነው ሁለት እንጨት ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡የመጨረሻው እንጨት ውሃውን እንዲያፈላው መጀመሪያ ውሃው መሞቅ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ውሃው ከተጣደ ጀምሮ ሙቀት ማግኘት አለበትና ብዙ እንጨቶች መቃጠል አለባቸው፡፡ከተጣደ ጀምሮ የገቡት እንጨቶች በመጨረሻ ለማፍላት ከገቡት እንጨቶች ይበልጥ ለውሃው መፍላት አስተፅኦ አበርክተዋል፡፡ በሌላ ምሳሌ የተነፋ ፊኛን በእስፒል በስቶ ለማፈንዳት በመጀመሪያ ፊኛው አብጦ ለማፈንዳት እንዲመች ትንፋሽ ወደፊኛው እየላኩ እንዲወጠር የማድረግ ትልቅ ስራ ያስፈልጋል፡፡ የተነፋ ፊኛን ለማፈንዳት በስፒል መውጋቱም አስፈላጊ ድርጊት ቢሆንም ብቸኛ እና ቀድሞ ተሰራውን ስራ ገደል የሚከት መሆን የለበትም፡፡
ፖለቲካም እንዲህ ነው፡፡ፖለቲካዊ ለውጥን የሚያመጣው ብዙሃኑ በጉልህ የሚያየውም፣የማያየውም፣ ሁነቱ የተከሰተበት አካባቢ አባል የሆነም ያልሆነም አካል መዋጮ በማድረጉ ነው፡፡በአፍሪካ የቅኝ አገዛዝ ስርዓት እንዲያበቃ አፍሪካዊያን ያደረጉት ትግል እንዳለ ሆኖ የአሜሪካ እና የሶቬት ህብረት ልዕለ ሃያል ሆኖ በአለም ፖለቲካ ብቅ ማለት እና ከቅኝ አገዛዝ ተግባር በተቃራኒ መቆም እጅግ ወሳኝ ነገር ነበር፡፡እነዚህ ልዕለ ሃያላን ሃገራት ግን ከቅኝ ገዥዎችም ተገዥዎችም ወገን አልነበሩም፡፡ በራሳቸው መንገድ ለራሳቸው ጥቅም ሲሰሩ ቅኝ አገዛዝ እንዲያበቃ መስራት ስለነበረባቸው የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካ የነበራቸው ህልውና እንዲመናመን እና እንዲጠፋ አበርከቶ አድርገዋል፡፡
የሃገራችን ፖለቲካም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡በሃገራችን ጥንቅቅ ብሎ የተደረገ ለውጥ የለም/ አልነበረም ለማለት ያስደፍራል፡፡ሃገራችን ለውጥ የሚያመክን ወይ የሚያጨነግፍ ሾተላይ የተጣባት አሳዛኝ ሃገር ነች፡፡የቀደሙትን አሳዛኝ የለውጥ ጭንገፋ ታሪካዊ ክስተቶችን ለጊዜው ወደጎን ትተን አሁን ያለንበትን ፖለቲካዊ ከባቢ ብናስተውል የለማ ቡድን የሚባለውን አካል ወደ ስልጣን ያመጣው ፖለቲካዊ ግፊት ጥንቅቅ ያለ ለውጥን ያመጣ አብዮት ሳይሆን ኢህአዴግን ያደሰ ተሃድሶ ነው ቢባል ይመረጣል፡፡ተሃድሶው ብዙ ልብ ያሳረፉ በጎ እርምጃዎችን የወሰደ፣መሪዎቹም እስከዛሬ ካየናቸው መሪዎች በተሻለ ፖለቲካውን አንድ እርምጃ ለማራመድ ላይ ታች የሚሉ ቅንነት የማያጡ  መሆናቸው ግልፅ ሃቅ ነው፡፡
