>
5:13 pm - Friday April 20, 6440

ኢትዮጵያዬ  ሆይ!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ኢ ት ዮ ጵ ያ ዬ  ሆ ይ !!!
አሰፋ ሀይሉ
* ኢትዮጵያውያን ሁሉ – እነርሱ ስለከፈሉልን የማይተካ ክቡር ዋጋ – በምጥ በተያዝን ጊዜ –  ስላሣዩን ወደር የሌለው የወገን ፍቅር – በታላቅ ክብር፣ በታላቅ ፍቅር፣ እና በታላቅ የባለውለታነት ስሜት – ታላቅ ውለታቸውን እያነሣን – ደግመን ደጋግመን ልንዘክራቸው ይገባል!!
ይሄ በቀይ ደማቅ ቀለም አሸብርቆ የምናየው ሜዳሊያ – ያኔ – በጭንቅና ረሃብ – በእርስ-በእርስ ንክሻና ውጥረት የተነሣ – በድካም አሸልባ የነበረችውን ምስኪኗን እናት ሀገራችንን – ቀን ጠብቆ – ቁጥር-ሥፍር ባልነበረው ኃይሉ እየጠረማመሰ ሀገራችንን የወረረውን – የዚአድ ባሬን የሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት – ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጎ ለማስወጣት – በ1969/70 በተደረገው ታላቅ ሀገራዊ-ሕዝባዊ ትንቅንቅ – እናት ሀገራቸውን ኢትዮጵያን – ከጡንቸኛ ወራሪዎች እጅ ለመታደግ ቆርጠው – በጀግንነት ለተሠለፉ – እና በተሠለፉበትም ጎራ – የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው – ኢትዮጵያውያውያን ቁስለኛ ወታደሮች፣ ፖሊሶች፣ የሕዝባዊ ሚሊሺያ አባላትና ወዶ-ዘማች ኢትዮጵያውያን – የተሠጠ የክብር ሜዳሊያ ነው፡፡
ይህ መሐሉ ላይ – እነዚያ ስለሀገራቸውና ህዝባቸው ሲሉ የቆሰሉትን የደም ጠብታ በተምሣሌትነት የሚያወሳ – ያ የማይረሣ ታላቅ ሀገራዊ ወገናዊ ፍቅራቸው በደማቅ ቀይ ቀለም የተቀረፀበት – «በግዳጅ ላይ የቆሰለ» የሚል – ታላቅ የጦርሜዳ የክብር ኒሻን – በ1971 ዓ.ም.፣ በአዋጅ ቁጥር 157 አማካይነት ብሔራዊ ህጋዊ ዕውቅና አግኝቶ – ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ከባዕዳን ወራሪዎች ለመታደግ ሲሉ – እነዚያ ወገኖቻችን ለከፈሉት የማይተካ ውለታ – ሀገራቸውና ሕዝባቸው በክብር ውለታቸውን ሲያስታውስ እንደሚኖር ባረጋገጠ ብሔራዊ አቋም መሠረት – ከወራሪው ኃይል ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ለቆሰሉ የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች – እንዲሁም ደግሞ – እኛን ሊራዱ ምድራችንን ረግጠው – ለተመሣሣይ ሀገራዊ ዓላማ – አብረውን ለቆሰሉ፣ አብረውን ደማቸውን ላንጠበጠቡ (እንደ ኩባውያን ላሉ) የወዳጅ ሀገራት ዜጎች ሁሉ – የተበረከተላቸው ብሔራዊ የክብር ኒሻን ነው – ይህ ባለ ቀይ ልብ ሜዳሊያ፡፡
