>

ከእውነት ጋር መጋጨት! (ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ)

ከእውነት ጋር መጋጨት!
ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ
ወጣቱ በመረጃ ከተደገፈበት እውነታ እያራቀ፣ በጊዜ እያሸሸ፣ ከአመክንዮ ወርዶ ከሀቅ ጋር እየተጣላ በነቀዘ አስተሳሰብ፣ በተመረዘ ጭንቅላት፣ በደነዘዘ አእምሮ፣ በመሳይ ውሸትና በመከነ ርዕዮተ አለም እውር ድንብሩን እየሄደ ወደየት እንደሚያመራ አያውቀውም!!
እኔ ስለ ጎሳ ፖለቲካና ስለዜግነት ፖለቲካ እያነፀርኩ ስፅፍ የማይመቸው የማህበራዊ ሚድያ ወዳጅ አለኝ። እየተናደደ ኮሜነት ያደርጋል። በውስጥ መስመስመር ብቅ ብሎ ዘብዝቦ ተነጫንጮ ይሄዳል። ከህሊናው ጋር እየተጋጨ ሰላሙ ስለሚጠፋ ነው።
የስነልቦና ሊቃውንት cognitive dissonance ይሉታል። ማንኛውም ሰው በተለይ ደግሞ የሚጣላ ሕሊና ያለው ፍጡር ሁሉ ተቀብሎ የሚያምንበት ነገር በማስረጃ ሊታይ ከሚችለው እውነታ ሲለይበት ጭንቀት ውስጥ ይገባል። ሰው ሰላም የሚኖረው በጭንቅላቱ ውስጥ ያለው እና በማስረጃ የተደገፈው እውነታ ሲጣጣሙ ነው። ያለዚያ ሆዳም ያልሆነ ያዳም ልጅ ሰላም የለውም።
የሰው ልጅ ከሰው ጋር የሚወያየው፣ የሚጨቃጨቀው፣ ከራሱ ጋር የሚሟገተው፣ ሀሳብ ይዞ የሚቆዝመው [contemplate የሚያደርገው] እዛ ሚዛን ላይ ለመድረስ ነው። ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች ተረጋግተው በሸመቱት እውቀት እየተመሩ በመሳይ ውሸትና በእውነት መካከል ያለውን ልዩነት አንጥሮ በማውጣት ሰላማቸውን ይመለሳል።
አንዳንድ ጊዜ ግን ሰዎች የሚያምኑበት ነገር ለሕይወታቸው ወሳኝ እንደሆነ አድርገው ከወሰዱትና እውነታው የተለየ ሆኖ ከተገኘ የሚያሳዩት ባህሪ ሁል ጊዜ አመክንዮ አልባ ሊሆን ይችላል። እውነታውን ለመካድ ከእውነታው በተቃራኒ ይሄዳሉ ወይም እውነታውን ለማጥፋት ይነሳሉ። ደርግ፣ ወያኔ፣ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ መኢሶን ወዘተ ሁሉ ይህንን አድርገውታል።
 በዘረኛና የጥላቻ ብሄረተኛ አስተሳሰብ የተሞሉ ግለሰቦችና ቡድኖች በአብዛኛው ወደ ንዴትና የኃይል እርምጃ የሚሄዱት ለዚህ ነው። እውነት የሌላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የሀሳብ ውይይትና ክርክር አይወዱም። ምክንያቱም የሀሳብ ውይይትና ክርክር ከሚወዱትና ከሚያምኑት መሳይ ውሸት ሊነጥላቸው ይችላልና። ይህ በሳይንሳዊ ጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
የማንነት ፖለቲካን እንደሙያ የያዙ ግለሰቦችና ቡድኖችም ዋና ዓላማቸው ይህንን የሰዎችን ድክመት በመበዝበዝ ኃይልና ስልጣን ማግኘት ነው። በሰዎች ድክመት ማትረፍ ኢሞራል የሆነ ነገር ነው። ይሄ ደግሞ የማንኛውም ወንጀለኛ በህሪ ነው። እነዚህ ግለሰቦች የሚጣላ ሕሊና ስለሌላቸው በሰዎች ድክመት አትርፈውና ወንጀል ሰርተው እንቅልፍ ተኝተው ያድራሉ። እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ከሌላው ጤነኛ ሰው የሚለዩበት አንዱ መገለጫቸው ይሄ ነው።
የሚጣላ ሕሊና ያለው ጤነኛ ሰው ነገሮች ትክክል ካልሆኑ ሰላም አያገኝም፤ እንቅልፍ የለውም። የሚጣላ ሕሊና የሌላቸው በሰዎች ድክመት አትርፈው ኢሞራላዊ ተግባርን ስራቸው የሚያደርጉ የወንጀለኛ ባህሪ የተጠናወታቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ግን ነገሮች ትክክል ያልሆኑበት ቦታ ሰላም አላቸው ብቻ ሳይሆን የአቅማቸው ማነስ ከሚገታቸው በስተቀር በኢሞራላዊ ተግባሮች ለማትረፍ የሞራልና የስልጣኔ ልጓም የላቸውም። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ጸረ-ማኅበረሰብ ወይም psychopath ተብለው ይታወቃሉ።
ጤነኛ ለሆነው ሰው ግን ያ በአዕምሮ ውስጥ ያለና እውነታ መለያየት ምክናታዊ ሆነው በጥሞና ማቀራረብ ካልቻሉ ወደ ግለሰብም ሆነ ማኅበራዊ ጭንቀትና እብደት ሊያመራ ይችላል። ያኔ እነዛ መታከም የማይችሉት በሽተኞች ተቀብለው የፈለጋቸውን ያስደርጓቸዋል።
ለጽሁፌ መነሻ የሆነው ያወዳጄ እንደ አብዛኛው ሕዝብ ጤነኛ ነው። ማለቴ ይህ ወዳጄ ወንጀለኛ ሆኖ አልተፈጠረም። እሱ ያላየው ነገር ግን እነዛ ወንጀለኛ ሆነው የተፈጠሩት ሊያሳብዱት እንደሆነ ለመገንዘብ ጭንቅላቱ ድፍን መሆኑ ላይ ነው። በመረጃ ከተደገፈበት እውነታ እያራቀ፣ በጊዜ እያሸሸ፣ ከአመክንዮ ወርዶ ከሀቅ ጋር እየተጣላ በነቀዘ አስተሳሰብ፣ በተመረዘ ጭንቅላት፣ በደነዘዘ አእምሮ፣ በመሳይ ውሸትና በመከነ ርዕዮተ አለም እውር ድንብሩን እየሄደ ወደየት እንደሚያመራ አላየውም።
እኔ ደጋግሜ የምፅፈው እነዚህ ወገኖቼን ከህሊናቸው ጋር እያጋጨሁ፣ ሰላማቸውን እየነሳሁ፣ ወደ ትክክለኛው አስተሳሰብ መምራት ነው!
Filed in: Amharic