ለሃገራችን ፖለቲካዊ ፈውስ እስካመጣ ድረስ የቤት ስራውን ጠንቅቆ ያልጨረሰው ተሃድሶም ቢሆን ይሁን የሚባል እንጅ የሚጠላ አይደለም፤እንደውም የሚመረጥ ሊሆን ይችላል፡፡ የለማ ቡድንን ወደስልጣን ያመጣው ተሃድሶ ከአብዮት የሚመረጠው ከዚህ ቀደም ስልጣን ላይ የቆየው ህወሃት የሚባል መሰሪ ቡድን ሃገሪቱ በቀላሉ ልትፈራርስ የምትችልበትን ሁሉ ሲያደርግ በመኖሩ ነው፡፡ አብዮት ይምጣ ከተባለ ኢህአዴግ የሚባል አካል ከአስተዳደሩ ዞር ሊል ነው፡፡በዚህ የጊዜ ክፍተት ደግሞ እድሜ ለህወሃት የጎሳ ፖለቲካ ሃገር ማጣትም ሊመጣ ይችል ነበር፡፡ስለዚህ ይህ ክፍተት ሳይፈጠር የዶ/ር አብይ ቡድን ወደስልጣን መጥቶ የቻለውን በጎ ነገር ሁሉ በቅንነት፣ከታሰበው በላይ እያደረገ ነው፡፡
ትልቁ ስራ እነዶ/ር አብይ/አቶ ለማ መገርሳ እና ቡድናቸው እያደረጉት ያለው ሃገር የማዳን ስራ ሆኖ ሳለ እዚህ ግባ የማይባል ግን ደግሞ ይህን በጎ ተግባር ለማደናቀፍ እሰራ ያለ “እነ አብይን ወደ ስልጣን ያመጣው የማን ጉብዝና፣የየትኛው ዘር በለጥ ያለ መስዕዋትነት ነው?” የሚል የጀብድ ሽሚያ ፈተና ሆኖ መጥቷል፡፡ይህ የጀብድ ሽሚያ ችግር የሚሆነው ያስከተለው አላማ ሲመረመር ነው፡፡ እነ አብይን ወደስልጣን ያመጣሁት በእኔ የበለጠ ጀግንነት ነው የሚለው ቡድን ይህን ጉዳይ የሚያነሳው ጎበዝ ተብሎ ተጨብጭቦለት እንዲያልፍ ብቻ አይደለም፡፡ይልቅስ በጀግንነቴ መጠን፣ በጀብዴ ብልጫ ሳቢያ የእኔ ዘር ይበልጥ ይከበር፣ያልታገለውን ዘር ይገዛ፣ያስፈራራ ዘንድ፣የጠያቀው ሁሉ ወዲያው ከመናገሩ ይደረግለት ዘንድ  የተገባ ነው ለማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሄዶ ሄዶ ማቆሚያው የህወሃትን የበላይነት በሌላ የበላይነት መተካት፣እየዞሩ እዛው መቀመቅ ውስጥ መገኘትን እንጅ ማደግን አያመጣም -ምናልባት መተላለቅን ያመጣ ይሆናል እንጅ፡፡ ህወሃትን ያየው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአሁን በኋላ በአንድ ወገን ዘዋሪነት ባሪያሆኖ መገዛትን አይፈቅድም፡፡
የቄሮ አለቃነኝ ከሚለው አቶ ጃዋር ጀምሮ እነ ኦቦ በቀለ ገርባን ይዞ እስከ እነ ዶ/ር ፀጋየ አራርሳ ድረስ የሚደርሰው፤ቄሮ ካልፈቀደ በኢትዮጵያ ሰማይ ፀሃይ ወጥታ አትጠልቅም ከሚል አይነት ንግግር እስከ የእኛ ሰው ወደስልጣን ቢመጣም ለኦሮሞ የሆነለት ነገር የለም እስከሚለው የአቶ በቀለ ገርባ የዘወትር ንግግር የሚያስረዳው የልብለጥ ባይነትን ምኞት ነው፡፡ይህን ልብለጥ ባይነት ያመጣው ደግሞ ወያኔን የጣለው ሶስት አመት የተጓዘው የቄሮ ትግል ስለሆነ ሳይታገል ተቀምጦ የቄሮን የጀግንነት ቱርፋት እያጣጣመ ባለ ዜጋ ላይ ሁሉ የቄሮ መንፈስ ይግነን የሚል ምኞት ነው፡፡