እናት ኢትዮጵያችን – በተለያዩ ዘመናት – ምድሯን ጎምጅተው – ህዝቦቿን ለባርነት ተመኝተው – እግራቸውን በአፈሯ ያሣረፉባትን የውጭ ወራሪዎች ሁሉ – እያሣፈረች የመለሰች – ታላቅ የጀግኖች ሀገር እንደሆነች – ዓለም ሁሉ የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ እምዬ ኢትዮጵያ ግን – በየዘመኑ የተቃጡባትን ፈርጣማ ወራሪዎች ተቋቁማ – ሉዐላዊነቷን አስጠብቃ – ሕዝቦቿን በባዕዳን እጅ በባርነት ከመጣፍ አስከፊ ዕጣ ፈንታ ተከላክላ – ለዘመናት ኖራለች ስንል – እየተናገርን ያለነው – ስለማን ነው?? ስለእነዚያ በየዘመኑ በጀግንነት ሀገሬን ብለው ተነስተው ጠላትን ድባቅ ስለመቱት ኢትዮጵያውያን ነው የምንናገረው፡፡ ስለነዚህ – ህይወታቸውን ለታላቅ መሥዋዕትነት አሣልፈው የሰጡ ሰዎች ነው፡፡ ስለሀገራችን የዘመናት የነፃነት ተጋድሎ ስናወሳ – የምናወሳው – ከሚኖሩበት ሕዝብና ሠላማዊ ኑሮ መሐል – በጀግንነት መሰስ ብለው ወጥተው – ለአንዲቱ ሀገራቸውና – ላበቀላቸው ላሳደጋቸው ሕዝባቸው ሲሉ – ውድ አካላቸውን አስረክበው – ባዶ እጃቸውን ስለተመለሱት – ስለእነዚህ የወገን ፍቅር መገለጫዎች – ስለእነዚህ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ታላቅ አኩሪ ተግባር ነው በክብር የምናወሳው፡፡
ስለ ሌላ ምክንያት አይደለም – አሁን ያገኘናትን ሀገር ያገኘናት፡፡ ስለ እነዚያ – ስለ እነርሱ ፍቅር ነው፡፡ ስለ እነርሱ መስዋዕትነት ነው፡፡ ስለ እነርሱ ውድ ጀግንነት ነው፡፡ ስለ እነርሱ እና እነርሱን መሰል ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ታላቅ ተጋድሎና መሥዋዕትነት ነው – ይህች ሀገር የኖረችን፡፡ በእነርሱ ታላቅ selfless ተግባር ነው – ሀገር ያለን ሰዎች የሆንነው፡፡ እንጂ – ምናልባት – እነዚያ ጀግኖች አባቶቻችን ደረታቸውን ለወራሪ ሰጥተው ባይታደጉን ኖሮ – ምናልባት አሁን – አገር አልባ ሆነው ካገር ሀገር እንደሚንከራተቱት – እንደ ጂብሲዎች ሆነን እንቀር ነበር፡፡ ወይ የህዝበ አይሁድ ዕጣ ፈንታ አይቀርልንም ነበር፡፡ ኩርዶችን የማንሆንበት ምክንያትም አልነበረም፡፡ እነዚህ ጀግኖች ውድ ኢትዮጵያውያን ግን – ሀገራቸው እና ህዝባቸው እነርሱን በሻተበት ጊዜ ሁሉ ያለማቅማማት እየተሠለፉ – ህዝባቸውን እና ሀገራቸውን ከወራሪዎች ጠብቀው አቆይተውልናል፡፡ እነርሱ ደማቸውን አዝርተው ነው – ደም የማይዘራባትን ሀገር ትተውልን ያለፉት፡፡ እነርሱ ህይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተው ነው – ህይወት የሚቀጥልባትን ሀገር ልናገኝ የበቃነው፡፡ መራመዳችን – መኖራችን – መገኘታችን  – ከአንድዬ አምላካችን ቀጥሎ – በእነዚህ – በእነርሱ – በጀግኖቹ ወደር የሌለው ፍቅርና ሥጦታ የተነሣ ነው፡፡
እና ለእነዚህ – ከራሳቸው የግል ህይወት አልፈው – ስለቀጣዩ ትውልድና ስለሀገር ብለው – ለህዝባቸው ቤዛ የሆኑ – የየዘመኑ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን የወገን አርበኞች – በሙሉ ልብ ወጥተው – ከነሙሉ ልባቸው የተመለሱ – ነገር ግን – ሙሉ አካል ይዘው ወጥተው – ነፍሳቸው ብትተርፍም – የጎደለ አካል ይዘው ለተመለሱ፡፡ ጤነኛ ሰውነት ይዘው ወጥተው – አንድዬ በቸርነቱ ነፍሳቸውን ቢታደጋትም – የቆሰለ አካልን አትርፈው ለተመለሱልን – ለእነዚህ ታላቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመን-አይሽሬ ጀግኖች ባለውለታዎች – እና እነዚህን ለመሰሉ በየዘመኑ ለተነሱ እና ለወደቁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ – ዘለዓለማዊ ክብርና ፍቅር ይገባቸዋልና –  ውለታቸውን እናስብ፡፡ በየወጡበት በረሃ፣ በየተሰለፉበት የጦር ጎራ – የሚኖሩበትን የሚያኖሩትን ቤተሰባቸውን አጉድለው – እነርሱ ግን – ሀገር ብለው እንደወጡ ለቀሩ – በምንም ዋጋ የማትተመነውን ውዲቱን አካላቸውን – ለዚህች ምድርና ሕዝብ – ለእኛ – ለትውልዶቻቸው ሲሉ አጉድለው – ማንም የማይከፍለውን እጅግ ከባድ ዋጋ ከፍለው ለተመለሱ – እና ላልተመለሱምና አፈር በልቷቸው ለቀሩትም – አኩሪ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ወገኖቻችን – እኛ አሁን ላይ ያለን እያንዳንዳችን – አሁን እነሱ ባተረፉልን ምድር-ሠማይ ላይ ደረታችንን ነፍተን የምንመላለሰው ሁላችን ኢትዮጵያውያን ሁሉ – እነርሱ ስለከፈሉልን የማይተካ ክቡር ዋጋ – በምጥ በተያዝን ጊዜ –  ስላሣዩን ወደር የሌለው የወገን ፍቅር – በታላቅ ክብር፣ በታላቅ ፍቅር፣ እና በታላቅ የባለውለታነት ስሜት – ታላቅ ውለታቸውን እያነሣን – ደግመን ደጋግመን ልንዘክራቸው – ደግመን ደጋግመን በመጪ ትውልዶቻችን ውስጥ – ለእኛ ወገኖቻቸው የሠጡንን ታላቅ ፍቅርና  – የከፈሉልንን ታላቅ የወገን ዋጋ – በየልባችን ውስጥ – በታላቅ የአደራ ማተም አትመን ልናኖርላቸው – የሞራል ግዴታ አለብን፡፡ የመንፈስ አደራ ወድቆብናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ – ሁላችንን – ግድ ይለናል፡፡
አንድዬ ያለልን ቀን ደግሞ መምጣቱ አይቀርም ይመስለኛል፡፡ እኛም – አንድዬ ያለ ቀን – እኛም በሥልጣኔ እንደጓኑት ሀገራት ህዝቦች እንደሚደረገው ሁሉ – እኛም ደግሞ በሀገር ደረጃ – በማናቸውም ጎራ ወገንን ብለው ተሠልፈው – ላበቀለቻቸው ሀገራቸው፣ ላሳደጋቸው ህዝባቸው፣ እና ለታላቅ ህዝባዊ ሀገራዊ ዓላማቸው ሲሉ – ውድ አካላቸውን አሳልፈው ለሰጡ – እልፍ አዕላፍ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን – እና ቤተሰቦቻቸው – ከትውልድ ትውልድ የሚታወሱበት – ሀገራዊ መታሰቢያ የሚሆናቸው፣ – እነርሱ ያጎደሏቸውን ወገኖችና ቤተሰቦች መርጃ የሚሆን፣ – ስለሀገራቸው ብለው ለደረሰባቸው ስብራት ካሣ የሚሆን፣ – ስለጉድለታቸው አለኝታ የሚሆናቸው፣ – ሥራቸውን ታሪካቸውን የሚያጠና፣ የሚዘክር – አንድ ብሔራዊ ሀገር-አቀፍ የኢትዮጵያውያን ወገኖች የጦር ሜዳ ቁስለኞች መታሰቢያ ብሔራዊ ተቋም – በሀገር ደረጃ የምንመሠርትበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን  – ታላቅ ተስፋ አለኝ፡፡
መመሥረቱ ብቻም አይደለም፡፡ ይህ ተቋም ደግሞ ተመሥርቶ – መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ – በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመከባበር፣ በጀግንነት፣ በአንድነት፣ እና በሀዘንም ሆነ በደስታ – እጅ ለእጅ አያይዞ – ሁላችንንም አሁን ያለነውን የኢትዮጵያ ልጆች – እና ወደፊትም የሚወለዱትን ልጆቻችንን ሁሉ – በአንድ ታላቅ ሀገራዊ ወገናዊ ፍቅር የሚያስተሳስርበት ጊዜ – ሩቅ እንደማይሆን – ታላቅን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እናደርጋለን፡፡
