>

የያዝከው ራዕይ ከመንደር ካላለፈ፣ ታሪክህም ከመንደር አያልፍም!!! (ፋሲል የኔአለም)

የያዝከው ራዕይ ከመንደር ካላለፈ፣ ታሪክህም ከመንደር አያልፍም!!!
ፋሲል የኔአለም
 
ለባህርዳርና አካባቢው ወጣቶች
የአርበኞች ግንቦት7 አባላት ወደ ባህርዳር እንዳይገቡ እንዲከለከሉ፣ ከገቡም ተቃውሞ እንዲደረግባቸው የሚተላለፉትን መልዕክቶች አይቼ በእጅጉ ተገረምኩ። የአማራን ወጣት እንዴት ቢንቁት ነው እንዲህ አይነት ትዕዛዝ የሚያስተላልፉት? የአማራ መታወቂያ የሆነው ሁሉንም ወገን አዳምጦ የራሱን ፍርድ የመስጠት ባህል ከመቼው ተረሳ? የባህርዳር ልጆች ይህን አያደርጉትም፤ የመራዊ ልጆች ይህን አያደርጉትም፣ የአዴት ልጆች ይህን አያደርጉትም፣ የዘጌ ልጆች ይህን አያደርጉትም፣ የዱርቤቴ ልጆች ይህን አያደርጉትም። አውቃቸዋለሁ። አይደለም አርበኞች ግንቦት7 ኦነግ ወደ ክልሉ ሄዶ  አላማውን እንዲያስረዳ ቢጠይቅ  “ እንኳን ደህና መጣህ” ብለው የሚቀበሉ፣ ሁሉንም ሰምተው፣ በግላቸው አመዛዝነው የሚፍርዱ ሰዎች የሞሉበት አካባቢ ነው።
የአማራ ህዝብ ሰፊ ራዕይ ያለው ህዝብ ነው፤ ታሪኩም ስፋቱን እንጅ ጥበቱን አያሳይም። ቴዎድሮስን ከቋራ ጫካ ያወጣው እስከ እየሩሳሌም የተዘረጋው  ራዕዩ ነበር። ጀግና ያስባለውም የራዕዩ ስፋት ነው እንጅ ተኳሽነቱ ወይም ፊታውራሪነቱ ብቻ አልነበረም።  ከቴዎድሮስ የማይንስ ጀግንነት የነበራቸው ብዙ ሰዎች፣ በራዕያቸው ጥበት ብቻ መንደራቸው ውስጥ ቀልጠው ቀርተዋል። የያዝከው ራዕይ ከመንደር ካላለፈ፣ ታሪክህም ከመንደር አያልፍም። የወጣቱን ራዕይ ሊያጠቡ የሚፈልጉ ሰዎች፣ ራዕያቸው የጠበባቸው ናቸውና ወጣቱ  ራዕያችሁን መርምሩ ሊላቸው ይገባል። ዱርቤቴ ላይ ቁጭ ብለህ፣ ስለዱርቤቴ ብቻ እያሰብክ ብትብሰከሰክ ራዕይህ ከዱርቤቴ አያልፍም።  ኢትዮጵያን እወቅ፣ አፍሪካን እወቅ፣ አለምን እወቅ። ራዕይህንም በዚሁ ልክ አስፋ። እንዲህ ስታደርግ ለዱርቤቴ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ሰው መኩሪያ ትሆናለህ። የባህርዳር ህዝብ አይደለም ከራሱ አብራክ የወጡትን ልጆች ይቅርና የአለምን ቱሪስቶች ተቀብሎ በፍቅር አስተናግዶ የሚመልስ ውብ ህዝብ ነው። ራዕዩም እንደጣና  ሰፊ ነው።
