>

የተፈለገው ነገር ምንድን ነው?  የተፈጠረው ስሜትስ ምንድን ነው?  (በናሁሰናይ በላይ)

የተፈለገው ነገር ምንድን ነው? 
የተፈጠረው ስሜትስ ምንድን ነው? 
በ ናሁሰናይ በላይ 
የህዳሴ ግድብ ከሃይል ማመንጫ ግድብም በላይ ነው። በዚህ መንፈስ ነበር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የአቅሙን ለማበርከት በላቀ ሃገራዊ ስሜት የተንቀሳቀሰው። እንደማነኛዉም የመንግስት ሰራተኛ የወር ደሞዝ ብቻ ሳይበቃኝ ለትምህርት ጄኔቫ በቆየሁባቸው ዓመታትም ከበርካታ ኢትዮጵያዊ ጋር በመሆን ትልቅ ኮንሰርት አዘጋጅተን በርካታ ብር ገቢ ማድረግ  ችለን ነበር። ይህ የአብዛኛው ግድቡን የደገፍን ኢትዮጵያዉን ታሪክ ነው። ግድቡ ስትራቴጅያዊ ስራ በመሆኑ አያያዙም ስትራቴጅያዊና ዉጤቱም የሃገርን ቁመናና የሚወስን ስትራቴጅያዊ ጠላት አእነና ወዳጅ በግልፅ የተሰለፈበት ጉዳይ ነው። በዚህ ዙርያ ተፎካካሪ ብሎ ነገር የለመም፡፡ ምሽግ ተቆፍሮ ከሚደረግ ጦርነት በላይ የሆነ ዉስብስብ ጦርነት ነው። ባጭሩ ጉዳዩ ነጮች መሆን አለመሆን የሚሉት የሃገራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው። ስንገመግመዉም ስንደግፈዉም ስትራቴጅያዊ ፕሮጀክት መሆኑ ታሳቢ በማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር በቅርብ ግዝያት እየሆኑ ያሉ ነገሮች እንገምግማቸው።
የሜቴክ ጉዳይ
ሜቴክ ለዓመታት በርካታ ክሶች ስሞታዎች፣ ዉንጀላዎች ሲቀርቡበት የነበረ ተቋም ነው። እንደ ማነኛዉም ዜጋ እኔም የምሰማዉና የሚወራው ያሳስበኛል። አጥፍተው የተገኙ ሰዎችም በህጉ መሰረት መጠየቅ ካለባቸው መጠየቅ አለባቸው። ይህ በስትራቴጅያዊ ጉዳያችን የሚታይ የህግ ጉዳይ ሆኖ፤ የኔ ስጋትና ጥያቄ ግን እንዴት ነው ደምብ የለበሱ ሚስኪን ፖሊሶችን የገደለ ነፃ ተብሎ በጀግንነት እየተሸለመ በምን ሞራል ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ማሳደድ ይቻላል? የሚለው ነው። ፖለቲካዊ ጥቅም ህግን ካሸነፈ ህዝቦች ሊተማመኑበት የሚችሉ የህግ ስርዓት በማይኖርበት ግዜ ህግን ማክበርና ማስከበር ተገቢ በሚሆንበት ሰዓት ላይ እንኳን አሽቸጋሪ ይሆናል። ለሃገሩ ሲሰራ የተሳሳተ ተሳዳጅ፣ ኢትዮጵያን በተጨባጭ ለማተራመስ ሌት ተቀን የሰራ ኢሳያስ ተወዳሽ በሆኑባት ኢትዮጵያ በምን አግባብ ህግን መጥቀስ ይቻላል? የሚለው መንግስት ራሱ ይመልሰው። በበኩሌ አሁንም ትላንትም ህግን ጥሰው በሰው ህይወትና በሀገር ንብረት ጉዳት ያደረሱ ሁሉም በእኩል መዳኘት ስላለባቸው የሜቴክ ሃላፊዎችም መጠየቅ ካለባቸው ይጠየቁ እያላኩ ወደ ዋና ጉዳየ ልግባ:: የኔ ስጋት ከሜቴክ ጋር ማያያዝ ለሚፈልግ አንድ ነገር ልበል፥ ብትፈልግ ሜቴክን ገንድሰው፣ ጠቅላላ አመራሩም በሞት ቅጣው፣ አይሞቀኝ አይበርደኝ፤ ሂደቱ ህግ ተከትሎ እስከሄደ ድረስ። ጉዳየ የገባንበት ስትራቴጅያዊ የመሆን ያለመሆን ጦርነት የሚመለከት ነው።
የሰሞኑ ዶክመንተሪ ዓላማው ምንድን ነው? 5 መላምቶች ላስቀምጥ