ይህ አስራ ሰባት አመት ስዋጋ ስልሳ ሽህ ሰማዕታት ዘሮቼን በመሰዋቴ ዝንተ አለም እንደ ከብት ልንዳችሁ ሲል የነበረው የህወሃት አስተምሮ ኦሮሟዊ ትርጉም ነው፡፡ በዚህ አይነት በእኩልነት ልንኖር የምንችለው ሰማኒያ አምስት ጊዜ አብዮት እያደረግን ሰማኒያ አምስቱም ዘር ጉብዝናውን፣የበላይነቱን ካሳየ በኋላ ነው ማለት ነው፡፡እንዲህ ከሆነ ደግሞ ቄሮም ሆነ ህወሃት የተዋጋው ቋንጃችንን ቆርጦ እያንፏቀቀ ሊገዛን እንጅ የወያኔ ታጋዮችም ሆኑ ጃዋር እንደሚያወራው ከደርግ አምባገነናዊ ስርዓትም ሆነ ከወያኔ እስር ሊያስፈታን አይደለም፡፡
እውነት እውነቱን ስንነጋገር ወያኔም ከአስራ ሰባት አመቱ ውስጥ አስራ አራቱን ዓመት የተዋጋው ትግራይን ሊገነጥል እንጅ ኢትዮጵያዊን ነፃ ሊያወጣ አልነበረም፡፡ትግራይን ከመገንጠል ይልቅ ኢትዮጵያን እየዘረፈ ኢፈርት የሚባል ኢምፓየርን በትግራይ መገንባቱ አዋጭ እንደሆነ በተረዳበት ቀሪ ሶስት አመት ያደረገው ትግልም ለሌላው ኢትዮጵያዊ ነፃነት መሞት ሆኖ የሚቆጠርበት ነገር የለም፤እስከመጨረሻው ተያይተናል!ይህንኑ የህወሃት መንገድ ሊደግም እየሞከረው ያለው ጃዋር የቄሮ ገድል ተረክም ቢሆን የትግሉ አላማ ራስን ማዕከል ያደረገ እንጅ ጃዋር እንደሚያወራው የኢትዮጵያ ህዝብን ነፃ የማውጣትን አላማ ያነገበ አልነበረም፡፡
ለዚህ ማመሳከሪያው ስልጣን ላይ የወጡት ዶ/ር አብይ ኦሮሞ ባይሆኑ ኖሮ በአብይ ወንበር ላይ መለኮት ቢቀመጥ እንኳን ቄሮም ሆኑ ጃዋር ወያኔን ጥያለሁ ብለው አሁን እንዳደረጉት ቤታቸው ገብተው እንደማይቀመጡ ግልፅ ነገር ነው፡፡ዶ/ር አብይ ኦሮሞ ሆነው ሳለ ለኢትዮጵያዊ ሁሉ ተስፋ መሆኖቸውን ተከትሎ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ ሲብጠለጠሉ እንደሚውሉ በኦሮምኛው ቀርቶ በአማርኛው የሚተላለፉ የ”OMN” ፕሮግራሞችን ማድመጥ በቂ ነው፡፡ሰው አንድ ነገር በተናገረ ቁጥር አፍ እየተከተለ ቄሮ ባይኖር ኖሮ ይህን ማለት ባልቻልክ፣ስለሁሉ ቄሮን አመስግን የሚለው ጃዋር የረሳው አንድ ነገር ቄሮ ትግል በሚያደርግበት ዘመን ሁሉ ከኦሮሞ አጀንዳ ውጭ ሌላ ነገር ሲል ሰምተን የማናውቅ መሆኑ ነው፡፡
ለምልክት አንድ የኢትዮጵያ ባንዲራ አይተንበት የማናውቀው የቄሮ እንቅስቃሴ እንዴት ብሎ ለእኛ ነፃነት ሲታገል እንደነበረ እንደልቡ የሚናገረው ጃዋር ብቻ ያውቃል፡፡ጠለቅ ብለን እንነጋገር ከተባለ ደግሞ ቄሮ በኦሮሚያ በሚያደርገው ትግል ወቅት ከኦሮሞ ብሄር ውጭ የሆኑ  ኢትዮጵያዊያን የአረመኔውን የህወሃትን እንድሜ ሳይቀር በሚያስለምን ትልቅ የህልውና ስጋት ውስጥ እንደነበሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ጃዋር ራሱ ሚኒሶታ ላይ ሆኖ “በሃረር ለምናደርገው የቄሮ ትግል እንቅፋት የሚሆኑብን በሃረር የሚኖሩ የጉራጌ እና የስልጤ ተወላጆች ናቸው” እያለ የፃፈው ሃላፊነት የጎደለው የተጋደሉ ጥሪ በፌስቡክ ገፁ የገባ ሁሉ የሚያገኘው ነው፡፡
የተሃድሶ ለውጡን ማን አመጣው?
