>

ለካ የግፍ አገዛዝ ገበና ሸፋኝ ነው!  (ያሬድ ሀይለማርያም)

ለካ የግፍ አገዛዝ ገበና ሸፋኝ ነው! 
ያሬድ ሀይለማርያም
የፍ አገዛዝ በተንሰራፋበት ሥፍራ ሁሉ አለቃው አንድ እና አንድ ሰው ወይም አብድ ቡድን ብቻ ነው። ያሻውን ያስራልም፣ ይገላል፣ ያፍናል፣ ይቆርጣል፣ ይፈልጣል። በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ሁሉም አልቃሽ፣ ብሶተኛ፣ የግፍ ሰለባ እና ተሰዳጅ ነው። በደርግም ሆነ በወያኔ ዘመን አንድ ጉልበተኛ ብቻ ስለነበር አገሪቱን የተቆጣጠረው ሁሉም ጸጥ ለጥ ብሎ ነበር የግፍ እንቆቆውን ይጋት የነበረው።
ነጻነት ሁሉንም እኩል ያደርጋል። መንግስትንም ከገዳይ እና ገፈኛ ነው አውርዶ የሕዝብ አገልጋይ ያደርጋል። ነጻነት ቀለም የለውም፣ ነጻነት ኃይማኖት የለውም፣ ነጻነት ብሔር ወይም ጎሳ የለውም፣ ነጻነት ባንዲራ ወይም መለያ የለውም። ነጻነት በሰፈነበት አገር ሁሉም ሰው እኩል ዋጋ አለው። ሁሉም ባህሎች፣ ኃይማኖቶች፣ ጎሳዎች ወይም ሌሎች መለያዎች ሁሉ እኩል ነጻ ናቸው። በነጻነት ምድር አንድ ነገር ብቻ ነው ኃያል ወይም የበላይ፤ እሱም የሕግ ልዕልና ነው።
የአንድ ሕዝብ ሕግ አክባሪነቱ፣ ሥርዓት አዋቂነቱም ሆነ ስልጡንነቱ የሚፈተነው በነጻነት ዘመን ነው። እያንዳንዱ ሰው ነጻነት ሲሰማው የሚያደርገው ነገር እና ነጻ ባልሆነበት ሥፍራ የሚያደርገው ነገር ፍጹም የተለየ ነው።
በአፈና ውስጥ ያለን ሕዝብ ባሕሪ ለማጥናትም ሆነ ለማወቅ እጅግ ከባድ ነው። ባህሪውን ላጥናም ብትል ሁለት ነገር ነው የምታገኘው አንዱ ሁሉም የጥቃት ሰለባ ስለሆነ በተበዳይነት ስነልቦና ሁሉም በጋራ ሊቆም ይችላል፣ አንድ አይነት ብሶትም ይነግርሃል። ሁለተናው በፍርሃት ውስጥ ስለሚኖር አብዛናው ሰው የልቡን ሳይሆን ገራፊዎቹ እና አሳሪዎቹ መስማት የሚፈልጉትን ነው የሚነግርህ። ወይም ለዘመናት ጸጥ እረጭ ብሎ ስለሚቆይ ምንም እንደሚያስብ አታውቅም።
ባህሪ መገለጫው ያሳቡትን ሲናገሩ ወይም በተግባር ሲከውኑት ብቻ ነው። ለዛ ደግሞ ነጻ እና መብት ፈቃጅ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት መኖር አለበት።  ይህን ገበናⶭንን ደርግ እና ወያኔ ጋርደውልን ኖረዋል። ዛሬ ያ መጋረጃ ተቀዳዶ ገበናችን አደባባይ ላይ ወጥቷል።
ለፍቅር፣ ለመቻቻል፣ ለውይይት፣ ለመደማመጥ እና በእውቀት ላይ ለተመሰረጠ የለውጥ ጉዞ ወይስ ለጸብ፣ ለአንባጓሮ፣ እርስ በርስ ለመጠላለፍ ነው ቅርብ የሆነው?
እውነተኛ ማንነታችን የሚታየው አሁን ነው። ለዛም ነው የአዲስ አመታ ዋዜማ ላይ ባስተላለፍኩት የምኞት መልዕክቴን “እንኳን ለፈተና ዘመን አደረሰን!!!” ያልኩ።
ከዚህ ጽሑፍ ጋር ያያዘኳቸው ሁለት ምስሎች ያለፍነውን እና የምንመኘውን ሥርዓቶች ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ። ከነ ልዩነቶቻችን አንድ ኢትዮጵያ በምትባል እሥር ቤት ውስጥ አብረን ሁሉንም መከራዎች አሳልፈናል። ዛሬ ከነ ልዩነቶቻችን ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ ነጻነትን ማጣጣም ጀምረናል። እርስ በእርስ እና ከመንግስትም ጋር ተከባብሮ መኖር እና መሥራት ያለውንም ትርፍ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ታዝበናል። አሁንም የሚጥመንን እንምረጥ፤ ታፍኖ – ተከባብሮ መኖር ወይስ ነጻ ሆኖ – ተከባብሮ መኖር ወይስ ነጻ ሆኖ- መገዳደል።
Filed in: Amharic