አንድ፥ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በነበራቸው ቆይታ (ግማሽ የተሳተፍኩበት) ስለ ታላላቅ ፕሮጀክቶች መዘግየት ባነሱበት ግዜ የህዳሴው ግድብም ችግር እንዳለበትና በዚህ ፍጥነት ከሄደ በሚቀጥሉት አስር አመታትም ላያልቅ ይችላል ብለው ነበር :: ይህ ብዙ ጥያቄዎችና ክርክሮች አንስቶ እንደነበር ይታወሳል። የግድቡን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎችን በተለይ አስደንግጥዋል። ይህ ግብፆች ከሚያነሱት ግድቡ በአስር አመት እንዲሞላ ይደረግልን ከሚለው ጥያቅያቸው ጋርም ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ የጉዳዩ የቅርብ ባለቤቶች ነገርየዉን ከሌላ አቅጣጫ አይተዉት ተረብሸዋል። አሁን አመራር የሆነው ሃይል ወደ ስልጣን በማምጣት ረገድ ግብፅ ሚና ነበራት ብለው ለሚያምኑ ደግሞ ትርጉሙ ሌላ ነበር:: በነሱ አነጋገር ይህ ንግግር ለግብፅ  የተቸረ ስጦታም አድርገው ቆጥረዉታል። ከዚህ ስንነሳ በተደጋጋሚ እየታየ ያለው ዶክመንተሪ የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቃል ልክ እንደሆነ ለማስረገጥ ነው ማለት ይቻላል።  በዛዉም በስፋት የተሰራጨው ግድያው ከጠቅላዩ ጋር ተያይዞ የሚወራዉን ፉርሽ ለማድረግ ሊሆን ይችላል።
ሁለት፥ በጠቅላይ ሚንስቴሩ ንግግር የተፈጠረውን ዉዝግብ ተከትሎ፣ ቢቢሲ አማርኛ ኢንጅነር ስመኘው ከመሞታቸው አንድ ቀን በፊት ተጠይቀው  የግድቡ ስራ በታቀደለት እየሄደ ነው፣ ስራችን እየሰራን ነው ብለው መልሰው ነበር።  ይህ በተናገሩ በነገታው መስቀል አደባባይ ሞተው ተገኙ። ይህም ህዝቡን ለሌላ ቁጭት ዳረገው ብዙ ግምታዊ ዉንጀላዎችና መላምቶችም ተሰነዘሩ። አንድ እዉነት ግን አለ፣ መንግስት ይህንን ህዝባዊ ቁጣ ተጠቅሞ ህዝቡን ለበለጠ ቁርጠኝነት አላነሳሳዉም። ጉዳዩ ስትራቴጅያዊ ትግል መሆኑ ተረስቶ ተራ የግድያ ምርመራ ጉዳይ አድርጎ ቴክኒካል በሆነ መልክ ሊያልፈው የፈለገበት ምክንያት ብዙዎችን አስደንግጣል።
ሁለተኛው መላምት መንግስት ይነግረናል ተብሎ ለሚጠበቀዉን ሪፖርት መደላድል እያዘጋጀ ነው የሚል ነው። ይህ ማለት ኢንጅነር ስመኘው “ራሱን ነው ያጠፋው” ምክንያቱም ፕሮጀክቱ ደካማ ነበር ለማለት እንዲመቸው ሊሆን ይችላል ማለት ነው።
ሶስት፥ የሜቴክ አመራሮች በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል በህዝቡ በኩል ግፊት እንዲፈጠርና በቀላሉ ለመያዝ እንዲቻል። በበኩሌ ይሄ ወሃ የማይቋጥር ነጥብ ነው። ምክንያቱም አመራሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተጠይቆ እምቢ ያለ የለም ብቻ ሳይሆን የሚመለከተው አካል ያለመተባበር ነገር አላሳየም። ሆኖም አሁን ፖለቲካዊ እርባናና ስሌት ህግን እየደፈጠጠ ወዳጅ የተባለ ካጠፋ የማይቀጣበት ዓይነት ከባቢ ስለተፈጠረ ነገሩን አስቸጋሪ ሊያደርገው ቢችልም፤ አንድ ሁለት ሰዎች በህግ ለመጠየቅ ሲባል የህዝቡን ሞራል የሚያላሽቅ ዶክመንተሪ ይሰራል ብየ አልገምትም። ለማሰር ዶክመተሪ ሳይሆን የፍርድቤት ማዘዣ ብቻዉን በቂ ነው። እስካሁን ያየነዉም ይሄ ነው። ህዝቡም የኢንጅነሩ ጉዳይ ሪፖርት በቀላሉ እንዲቀበለው ያደርግ ይሆን ተብሎ ሊታሰብ ይችላል። ሰፊ ስነልቦናዊ ዘመቻ በማድረግ ግድያው ከሜቴክ ጋር ለማያያዝ እንዳይባል ኢንጅነር ስመኘው የሰጣት የመጨረሻዋ ቃለ መጠይቅ ላይ የተቃረነው ጠቅላይ ሚኒስቴሩን እንጂ ሜቴክን ስላልሆነ ይህም ሩቅ እሚወስደን ሙግት አይሆንም።
አራት፥ በኢህአዴግ ዉስጥ ባለው የዉስጥ ሹክቻ ሜቴክን ተጠቅሞ ህወሓትን መምታት። ይህ አልጂዚራ ላይ የቀረበው የጆርጅ ዋሽንግተን ፕሮፌሰርም ይጠቅሰዋል። ሜቴክ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ ነው። ስለዚህ ጉድለት ተፈፀመባቸው የተባሉ ዓመታት ደግሞ ሃይለማርያም ጠቅላይ የነበረባቸው ግዝያቶች ናቸው። አብይ የያዛት ወምበር ነበር ሃይለማርያምም የያዛት። ወምበር ሲያዝ ከነጥቅሙና ሃላፊነቱ መሆኑ ግልፅ ነው። ስለዚህ በተጠያቂነት ሰንሰለትም ይሁን በሌላ ነገር ከህዋሓት ጋር ባይገናኘም በህዝቡ ያለው ስሜት ተጠቅሞ ህወሓትን መከትከቻ ማድረግ ታስቦ ሊሆን ይችላል። በዚህም በነሱ አነጋገር ህወሓት ጀምራ ያበላሸችው ነገር አብይ ነው የጨረሰው ( ከተጨረሰ ነው) ለማለትና የታሪክ ሽምያ አካል ለመሆን ሊሆን ይችላል። ተወደደም ተጠላም ይህ ግድብ የመለስ ሃወልት ሆኖ ይኖራል፤ ቢያልቅም ባያልቅም። ሜቴክ አለቃው አባይ ወልዱ ወይም ደብረፅየን ሳይሆኑ ሃይለማርያም ነበር። ዋና አመራሩ ትግራዋይ ስለሆኑ ግን ህወሓትና የትግራይ ህዝብን ለማሸማቀቅ የሚፈልግ አካል መሳርያ እያደረገው ነው። የሚገርመው ነገር ግድቡን ሲቃወሙ የነበሩ ወይም በዝምታ አንዲትም ነገር ለማበርከት ፍቃደኛ ያልነበሩ ሰዎች የግድቡን መሰራት ያለአንዳች ጥርጣሬ ሲደግፍ የነበረዉን ህዝብ መዉቀሳቸው ያስተዛዝባል። የዲያስፖራ የተዋጣው ብናየው የምናዉቀው እናዉቀዋለን።
አምስት፥ በግብፅና ሌሎች የኢትዮጵያ የዉስጥ አቅም መጠናከር እንቅልፍ የሚያጡ ሃይሎች የሚደረግ ሊሆን ስለመቻሉ። ሜቴክ የያዛቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች በርካታ ካፒታል የሚፈስባቸው በመሆናቸው የብዙ ትላልቅ ካምፓኒዎች የአይን ማረፍያዎች ናቸው። የሜቴክን ድክመት ተገን አድርገው የራሳችን አቅም እንዳንገነባ የሚፈልጉና እንደ ግብፅ አይነት ደግሞ ግድቡን ማስቆም ወይም ማኮላሸት የሚፈልጉ ሃይሎች ስትራቴጅያዊ ጠላታቸው ሜቴክ ነው። በዛ ላይ የግድቡ ወሳኝ ክፍሎች ለመቆጣጠር አለመቻል ብሄራዊ የድህንነት ስጋት አድርጋ ለምታየው ግብፅ ሜቴክ ራስ ምታት ነው። እድገት ማለት የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሆነ ጠንቅቀው የሚረዱ ምዕራባዉያንም ዘዉትር ተመፅዋች እንድንሆን ካላቸው ፍላጎት ሜቴክ ቢጠፋ ደስታቸው አይችሉትም። በዚህና በሌላ ምክንያት ሜቴክን ማጥፋት በኢኮኖሚው ዘርፍ ሉዓላዊነትን መስበር ስለሚችሉ ይረባረቡበታል። ሜቴክ በተሰጠው ግዴታና ሃላፊነት መጠን ይሰራ ነበር የሚለው ለክርክር ትተን።
ማጠቃለያ