በአርበኞች ግንባት7 ላይ ቅሬታ ያላችሁ ወጣቶች፣ ወደ ክልላችሁ የመጡትን መሪዎች ጨዋነት በተሞላበት መልኩ በጥያቄ አፋጡዋቸው። ስህተት ካገኛችሁባቸው ደግሞ ፊት ለፊት ገስጿቸው። ከዚያ ውጭ ያለውን ምክር አዕምሮን የሚደፍን፣ ጠባብነት ስለሆነ አትቀበሉት። በፍጹም እናንተን አይመጥንም። የአበረ ይማም ልጆች፣ የመንገሻ ጀምብሬ ልጆች የበላይ ዘለቀ ልጆች አባቶቻችሁ ለነጻነት የከፈሉትን መስዋትነት አስታውሱ። ብአዴን ይሁን አብን ወይም አዴሃን ከ አርበኞች ግንቦት7 ጋር ይህን ያክል የከረረና ደም የሚያቃባ ልዩነት ያላቸው አይመስለኝም። በኢትዮጵያ አንድነት፣ በሰንደቃላማ እና በብዙ ጥያቄዎች ዙሪያ  አቋማችሁ ተመሳሳይ ነው። ልዩነት ቢኖር ከአደረጃጀት ጋር የተያያዘ  ነው። ይህንንም ቢሆን ሁሉም ድርጅቶች ቁጭ ብለው ተነጋግረው መፍትሄ ሊፈልጉለት ይችላሉ። ተነጋግሮ የጋራ የትግል ስትራቴጂ በማውጣት፣ ሃይልን ማጠንከር ነው እንጅ፣ በረባው ባልረባው ሃይልን ማዳከምና  ህዝብን መጉዳት ተገቢ አይደለም። በደንብ ይታሰብበት። በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ የእናንተ ወንድሞችና እህቶች ናቸው። ሙላለም ከደሳለኝ፣ ደነቀው ከንጉሱ ቁጭ ብለው ሲነጋገሩ ማዬት እንሻለን።
በክልሉ አሉ የምንላቸውን ጀግናው አባታችንን አቶ ሽባባው የኔአባትን የሚያወግዝ ጽሁፍ ተመልክቻለሁ።  በዚህ ድርጊት እጅግ አዝኛለሁ። አቶ ሽባባው  በእንክብካቤ መያዝ ያለባቸው ኩሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው።  የአቶ ሽባባውን ጀግንነትና ድፍረት ያየሁት እስር ቤት እያለሁ ነበር፤ የቅንጅት መሪዎችን እየተመላለሱ  ከጠየቁት ጥቂት ባለሃብቶች ውስጥ አቶ ሽባባው ተጠቃሽ ናቸው። ስልጣኔ የገባቸው፣ ለክልሉ እድገት ብዙ የጣሩትን ሰው  እድሜያቸውን እንዲያረዝምልን መጸለይ ሲገባ፣ የውግዘት ቃል ሲድረስባቸው መስማት ያማል። የባህርዳር ልጆች እንዲህ እንደማታድርጉ ባውቅም፣ በመካከላችሁ እንዲህ የሚያደረጉት ካሉ ተው በሏቸው።
በመጨረሻም ያ ሁሉ የጎጠኞች ሴራ ከሽፎ
ባህርዳር ዶ/ር ብርሀኑን እና  አብሮት የተጓዘውን ልዑክ በክብር ተቀብላ እያስተናገደችው ነው። የአማራ ህዝብ መንገድ ላደከመው እንግዳ አልጋውን የሚለቅ ፤ ያለውን አካፍሎ በፍቅር ተንከባክቦ የሚሸኝ ትሁት ህዝብ ነው። ዛሬም የሆነው ይሄ ነው እስከዘመን መጨረሻ ጠብቆ የሚያቆየው ልማዱ ነው ።
እንደ ቅንጅት ወራሽነቱ አግ7 የዜግነትና የአንድነት ፓለቲካ ርዕዮትን በመላው ኢትዮጵያ ይሰብካል። ከሰሜን ዛላ አንበሳ እስከ ደቡብ ጫፍ ሞያሌ ፤ ከደጋሀቡር እስከ ጋምቤላ ኢትዮጵያውያን በነጻነት ተንቀሳቅሰው ይኖሩ እና ሙሉ የባለቤትነት ስሜት ይሰማቸው ዘንድ የዜግነት ፓለቲካ ወሳኝ ሚና አለው። የብሄር ማንነቱን ሳይተው የኢትዮጵያን አንድነትን በጽኑ ለሚመኘው ይህ ትውልድ አግ7 መሰባሰቢያው ነው። 
 
እናመሰግናለን ባህርዳር !  
Filed in: Amharic