አምላክ – እምዬ ኢትዮጵያን ያሉ – የእምዬ ኢትዮጵያን ልጆች – የልጅ ልጆች – የልጅ ልጅ ልጅ …. ልጆች – ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መልካሙን ተመኝተው – የቻሉትን ዋጋ – የማይቻላን ከባድ ውድ ዋጋ – የከፈሉና የሚከፍሉትን መላውን ኢትዮጵያውያን ትውልዶች ሁሉ – በአንድ ታላቅ ሀገራዊ የፍቅር በትር የልባቸውን – የልባችንን – ታላቅ ወገናዊ ፍቅር ያፍልቅልን፡፡  የመተሳሰብን መንፈስ – በመካከላችን ይዝራብን፡፡ የወደፊት ተስፋችንን የምናድስ – በአንድ ታላቅ – ሠፊ – ቻይ – ታጋሽ – ሀገራዊ ልብ – በአንድ ታላቅ የመዋደድ ሀገራዊ መንፈስ የምንመራ – ታለቅ ህዝቦች እንሆን ዘንድ አምላካችን ይርዳን፡፡
አንድዬ የኢትዮጵያ አምላክ – በእኛ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ – በትውልዶቻችን ሁሉ ልብ ውስጥ – ልክ እዚህ ሜዳሊያ ላይ እንደተቀረፀው ቀይ ልብ ያለ – በሀገር ፍቅር የሚንቀለቀልን የወገናዊነትን ህዋስ ይረጭብን ዘንድ – በመላ ህዋሳችን ሁሉ ውስጥ – ታላቅ የሀገር ፍቅርን መንፈስ ያሰርፅብን ዘንድ – እርስበርስ እጅ-ለእጅ የሚያስተሣስረንን – ልብ-ለልብ የሚያቆላልፈንን – ታላቅ የፍቅር መንፈስ ይዘራብን ዘንድ – እንለምነዋለን አምላካችንን፡፡ አምላክ – ለመላው – ከኢትዮጵያ ጫፍ እስከ ጫፍ – ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተሠራጭተን ለምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ – ለሁላችንም – በወገናዊ ፍቅር እየተዋደድን የምንጓዝበትን፣ በህብረት ተዋድደን የምንኖርበትን – በፍቅር ተፈላልገን የምናዘግምበትን – ታላቅ የፍቅር ጎዳና  – ታላቅ የፍቅር ልብን ከፊታችን እንዲዘረጋልን – በያለንበት ፍቅርን እንዲሰጠን – በመካከላችን እንዲያፀናልን – በቸርነቱ እንዲለግሰን – በእውነት – በየእምነታችን – በየአንደበታችን – በየልባችን እንለምነው እስቲ፡፡
ስለሚያፈቅር ልባችን – ስለሚተሳሰብ ኃይላችን – ስለሚያዋድደን ፀጋችን – ስለታላቁ አብሮነታችን – የአብርሆት ፀጋን ስላላበሰን ህሊናችን – በችግር መከራ ጠውልጎ ስለማይሞት ኢትዮጵያዊነታችን – ስለታላቅ የዘመን ብርታታችን – ስለለሰጠን ወገናዊ መዋደድና መስዋዕትነት – ስለተደረገልንና ስለሆንነው መልካሙ ሁሉ ሰብዕናችን – ስላልሆነብንም ስላልደረሰብንም ስለታደገንም መከራችንም ስንል ደግሞ – ቸሩ አምላካችንን – በጨዋ ወግ – እነሆ ከወገባችን ጎንበስ ብለን – በተሰበረ ልብ ተንበርክከን – እናመሰግነዋለን – ስሙን እንጠራዋለን አምላካችንን፡፡ አምላክ – በመከራም ሆነ በፍስሐ – ሁላችን ከነልጆቻችን ወጥተን የምንገባባትን – ውዲቱን እናታችንን – እምዬ ኢትዮጵያን – አብዝቶ አብዝቶ ይባርክልን፡፡ እምዬ ኢትዮጵያ – በልጆቿ ታላቅ ወገናዊ ፍቅር ፀንታና ደምቃ- ለዘለዓለም ትኑር፡፡
Filed in: Amharic