ከላይ በመግቢያየ ለመጥቀስ እንደከርኩት ለውጥ መሰረታዊ እና የወዲያው ምክንያቶች አሉት፡፡ ከሁለቱ ምክንያቶች ለለውጥ መምጣት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት መሰረታዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ሃገራችንም ከዚህ ነባራዊ ሃቅ ውጭ ልትሆን አትችልም፡፡አሁን የመጣውን የተሃድሶ ለውጥ እውን ያደረጉት መሰረታዊ ምክንያቶች ምናልባትም ወያኔ ስልጣን አያያዙን አልችል ብሎ መወለጋገድ ከጀመረበት ከ1983 ማግስት፤ጭራሽ ከዛም ቀደም ብሎ ስልጣን ላይ ሳይወጣ ጀምሮ  በተፈጠሩ ሁነቶች ሊሆን ይችላል፡፡ህወሃት ስልጣን ላይ ሊወጣ ዳር ዳር ሲል አፈንግጠው ወጥተው ጉዱን የዘረዘሩለት አይተ ገብረመድህን አርአያ ለዛሬው የህወሃት መውደቅ ሩቅ ቆሞ የሰራው ስራ አለ፡፡እሳቸውን ያዩት እነ አይተ አስገደ ገ/ስላሴ የህወሃት የሙስና ዝንባሌ አይተው ስልጣን በተያዘ ማግስት ከህወሃት መውጣታቸው እና የግልፕሬሱን ተጠቅመው ይህን ማጋለጣቸው ለወያኔ መውደቅ አበርክቶት አለው፡፡
የወያኔ ማንነት ታውቆ በሰፊው ህዝብ ዘንድ ወድቀህ ተነሳ የሚለው ባይጠፋ ኖሮ ስር ሰዶ የኖረው ወያኔ እንዲህ እንደንፋስ ብን ብሎ ባልጠፋ፡፡ለአንድ ስርዓት መንኮታኮት ዋናው ምክንያት በህዝብ ዘንድ ያለውን አመኔታ፣ተቀባነት፣ተወዳጅነት ማጣቱ ነው፡፡ይህን ለማድረግ ሚዲያዎች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ወያኔ ሊወድቅ ዘመም ዘመም ያለው ኢፈርት የሚባል የሌብነት ኢምፓየር ገንብቶ እንደሚዘርፍ በግሉ ሚዲያ የወጣ ቀን፣ የዝርፊያው መረብ በመፅሃፍ ተጠርዞ ለህዝብ እነሆ የተባለ ቀን ነው፡፡
የ1997ቱን ከምርጫ ጋር የተያያዘ መንግስታዊ ቅሌት በማጋለጡ ብዙ ጋዜጠኛ፣ፖለቲከኛ ዋጋ ከፍሏል፡፡ወያኔን መጣሉ ባይሳካላቸውም፣የራሳቸው የቤታቤት ችግር ባይጠፋቸውም በተቃውሞው ፖለቲካ የተሰለፉ ወገኖቻችንም አሁን ኢትዮጵያ እያጣጣመችው ላለው ለውጥ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡እነዚህ ሰዎች የሚታገሉት አርባ ክንድ ርቀው ተቀምጠው ሳይሆን እዚሁ አምባገነኑ ህወሃት ይገዛው በነበረው ምድር ተቀምጠው፣ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው፣ልጆቻቸውን እያሳቀቁ፣ቤተሰባቸውን በትነው፣እስርቤት ገብተው ሞባይል ነጥቆ በታሰረ ወሮበላ ሳይቀር እየተደበደቡ፣ከሰውነት ጎዳና ወጥተው፣ክብራቸው ተዋርዶ ነው፡፡ይህን ሁሉ ዋጋ ከፍለው እንዲህ አድርገው ያላነቁት፣ያላሳወቁት ህዝብ አምባገነኖችን በቃችሁ ሊል አይችልም፡፡ጋዜጠኛ እየታሰረ፣እየተደበደበ፣እየተሰደደ ያነቃውን ህዝብ ባህርማዶ ሆኖ ኪፓድ የመጫን “መስዕዋትነት” ከፍሎ አደባባይ እንዲወጣ ማድረግ የሚናቅ አስተዋፅኦ ባይሆንም “ከእኔ በላይ ላሳር” የሚያስብል፣በአምባገገን አፈሙዝ ስር፣ከእስርቤቱ አምባ ሲማቅቅ የኖረን፣ልጅቀብሮ የገባን ህዝብ “እድሜ ለእኔ እና ለዘሬ በሉ” ለማለት የሚያደርስ ግን አይደለም!
