>

ለአዲስ አበባ እና ዙሪያው ቄሮዎችና ፋኖዎች ማሳሰብያ!!! (ፕሮፎሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ)

ለአዲስ አበባ እና ዙሪያው ቄሮዎችና ፋኖዎች ማሳሰብያ!!!
ፕሮፎሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ
ከእዚህ በታች ፋኖ የሚል ቃል የተጠቀምኩት ታጋይ የአማራ ወጣቶችን ለመግለጽ እንጂ መላው የአዲስ አበባ ወጣት ፋኖ ነው ለማለት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። ደጋግሜ የአዲስ አበባ የአማራ ወጣቶች ከምል ይልቅ ፋኖ ብዬ አጠቃልዬዋለሁ። አንባብያን መጠሪያውን ችላ ብላችሁ ቁምነገሩ ላይ አተኩሩልኝ።
ቄሮዎችና ፋኖዎች እስከ አሁን በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ ለተጀመረው የነጻነት ድል በቅታችኋል። ይህም ፍቅርና ሕብረታችሁ እጅግ ደስ ያሰኛል። ሆኖም ሰሞኑን በ ኦነግ የትግል አርማ እና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሰንደቅአላማ ሰበብ የተነሳ በአንዳንዶቻችሁ መሀል አለመግባባት እና ግጭት መከሰቱን ሰምቼ በጣም አዝኛለሁ።
እኔ በምኖርበት በአሜሪካን ሀገር እያንዳንዱ ስቴት የሚያውለበልበው የእየ ራሱ የመለያ አርማ አለው። ከእሱ በተጨማሪ እና ከፍ ብሎ የሚውለበለብ 52ቱን ስቴቶች እና መላውን የአሜሪካ ህዝብ የሚወክል 52 ኮከቦች ያሉበት ሰንደቅአላማ አለ። ሁለቱንም ሰንደቅአላማ ያውለበልባል።  ለምሳሌ በካሊፌርንያ ድብ ያለበት የካሊፎርንያ አርማ ከብሄራዊው ባለ 52 ኮከቦች ሰንደቅአላማ ጎን ይውለበለባል። በእዚህ ሁሉ አሜሪካኖች ቅር ተሰኝተው አይጣሉም። እናንተም በኦነግ የትግል አርማና በብሄራዊው ሰንደቅአላማ ምክንያት እባካችሁ አትጣሉ። እናንተ ስትጣሉ ደስ የሚላቸው ወይም እንድትጣሉ የሚፈልጉ ጸላኤ ፍቅርና አንድነት ስለአሉ በጣም ተጠንቅቃችሁ በጀመራችሁት ፍቅርና ሕብረት ቀጥሉባቸው።
የኦነግ ደጋፊ ቄሮዎች አርማውን በሰላም አውለብልቡ እንጂ የተሰቀለውን ብሄራዊ ሰንደቅአላማ አታውርዱ። ይህ በፍጹም ተገቢ አይደለም። የኦነግ ደጋፊ ያልሆኑትን እና በብሄራዊ ሰንደቅአላማው የሚወከሉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችሁን ያሳዝናል። ያስቆጣልም። እስከዛሬ የተደከመበትን ፍቅርና አንድነትም ያጎድፋል።
ፋኖዎች ደግሞ መታገስን ተማሩ። በአለፉት መሪር የትግል ዘመናት የኦነግን የትግል አርማ እንደታገሳችሁ አሁንም በጥበብ ታገሱ። ትግሉ ገና አልተፈጸመም። ቄሮን ተመስለው የሚያበጣብጡ መሰሪዎች እንደ አሉም ለደቂቃ አትዘንጉ። ቄሮዎችም እንዲሁ ፋኖን ተመስለው ጠብ የሚጭሩ እኩይዎች እንደአሉ አትርሱ።
ቀጥሎ መንግሥት በመገናኛ ብዙሀን ብቅ ብሎ በትግል አርማና በብሄራዊ ሰንደቅአላማ መሀል ያለውን ልዩነት አብራርቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ መግለጫ እንዲሰጥ እና ግጭት ያሉበት ቦታዎችንም በመከታተል
በሽምግልና እና ካስፈለገ በፓሊስ ኃይልም ባስቸኳይ መፍትሄ እንዲያደርግ ለመንግሥት አቤቱታ አቀርባለሁ።
ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ (ፒኤች ዲ)
የሁማኒቲስ ፕሮፌሰር
Filed in: Amharic