በኔ እይታ የህዳሴ ግድብ ማለት ክስትራቴጅያዊ ጥቅማችን ተነስተን የገባንበት ህዝቡም በሰፊ ድጋፍ የተሰለፈበት ጦርነት ነው። የሃገርን ክብር እና ሉዓላዊነት ወደላቀ ደረጃ ክፍ ለማድረግ የሚደረግ ጦርነት። በግምባር ምሽግ ቆፍረን ከምናደርገው ጦርነት የባሰ ከባድ እና የተወሳሰበ ጦርነት ነው። ህዝቡም ይህን ተገንዝቦ ያለ የሌለ ሃብቱና ጉልበቱ ያለስስት እየገበረ የነበረው። ይህ ስትራቴጅያዊ ፕሮጀክት ሰፊ ህዝባዊ አቅም ማሰባሰብ የቻለ፣ የብዙዎቹን ልብ በተስፋ የሞላ፣ ስለነገዋ ኢትዮጵያ የህዳሴ ችቦ የለኮሰ ነገር ነው። የይቻላል መንፈስን የተከለ፣ ከተባበርን የማንችለው ነገር እንደሌለ ያሳየ ስራ ነው።
ሆኖም ሰሞኑ በዋልታና በፋና የተለቀቀው ቪድዩ ዓላማና ዒላማው ምንም ይሁን ምንም የኢትዮጵያን ህዝብ ቅስም የሰበረ፣ የኩራት ምንጫችን በሆነው እንድናፍር ያደረገ፣ በስንት ዘመን የተሰበሰበው ሃይል የሚበትን፣ ዳግም ህዝቡ በታላላቅ ፕሮጀክቶች እምነት እንዲያጣ ያደረገ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ስትራቴጅያዊው የደህንነት ጉዳይ ሚስጢራዊነቱ ተጥሶ በግላጭ ለጠላት የምስራች የነገረ ቪድዮ ከመንግስት እንደመስማት ምን እሚያሳምም ነገር አለ። ጉዳዩስ ህዝብን ተስፋ በሚያስቆርጥ መልክ ያለዉን ጉዳይ መዘገብ አይቻልም ነበር ወይ? የህዝቡን ወሽመጥ ከበጠሱ በሃላ ግድቡ በዚህ ዓመት ያልቃል ብሎ ተስፋ መስጠት ያልተፈለገዉስ ለምንድን ነው? የኢንጅነር ስመኘው አሟሟትስ ለመናገር መንግስት ምክንያት እየደረደረ ያለው ለምንድን ነው?
የዚህ ዶክመንታሪ ፊልም ባለቤት ማን ይሁን ማን ይህንን ድምዳሜየን ማስቀመጥ እፈልጋለሁ። ከዚህ ዶክመንተሪ ምን ትርፍ አገኘን? ወሳኙ ጥያቄ ይሄ ነው።
ይህ ዶክመንተሪ ሌላ ስም አያስፈልገዉም፤ የሃገር ክህደት አዋጅ ነው። በህዝቡ ሞራል እና ተስፋ ላይ የሚረማመድ አካል ብቻ ሊፈፅም የሚችለው። በጦርነት ያለ ሃገር በጦርነቱ ሂደት የገጠመዉን ችግር በይፋ አዉጥቶ (ዝርዝር ቴክኒካል ጉዳዮች ሳይቀር)፣የሰበሰበዉን ህዝባዊ ሞራልና ድጋፍ ዲሞቢላይዝ አድርጎ (ወታደሩን በትኖ) የራሱን ህዝብ ቅስም ሰብሮ ተጋጣሚዉን ሲያስደስት ሰምቼም አይቼም አላዉቅም:: ሲታይና ሲሰማ ደግሞ ስም አለው፤ Treason ይባላል። የሀገር ክህደት። ከዚህ ዶክመንተሪ የተፈለገው ነገር ተሳክቷል፤ ህዝቡ ሞራሉ ደሽ ብሎ፣ ተስፋ ቢስ አድርጋቹሁታል። የመለወጥ ህልሙ ላይ ቀዝቃዛ ዉሃ ቸልሳቹሁበታል። በስፋት የሰፈነው የመጠላላት ስሜት በእጥፍ ጨምሮታል፣ ተጨማሪ የሚያባላን እርሾ ተሰጥቶናል።ግድቡ የደረሰበት ደረጃና የተጋረጡበት አደጋዎችም ማወቅ የለብንም አይደለም እያልኩ ያለሁት። የኔ ስጋት ከሜቴክ ጋር ማያያዝ ለሚፈልግ መግብያ ላይ ያልኩትን ልድገመው፤  ብትፈልግ ሜቴክን ገንድሰው፣ ጠቅላላ አመራሩም በሞት ቅጣው፣ አይሞቀኝ አይበርደኝሂደቱ ህግ ተከትሎ እስከሄደ ድረስ። ተጠያቂነት መስፈን አለበት የሚለው የዘዉትር ኣቋሜም በቦታው ነው። ይህንን ዶክመንታሪ ያዘጋጀህ አካል በሃገሬ ህልም ላይ ቆመህ ሳይህ ግን በስምህ እጠራሃለሁ። ከሃዲ ብየ።አመሰግናለሁ!
Filed in: Amharic