በአሁኑ ሰዓት የመጣው ለውጥ በኢህአዴግ ውስጥ የህወሃትን የበላይነት ማስወገድ ነው፤ከዛ በላይ የመጣ ተዓምር የለም፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ሆኖ የህወሃትን የበላይነት እምቢኝ ማለት እጅግ አደገኛ ውሳኔ ነው፡፡ለውጥ አመጣሁ ብሎ መመፃደቅ ካስፈለገ ከማንም በላይ መመፃደቅ ያለባቸው ይህን ያደረጉት የለማ ቡድን አባላት ናቸው፡፡እነዚህ ሰዎች ህወሃት ባልባረከው ሁኔታ የመለስ ዜናዊ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ሲሞክሩ ቢለዋ ላይ እየቆሙ ነበር፡፡ይህን አደገኛ ነገር ያሰቡ ሰዎች ትልቁን አደጋ የተሞላበት ጉዞ የጀመሩት ሃሳቡን ለሌላ ጓዳቸው አካፍለው ቡድን መመስረት ሲጀምሩ ነበር፡፡ ይሄን ማድረጉ ደግሞ ብዙዎቻንም እንደምናስበው የአንድ ቀን ጉዳይ አይደለም፡፡ይልቅስ የዘመናት መገፋት፣መንቋሸሽ፣መዋረድ ያመጣው፤ዶንቦስኮ ገብቶ በሞንጆሪኖ ምላስ ከመለብለብ ህመም ጋር የተጋመደ  ነገር ነው፡፡በዚህ አንፃር የህወሃት ቅጥ ያጣ እበልጣለሁ ባይነት ለራሱ ውድቀት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡ ስለዚህ ወያኔን በመጣሉ በኩል ራሱ ወያኔ አስተዋፅኦ ነበረው ማለት ነው፡፡
የለማ ቡድን የሚባለው ደፋር ስብስብ ለዚህ ለመብቃቱ እየታሰረ እየተፈታ፣ እልም ስልም እያለ የኖረው የግሉ ፕሬስ አስተዋፅኦ አያጣም፡፡በተለይ ዶ/ር አብይ ድሮ ቀርቶ ዛሬ ስልጣን ላይ ወጥተው እንኳን የግሉን ፕሬስ እንደሚከታተሉ ያስታውቃል፡፡ህወሃቶች አድራጊ ፈጣሪ ሆነው የዛሬዎቹን መሪዎች ሲኮረኩሙ በነበረበት ዘመን አብይ እና ለማ(ምናልባትም ሌሎችም) የመለስ ዜናዊን እውቀት ችላ ብለው ሌሎች መፅሃፍትን እና  የግሉን ፕሬስ ያነቡ እንደነበር ከኢህአዴግ ካድሬ የማይጠበቅ ማስተዋላቸው እና ህይወት ያለው ንግግራቸው ምስክር ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከሚያነቡ ጫካ ተመልሰው ቢገቡ የሚሻላቸው ህወሃቶች ያልተጠቀሙበት የስምንት ወሩ የአመራርነት ስልጠና መማር የሚወዱትን አብይን እና ለማን ሳይጠቅም አልቀረም፡፡ አስጎንብሶ መግዛት የሚወደው ህወሃት የአገልጋይ አመራርነት ዘይቤን የሚያስተምረውን የስምንት ወር (የማስተርስ ፕሮሮግራም) የአመራርነት ስልጠና ለምን እንደፈለገው ባይገባኝም የተማመነው የካድሬዎቹን ንባብ ጠልነት መሰለኝ፡፡ካድሬዎቹ መዝረፍ እንጅ ማንበብ እንደማያሻቸው በደምብ የሚያውቁት መለስ ዜናዊ ይህን ሲያደርጉ ብዙ ባይሳሳቱም ከሰው መሃል አንድ ሁለቱ ከግምታቸው ውጭ ሆኖ የተማረውን እውነት አድርጎ ህዝብን የማገልገል መልካም እድል ሊመርጥ እንደሚችል መገመት ነበረባቸው፡፡ይህ ሳይሆን ቀርቶ አብይ እና ለማ በዝተው ተባዝተው ቡድን መስርተው የሚያደርጉትን አደረጉ፡፡ ስለዚህ ወያኔ ገንዘቡን አፍስሶ ያመጣው የአመራርነት ስልጠናም ኢትዮጵያውስጥ ለመጣው ለውጥ ሚና አያጣም ማለት ነው፡፡
እነ አቶ ለማ እምቢ ለማለታቸው ደግሞ ከእነሱ በፊት ከህወሃት ግዙነት አፈንግጠው ባገኙት ቀዳዳ ሾልከው የወጡ ጓዶቻቸው ውሳኔ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የነለማን ልዩ የሚያደርገው በህይወታቸው እስከ መጨከን በደረሰ ድፍረት ሃገራቸውን ቀርቶ ፓርቲያቸውን ኢህአዴግንም ከህወሃት መንጋጋ ለመንጠቅ መጋደላቸው ነው፡፡ በዚህ ሰዓት የአውሬው  መንጋጋ ቢያገኛቸው የሚደርስባቸው መከራ አንድ ቀን ተዘግቶ ዋለን የፌስ ቡክ አካውንትን እንደ ማስከፈት የቀለለ አይደለም፡፡በፌስ ቡክ መታገል እና በጨካኙ ህወሃት ሜዳ፣ በመሃለኛው ክብ ውስጥ ተገኝቶ መታገል ልዩነቱ ይህ ነው! በወቅቱ እዚህ ሰዎች እውነት ህወሃትን እየታገሉ ነው ብሎ ለመቀበል በግሌ ያዳግተኝ የነበረው እና አጥብቄ እሟገት የነበረው ከሚጠይቀው መስዕዋትነት ምሬት አንፃር ነው፡፡ዛሬ እውነቱ ሲገጥ እያደር የሚያስገርመኝም ይሄው ነው፡፡ ይበልጥ የሚገርመው ብቻ ሳይሆን ከሳቅ ጋር የሚያታግለው  ደግሞ እነለማ ቁጭ ብለው በሚሰሙበት መድረክ የፌስቡክ ታጋዮች እኔ ልባስ ማለት ነው፡፡
ወደፌስ ቡኩ ትግል ቱርፋት ስንመጣ ወያኔን ለመጣል አደባባይ የወጣው ቄሮ ብቻ እንዳልሆነ ግልፅ ነገር ነው፡፡የከፋው ሁሉ ባገኘው አጋጣሚ አምባገነን አገዛዝን ከላዩ ላይ ለማንከባለል ጮኋል፡፡በባዶ እጅ ሶስት አመት ከመታገሉ እኩል የጎንደሩ ጠመንጃ ያከለ ትግል ብረት አጥብቆ የሚፈራውን ወያኔን እንዳላራደ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡በኮንሶ የተነሳው እንቅስቃሴ ወልቂጤን ማስከተሉ ወያኔ በአራቱም ማዕዘን የማይፈለግ፣እድሜው አጭር መንግስት እንደሆነ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ፍንጭ በመስጠቱ ወዳጅ የተባሉት ሃገራትም ሳይቀሩ ለውድቀቱ እንዳልሰሩ እንዴት ታወቀ?ቄሮ ብቻውን ወያኔን መጣል ከቻለ ጃዋር በትግሉ ወቅት ባገኘው ቀዳዳ ሁሉ “ኦሮሞ ሲሞት ሌላው ለምን ዝም ይላል? ለምን አንተባበርም?” እያለ ሲወተውት የነበረው ለምንድን ነበር?
የጃዋር ሚና ምንድን ነው?
የፖለቲካ ተንታኝ የሚባል ማዕረግ ተንጠልጥሎለት የኖረው ወንድም ጃዋር በቅርቡ “እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም? ምን ይደረግ ብላችሁ የአቅጣጫ ጥያቄ አትጠይቁኝ?” ሲል ሰማሁት፡፡ጃዋር የሚለው ብዙ እና የማይፀና ነው፡፡ይህንኑ ባለበት አፉ ደግሞ ለታማኝ ግብዣ መልስ ሲሰጥ “እኔ ኮ ሁሉን ጨርሼ ወደ አስተዳደራዊ ጉዳይ ገብቻለሁ” አለ፡፡ ስለ ዶ/ር አብይ የመደመር ፍልስፍና እፁብነት ሲወራ “የመደመር ካልኩሌተሩን የሰራሁት እኔ ነኝ” የሚል ነገር ተናገረ፡፡ “ኦሮሚያን ለመገንጠል ብንፈልግ እኮ እኔ እና ቄሮ በአንድ ሳምንት ውስጥ እናደርገው ነበር አሁንም ማድረግ እንችላለን ስላልፈለግን ነው እንጅ፤ይህን መሪዎች ራሳቸውም ያውቃሉኮ ህዝቡ ይቃዠል እንዴ?” የሚለው ጃዋር በአንድ ሳምንት ሃገር መገንጠል ይቻላል ወይ የሚለውን ለማገናዘብ ሳይቸገር ነው፡፡ይህን የሚለው ጃዋር “ህገ-መንግስቱን መቀየር ቀርቶ ስለመቀየር የሚያወራ እንዳልሰማ” ይላል፡፡ይህው ዘብ የሚቆምለት ህገ-መንግስት ግን ክልል መገንጠልን በአንድ ሳምንት የሚደረግ ቀላል ነገር አድርጎ አላስቀመጠውም፡፡ይህን ሁሉ የሚለው ጃዋር በስተመጨረሻው “አክቲቪስት ነኝ” ሲል ራሱን ይገልፃል፡፡
ከባለቤት ያወቀ የለምና አክቲቪስትነቱን እንያዝለትና ጥያቄዎች እናንሳ፡፡አክቲቪስት በመንግስታዊ አስተዳደር ውስጥ ገብቶ የሚሰራው በየትኛው የህግ አግባብ ነው? ሁሉን ጨርሼ አስተዳደራዊ ስራውን እያሳለጥኩ ነው የሚለው ጃዋር በየትኛው ሚኒስትር መስሪያቤት ወይም ሌላ የመንግስት ክንፍ ውስጥ ገብቶ ነው እየሰራ ያለው?አስተዳደራዊ ስራውስጥ ገብቻለሁ ካለ አሁን በሚታየው የአስተዳደር ቀውስ ውስጥ የእሱ ሚና ሆነ አስተዋፅኦ ምን እንደሆነ ማወቅ እንሻለንና የስልጣን ቦታው ይነገረን፡፡በአንድ ሳምንት ውስጥ ኦሮሚያን ገንጥሎ መጨረስ ያስቻለው ጉልበቱስ ከየት የመጣ ነው?ህግ ባለበት ሃገር ህግ ከሚለው በተለየ በደቂቃውስጥ እንዲህ ማድረግ የምችል ሰው ነኝ ማለት የህግ የበላይነትን የሚፈታተን ነገር አይደለም? ይህን መሪዎችም ያውቃሉ ሲባል መሪዎች የሚያውቁት የጃዋር ሁሉን የማድረግ ጉልበት ምንጩ ምንድን ነው? መከረኛ ቄሮ? ከሆነ ቄሮ እና ጃዋር ከህግ በላይ ናቸው ማለት ነው?ከሆነ ቄሮም ጃዋርም ያልሆነው ኢትዮጵያዊ ተስፋው ምንድን ነው?
አንደበታችሁን ቅጡልን!
ፖለቲካ በአጠቃላይ የጎሳ ፖለቲካ በተለይ እጅግ ከባድ በሆነ ጥንቃቄ ሊያዝ የሚገባው ነገር ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሁኔታ በሃገራችን ፖለቲካ ከተሰለፉ ሃይሎች ውስጥ የሚናገሩት ነገር የሚያመጣውን ነገር ቆም ብለው ሳያስቡ ስሜታቸው እንዳቀበላቸው፣ሃላፊነት በጎደለው መንገድ እንደፈለጉ የሚናገሩት ደግሞ የጎሳ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች መሆናቸው በጣም አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካውን የሚመሩ ሰዎች ቀደም ሲል የተናገሩት ነገር መጥፎ ተፅዕኖ እነሱ ተቀየርን ብለው ሌላ የፖለቲካ መስመር በያዙበት ቅፅበት የማይቀየር መሆኑ ነው ችግሩ፡፡ ለምሳሌ ኦቦ ሌንጮ ለታ ኦሮሚያን እገነጥላለሁ በሚሉበት ዘመን ይናገሩት፣ ይሰሩት የነበረው ነገር ተፅዕኖው ዛሬ እሳቸው እድሜም ተሞክሮም አለሳልሷቸው መስመር ቀይረው በኢትዮጵያ ጥላስር እታገላለሁ የሚል ነገር ባነሱበት ወቅት የሚቀየር አይደለም፡፡ ዛሬ ባህር ማዶ ተቀምጠው እጅግ አደገኛ የሆነ የጎሳ ፖለቲካ የሚያራምዱ ሰዎች እየተመገቡ ያደጉት የኦቦ ሌንጮ ለታን ፓርቲ  አስተምሮ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ዛሬ ኦቦ ሌንጮ ለታ ራሳቸው ሄደው ተው ቢሏቸው እንኳን የሚመለሱ አይመስለኝም፡፡
አቶ ጃዋር መሃመድ ሩቅ ሳይኬድ የዛሬ ሁለት ሶስት አመት የተናገረውን ነገር መልሰው ቢያሰሙት ለራሱም ሳያስደነግጠው አይቀርም፡፡ ከሰሞኑ LTV ከቀድሞው ንግግሮቹ አንዱን (Let Ethiopia be out of Oromiya የሚለውን) መልሶ ሲያስደምጠው በፍንዳታነቱ የተናገረው እንደሆነ ቀለል አድርጎ ተናግሯል፡፡ ይህ ግን ከጥፋት አያድንም! ምክንያቱም ይህን ነገር እውነት ነው ብሎ ሲከተል የኖረው ብዙ ነው፡፡ ምናልባትም እሱ በጉርምስና ነው የተናገርኩት እስከሚልባት ቅፅበት ድረስ ነገሩን እውነት አድርጎ የሚሰራ ተከታይ አይጠፋም፡፡ይህን ፕሮግራም የመስማት እድል አግኝቶ ጃዋር በጉርምስና እንደተናገረው የሚረዳውስ ስንት የጃዋር ተከታይ ነው?
በቅርቡ በኢትዮጵያ የቄሮ እና የአብይ የሚባል ሁለት መንግስት ነው ያለው ሲል አፉን ሞልቶ የተናገረው ነገር እጅግ ወጣት ለሆኑ ተከታዮቹ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው? የአዋቂ መጨረሻ አድርገው የሚያስቡት መሪያቸው ጃዋር ከአብይ መንግስት ጋር የሚስተካከል መንግስትነት እንዳላቸው ከነገራቸው “ጓደኛቸው” የአብይ መንግስት ያወጣውን ህግ እንዴት ብለው ያከብራሉ? ሁለት “እኩል ጉልበት” ያላቸው መንግስታት እንዴት በአንዱ መንግስት ህግ እና ስርዓት ውስጥ ያድራሉ? በዚህ ላይ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር  ቄሮ ያልፈቀደው ነገር አይሰራም አይነት ንግግር በየደረሱበት ማውራት ለልጆቹ የሚሰጠው ትርጉም ምንድን ነው? ይህን የሰሙ ወጣት ልጆች የሚያደርጉትን ቢያደርጉ ፍርዱ በማን ነው?
ጃዋር እራሱ በየደረሰበት የሚያወራው ነገር እንዳለ ሆኖ በሚመራው የተባለ ቴሌቭዥን ጣቢያ የተለያዩ ሰዎች እየተገኙ የጥላቻ ስብከትን ሲሰብኩ የጃዋር ቴሌቭዥን ጣቢያ የሚያደርገው ብቸኛ ነገር የሰዎቹ ንግግር የቴሌቭዥን ጣቢያውን እንደማይወክል ብቻነው፡፡ይህን ማለት የተጀመረውም ገና ትናንት ነው፡፡በዚህ የቴሌቭዥን ጣቢያ በኦሮምኛ የሚነገረው በአማርኛ ከሚነገረው እንደሚብስ ሰምቻለሁ፡፡ የተሻለ የተባለው የአማርኛው ንግግር ራሱ በጣም ብዙ አስደንጋጭ ንግግሮችን ያጨቀ ነው፡፡
የኦነግ አመራሮችን ለመቀበል አንድ ቀን ሲቀር በዚሁ ጣቢያ በአማርኛው ዝግጅት  ቀርበው የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ አፋቸውን ሞልተው “ኦሮምኛ የሚናገሩ ልጆች አዲስ አበባ እንዳይገቡ ተከልክለዋል፣የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ዝግጅቱ በሰላም እንዳይከናወን እየሰሩ ነው” የሚል ክስ ሲያቀርቡ ነበር የዋሉት፡፡ኦሮምኛ የሚናገር ሰው አዲስ አበባ አይገባም ከተባለ አራት ሚሊዮኑ የመስቀል አደባባይ/ስቴዲዮም ታዳሚ የምን ቋንቋ ተናጋሪ ነበር? የህግ አካላትስ ምን ፍለጋ ነው ዝግጅቱ በሰላም እንዳይከናወን የሚሰሩት? ስለታማ፣ተቀጣጣይ እና ሌላ መሳሪያ ተይዞ ሰልፍ እንዳይገባ መፈተሽ ለፕሮግራሙ መቃናት መስራት ነው ፕሮግራሙን ማስተጓጎል?ቀን ኦሮምኛ የሚናገር አዲስ አበባ አይገባም ተባለ የሚለውን የትልቅ ሰው ንግግር የሰማ ጎረምሳ ማታ ሰው ቢገድል፣ለፖሊስ አልታዘዝም ቢል በእሱ ይፈረዳል? የአቀባበሉ ዕለት ማታ ያሁሉ ደም መፍሰሱን ለማውገዝ የተፃፈውን የተፎካካሪ ፓርቲዎች የአቋም መግለጫ ለማንበብ የተገኙትም ራሳቸው ኦቦ በቀለ ገርባ መሆናቸው ግር ያሰኛል፡፡
Filed in: Amharic